ቀጥታ, ትራምፕ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክን እንደሚያግዱ ከዛቱ በኋላ አውሮፓ የነዳጅ ክምችቷን እንድትለቅ ሊጠይቁ ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክን ልታግድ እያሰበች በመሆኗ የአውሮፓ አገራት ከክምችታቸው የተወሰነውን እንዲለቅቁ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የተሰማው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት፣ አውሮፓ አገራት የነዳጅ አቅርቦታቸውን ወዲያውኑ ለመልቀቅ ዝግጅት እንዲያደርጉ ካሳሰቡ በኋላ ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየመን ያለው ረሃብ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ

    የተፈናቃይ መጠለያ ድንኳኖች

    በየመን ያለው ረሃብ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን እና ምግብ ማግኘት የማይችሉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ።

    በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣው ግጭት በርካታ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን ገበያዎች እንዲስተጓጎሉ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲገደብ አድርጓል።

    በየመን ሁቲዎች እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ባገረሸው ጦርነት ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

    ሁለቱ ወገኖች አአአ በ2022 የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ በተቀሰቀሰው ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

    እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ ከሆነ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ149 ሺህ በላይ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው ለመውጣት ተገደዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በድጋሚ የተፈናቀሉ ናቸው።

    የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ማቲው ሆሊንግዎርዝ እንዳሉትም መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች በአሳሳቢ ሁኔታ በርካታ ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት አልቻሉም።

    በአማካይ ከአራት የቤተሰብ አባላት ውስጥ ሦስቱ ምግባቸውን እንደሚዘሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የየመን አካባቢዎች ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንደሚኖር ይገመታል።

    በአጠቃላይ በየመን 18.3 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ሲሆን 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ከባድ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አለባቸው። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ያለባቸው የምግብ እጥረት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል እና እጅግ የከፋ ነው።

  2. “ከእኛ በስተቀር ማንም አፍሪካን ታላቅ ማድረግ አይችልም” አፍሪካዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ

    ናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ

    ናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ “ከእኛ ከአፍሪካውያን ውጭ ማንም አህጉሯን ታላቅ ማድረግ አይችልም” ሲሉ አፍሪካውያን በውጭ ላይ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ የአህጉራቸውን መፃዒ እድል በእጃቸው እንዲያደርጉ አሳሰቡ።

    ቢሊየነሩ ይህን ያሉት በኬንያ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ በምትገኘው ላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ማስጀመራቸውን ተከትሎ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ ነው።

    ዳንጎቴ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው የአፍሪካን ችግሮች እና እድሎች እንዲሁም ጥንካሬን የተመለከቱ አጫጭር መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።

    በዚህም የአፍሪካ ትልቁ ችግር የሰዎች፣ የምርቶች እና አገልግሎቶች ዝውውር አለመኖር እንደሆነ በመጥቀስ የአፍሪካ የነፃ ንግድ ስምምነት በተግባር መስራቱን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

    አፍሪካ ወጣት እና ታታሪ ሕዝብ ያላት እንዲሁም የነዳጅ ድፍድፍን ጨምሮ የሌሎች ማዕድናት ባለቤት መሆኗ ለአፍሪካ ትልቅ እድል መሆኑንም ዳንጎቴ አንስተዋል።

    ሆኖም “አፍሪካውያን በገዛ አህጉራችን ኢንቨስት ማድረግ ስለምንፈራ እና የውጭ ሰዎች መጥተው ያንን እንዲያደርጉ ስለምንፈልግ አፍሪካ ያላትን አቅም መጠቀም አልቻለችም” ብለዋል።

    “የውጭ ሰዎች የእኛን አህጉር ታላቅ ማድረግ አይችሉም፣ ከእኛ በስተቀር ማንም መጥቶ አፍሪካን ታላቅ ማድረግ እንደማይችል እኛ አፍሪካውያን መረዳት ይኖርብናል።” ሲሉም አስረድተዋል።

    ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኬንያ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ ላሙ ውስጥ 16 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታን በይፋ ያስጀመሩት በዚህ ሳምንት ነበር።

    የነዳጅ ማጣሪያው ሲጠናቀቅ በቀን 700 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እንደሚያመርት የሚጠበቅ ሲሆን ይህም በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የኢንደስትሪ ፕሮጀክት ያደርገዋል።

    በግንባታው ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጨምሮ የዩጋንዳ፣ የቶጎ እና የቤኒን መሪዎች ተገኝተዋል።

    በናይጄሪያ ካኖ ግዛት የተወለዱት የ67 ዓመቱ ዳንጎቴ፣ 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተጣራ ሃብት እንዳላቸው የፎርብስ መጽሔት መረጃ ያመለክታል።

