አሜሪካ በአደራዳሪዎች በኩል አዲስ ምክረ ሃሳብ ማቅረቧን ኢራን አስታወቀች
የኢራን ፓርላማ አፈጉባኤ የሆኑት ሞሃመድ ባጋር ጋሊባፍ፣ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በሰባት ቀን ውስጥ ዳግም ለመክፈት የሚያስችል ዕቅድ ካቀረበች በኋላ ዋሽንግተን "በአደራዳሪ በኩል አንዳንድ ሀሳቦችን" እንዳቀረበች ተናገሩ።
ነገር ግን፣ አሜሪካ "ጊዜን የማባከን እና በአንድ ወገን የሚወሰኑ ፍላጎቶችን የመጫን ዘመን ማብቃቱን" ማወቅ እንዳለባት፣ እንዲሁም የኢራን አቋም "ግልጽ እና የማያሻማ" ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢዝላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሠረት የተቀመጡት ሰባት ቅድመ ሁኔታዎቻችን ሳይሟሉ ዳግም አይከፈትም” ሲሉም አክለዋል።
ጋሊባፍ ኢራን በአሜሪካ እርምጃዎች “አትደነቅም” ወይንም “አትሸበርም” በማለት “እየተዋጋን እንደራደራለን” ማለታቸው ተሰምቷል።
“በጦርሜዳ ላይ በሙሉ አቅማችን እንገኛለን፤ አዳዲስ አስገራሚ እርምጃዎችን በመውሰድም እንገጥማቸዋለን። እንዲሁም በወታደራዊው መስክ የበላይነታችንን ለማረጋገጥ እና የኢራን ሕዝብ መብቶችን ለማስከበር የዲፕሎማሲ መንገዶችን እንጠቀማለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መክፈት ያስችላል ያለችውን ዕቅድ በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል አቅርባለች።
ቅድመ ሁኔታዎቹ በሁሉም ግንባሮች ጦርነትን ማቆም፣ የታገዱ ሃብቶችን መልቀቅ፣ በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለውን እገዳ ማንሳት እና በኢራን ውስጣዊ ጉዳይ አለመግባት፣ ከኢራን ባላጋራዎች ጋር ትብብርን ማቋረጥ እና በግዛቷ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጸም የሚጠይቁ ናቸው።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በበኩላቸው ቴህራን “ራሷን ለመከላከል ቁርጠኛ የሆነችውን ያህል ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመፈለግም ቁርጠኛ ነች” ብለዋል።
ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው፣ አራግቺ ከውጭ አገር አምባሳደሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ፍትሃዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ዝግጁ ነን፤ በተመሳሳይ ጊዜም ለማንኛውም ወታደራዊ ጥቃት የከፋ ምላሽ ለመስጠትተዘጋጅተናል” ብለዋል።