በሶማሊያ ሳውዝ ዌስት ግዛት ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ
በሶማሊያ ሳውዝ ዌስት ግዛት መዲና ባይዶዋ ዛሬ ጠዋት በመንግሥት ኃይሎች እና የቀድሞው ፕሬዚደንት አብዲአዚዝ ሃሰን ሞሃመድ (ላፍታጋሪን) ታማኝ በሆኑ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ።
ግጭቱ በከተማዋ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ በርካታ የባይዶዋ ጎረቤት አካባቢዎች መስፋፋቱን ገለልተኛ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በግጭቱ የደረሰው ጉዳት እስካሁን አልታወቀም።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ላፍታጋሪን ቃል አቀባይ ኃይላቸው የበላይነት ማሳየቱን የገለጹ ሲሆን፤ ቢቢሲ ግን እርሳቸው ያሉትን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
ግጭቱን በተመለከተ አስተያየት የሰጠው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በበኩሉ ዛሬ ጠዋት ባይዶዋ ከተማ ላይ ጥቃት የፈፀመውን ቡድን “ ሽብርተኛ” ሲል በመግለጽ ከባድ ሽንፈት መከናነባቸውን ገልጿል።
የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም ፊቂም በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “ ባይዶዋ ላይ ጥቃት የፈፀሙት "መንትዮቹ ሽብርተኞች ከባድ ምት አስተናግደዋል” ብለዋል።
ሚኒስትሩ መንትዮች ሲሉ የገለጿቸው የቀድሞው የደቡባዊ ምዕራብ ግዛት ፕሬዚደንት አብዲአዚዝ ላፍታጋሪን ታማኝ ወታደሮች እና ከዚህ በፊት ካጋጠሙ ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር በተያያዘ የሚከሰሰው አል ሸበብ ቡድኖችን ነው።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ታማኝ ኃይሎች ቃል አቀባይ ሃሰን አብዲ መሐመድ ኃይላቸው “ባይዶዋን እና አጠቃላይ ደቡብ ምዕራብ ግዛትን ለመቆጣጠር መቃረባቸው” ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ግን ባይዶዋ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር መሆኗን ገልጿል።
ሁለቱም ወገኖች ያሉትን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም። ነዋሪዎችም ስጋት የገባቸው ሲሆን በቤታቸው ተጠልለው ይገኛሉ።
የአሁኑ ግጭት መከሰቱ የተሰማው ነዋሪዎች በከፋ ረሃብ ቀውስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ባለበት ወቅት ነው።