    የሀብታቸው መነሻም በናይጄሪያ የሚያካሂዱት የሲሚንቶ እና የስኳር ንግድ ሲሆን፣ በኋላ ንግዳቸውን እና ምርታቸውን ወደ 16 ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አስፋፍተዋል።

  3. ጠ/ሚ ዐቢይ “መንገድ ስተው ከአገራቸው በተቃራኒው ለቆሙ” የሰላም በር ክፍት መሆኑን ተናገሩ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

    የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መንገድ ስተው ከአገራቸው በተቃራኒው የቆሙ" ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ዓርብ መስከረም 22/2019 ዓ.ም. መከበር የጀመረውን የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

    ዐቢይ ኢትዮጵያ የደኅንነት እና ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ውስጥ በገባችበት ወቅት በጽሑፍ ባስተላለፉት መልዕክት “ ከአገራቸው በተቃራኒ የቆሙ” ያሏቸውን አካላት በስም አልጠቀሱም።

    የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ህወሓት እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች "የዐቢይን መንግሥት ለመጣል" ያለመ "ትብብር ለኅልውና" ጥምረት መመስረታቸውን ካስታወቁ እና የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ካገረሸ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    በመልዕክታቸው “ኦሮሞ በትግሉ ነጻ ወጥቷል፤ ከዚህ በኋላ በጠብመንጃ አፈሙዝ እና ከጠላት ጋር በመወገን የሚመለስ የኦሮሞ ጥያቄ ፈፅሞ አይኖርም” ያሉት ዐቢይ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋውን፣ ባህሉን እና እሴቱን ለማሳደግ ያነሳውን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ የተደረገውን ጥረት አንስተዋል።

    ለዚህም “ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ወደ መልካው መመለሱን" እና "የሆራ አርሰዴ ኢሬቻ ደግሞ በቢሾፍቱ ውበት ደምቆ መከበሩን" በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

    በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን እንዲያጠናክር እና ሰላምን፣ እርቅን እና ወንድማማችነትን እንዲያበረታታ ጥሪ አቅርበዋል።

    በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የዐቢይ አስተዳደር የደኅንነት እና ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል።

    ኢትዮጵያ ትናንት በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን መዝጋቷን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችን በ48 ሰዓታት አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች።

    ኤርትራም በምላሹ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጧን አስታውቃለች። ግብፅ በበኩሏ አንድ ዲፕሎማቷ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከታዘዙ በኋላ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች።

    ውጥረቱ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ያሳሰበ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረትም ሦስቱ አገራት ሁኔታውን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

  4. በፈረንሳይ በተማሪዎች ተቃውሞ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

    የተማሪዎች ተቃውሞ

    በፈረንሳይ በቀጠለው የተማሪዎች ተቃውሞ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

    የመምህራን እጥረት፣ የክፍሎች መጨናነቅ እና የትምህርት ቤት ሕንጻዎች ማርጀትን በመቃወም ተማሪዎች አደባባይ ወጥተዋል።

    በያዝነው ሳምንት መባቻ ላይ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞችም ተስፋፍቷል።

    የምትህርት ሚኒስትር ኤድዋርድ ጀፍሪ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፤ 65 የትምህርት ቤት ሠራተኞች እና 40 መምህራን ተጎድተዋል።

    ማክሰኞ ዕለት ብቻ 1,949 ሰዎች መታሰራቸውንም ተናግረዋል።

    ጥቁር በጥቁር የለበሱ ተማሪዎች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ጊቢ አቅራቢያ ተቃውሞ ማሰማት ቀጥለዋል።

    ኤኤፍፒ ያነጋገራት የ16 ዓመቷ ሎላ “ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እንዳሸነፍን ነው የሚሰማን” ብላለች።

    ፖሊስ ተማሪዎቹ ላይ የኃይል እርምጃ መውሰዱንም ተማሪዋ ገልጻለች።

    የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን “ሁሉም ተቃዋሚዎች ተማሪዎች መሆናቸውን እርግጠኛ አይደለንም” ብለዋል።

    ከተያዙት 2,000 ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ገልጸዋል።

    “ከተማሪዎች ተቃውሞ ወደ ሕዝባዊ ነውጥ ተሻግሯል። አውቶብሶች ዒላማ ሲደረጉ እና ትምህርት ቤቶች በእሳት ሲጋዩ ጉዳዩ ከተቃውሞ አልፏል ማለት ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ተቃውሞው ከተጀመረ ወዲህ ወደ 100 ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    የተማሪዎች ተቃውሞ
    የተማሪዎች ተቃውሞ
    የተማሪዎች ተቃውሞ
  5. በዩኬ አየር ኃይል በተቃጣው ጥቃት የእንግሊዝ እና ኢራን ጥምር ዜግነት ያለው ግለሰብ መያዙ ተገለጸ

