በየመን ያለው ረሃብ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ
በየመን ያለው ረሃብ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን እና ምግብ ማግኘት የማይችሉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ።
በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣው ግጭት በርካታ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን ገበያዎች እንዲስተጓጎሉ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲገደብ አድርጓል።
በየመን ሁቲዎች እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ባገረሸው ጦርነት ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
ሁለቱ ወገኖች አአአ በ2022 የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ በተቀሰቀሰው ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ ከሆነ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ149 ሺህ በላይ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው ለመውጣት ተገደዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በድጋሚ የተፈናቀሉ ናቸው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ማቲው ሆሊንግዎርዝ እንዳሉትም መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች በአሳሳቢ ሁኔታ በርካታ ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት አልቻሉም።
በአማካይ ከአራት የቤተሰብ አባላት ውስጥ ሦስቱ ምግባቸውን እንደሚዘሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የየመን አካባቢዎች ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንደሚኖር ይገመታል።
በአጠቃላይ በየመን 18.3 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ሲሆን 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ከባድ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አለባቸው። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ያለባቸው የምግብ እጥረት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል እና እጅግ የከፋ ነው።