በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች አምስት የነዳጅ ጫኝ መርከብ ሰራተኞች ተገደሉ
በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ አምስት የመርከብ ሰራተኞች መገደላቸውን አንድ ከፍተኛ የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
የፑንትላንድ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ቢል ቃቦውሳድ እንዳሉት አምስቱ ባሕረተኞች የተገደሉት በባሕር ላይ ወንበዴዎች ነው።
ተጠልፋ የቆየችው እና 'ኤምቲ ሆርነር 25 የተሰኘችው' ነዳጅ ጫኝ መርከብ በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋሏን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ባሕረተኞቹ የተገደሉት መርከቧ በጸጥታ ኃይሎች እጅ ከመግባቷ አስቀድሞ እንደሆነ ገልጸዋል ።
ሟቾቹ ሦስት ፓኪስታናዊ፣ ሕንዳዊ እና ምያንማራዊ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሦስት ፓኪስታናዊ እና አንድ ሕንዳዊ እንዲሁም ሌሎች አራት ባሕረተኞች ላይም ጉዳት ደርሷል።
ነዳጅ ጫኝ መርከቧ ወደ 18 ሺህ 500 በርሜል ነዳጅ ጭና ወደ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ እየተጓዘች ሳለ ነበር ሚያዚያ ላይ በስድስት ታጣቂዎች የተጠለፈችው። አስራ ስድስት ተጠርጣሪ ወንበዴዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ሌሎች ማምለጣቸውን እና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
የተወሰኑ ወንበዴዎች እንዲያመልጡ ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ረድታላች በሚል የቀረቡ ክሶችን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አጣጥለዋል።
ባለሥልጣናት ወንበዴዎቹ መርከቧን እንዴት እንደተቆጣጠሩ እና አምስቱ ባሕረተኞች እንዴት እንደተገደሉ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ሆኖም ሚያዝያ ወር ላይ መርከቧ ስትጠለፍ 17 ባሕረተኞችን ይዛ እንደነበር ባለሥልጣናት ገልጸዋል። እነዚህም 10 ፓኪስታናዊ፣ አራት ኢንዶኔዥያውያን ፣ አንድ ሕንዳዊ፣ አንድ ስሪላንካዊ እና የምያንማር ዜጋ ናቸው።
ከአውሮፓውኑ 2011 ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ዘመቻዎች በኋላ የወንበዴዎች እንቅስቃሴ ቢቀንስም ጥቃቶች እና ጠለፋዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደገና ጨምረዋል።