    ፀረ ሽብር ፖሊስ

    በራፍ ወታደራዊ አየር ኃይል ጣቢያ ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተገናኘ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር የተጠረጠረ የእንግሊዝ እና የኢራን ጥምር ዜግነት ያለው ግለሰብ መያዙን የእንግሊዝ ፀረ ሽብር ፖሊስ አስታውቋል።

    ዕድሜው 25 ዓመት እንደሆነ የተገለጸውግለሰቡ የተያዘው በለንደን ዌስትሚንስተር ሲሆን፣ በአካባቢውየሚገኙ ሁለት ንብረቶችምተፈትሸዋል።

    በግሎስተርሻየር የሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል የሚጠቀምበትየአየር ማረፊያ አቅራቢያ ባለፈው እሑድ የተያዙት በ20ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አምስቱ የዩናይትድኪንግደም ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል።

    የፀረሽብርፖሊስ “የውጭ መንግሥት ተሳትፎን ጨምሮ” ክስተቱን እያጣራ መሆኑን የብሔራዊ ፀረ ሽብር ፖሊስ ከፍተኛ አስተባባሪ ቪኪ ኢቫንስ ተናግረዋል።

    የእንግሊዝጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ረቡዕ ዕለት ኢራን በዚህ ክስተት ላይ ሚና እንደነበራት “ጠንካራ ምልክቶች” እንዳሉ ተናግረዋል።

    ሆኖም ለዚህ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጡም፤ ቴህራንም በክስተቱ ላይ ማንኛውም ተሳትፎ እንደሌላት አጥብቃ አስታውቃለች።

    አምስቱ ወንዶች የተያዙት እሑድ ማለዳ ሲሆን፣ “አጠራጣሪ የሆኑ ሦስት ተሽከርካሪዎች” በአሜሪካ አየር ኃይል ወደሚጠቀምበት የአየር ማረፊያ እየተጓዙ መሆናቸው መዘገቡ ትልቅ የጸጥታ ክስተት እንዲፈጠር አድርጓል።

    ግለሰቦቹ መጀመሪያ በፈንጂ ጉዳይ ተጠርጥረው የተያዙ ሲሆን፣ በኋላም የሽብር ተግባር ለመፈጸም ዝግጅት በማድረግ ተጠርጥረዋል። ሰኞ ዕለት በፖሊስ ዋስ እንዲለቀቁተደርጓል። ፖሊስም ይህ ውሳኔ “በምርመራ ሂደት የተወሰደ” መሆኑን ገልጾ ነበር።

    ፖሊስ በአካባቢው በተፈተሹ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የተወሰነ መጠን ያለው ነዳጅ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን ፈንጂ መሣሪያ እንዳልተገኘ አስታውቋል።

  6. ጥቃት ያደረሰው ፓይለት ‘አክራሪ ኢስላሚስት ርዕዮተ ዓለም' የሰረጸበት ነው ሲሉ ኔታንያሁ ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ በነበረው አውሮፕላን ላይ አብራሪውን በስለት የወጋው ፓይለት “አክራሪ ኢስላሚስት ርዕዮተ ዓለም የሰረጸበት” መሆኑን ተናገሩ።

    የፍላይዱባይ አውሮፕላን በረራ በጀመረ በሁለት ሰዓት ውስጥ ከ17,000 በላይ ጫማ (5,200ሜትር) ተምዘግዝጎ ወርዷል።

    ያለፈው ረቡዕ ከፓይለቶቹ አንደኛው በሌላኛው አብራሪ ላይ ጥቃት ማድረሱ ተዘግቧል። ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሠራተኞች ጥቃት አድራሹን ፓይለት በቁጥጥራቸው ሥር አውለው አውሮፕላኑ በሰላም ማረፍ እንደቻለም ተገልጿል።

    ኔታንያሁ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ የኦማን ዜግነት ያለው ጥቃት አድራሹ “አውሮፕላኑን ሊከሰክስ የሚችልበት” ዕድል ነበር።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ክስተቱ “ከሽብር ድርጊት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ” ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።

    አውሮፕላኑ ያረፈው ሳዑዲ አረቢያ ሲሆን የአገሪቱ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳለው፤ ዋና አብራሪው እና ምክትሉ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ዩኤኢ ተመልሰዋል።

    ኔታንያሁ እንዳሉት ከሆነ፤ ፓይለቱ በተሳፋሪዎች እና የበረራ ሠራተኞች ከተያዘ በኋላ “ግደሉኝ፣ ግደሉኝ” እያለ ስለነበር ራሱን “የማጥፋት” ዓላማ እንዳለው ያሳያል።

  7. ትራምፕ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክን እንደሚያግዱ ከዛቱ በኋላ አውሮፓ የነዳጅ ክምችቷን እንድትለቅ ሊጠይቁ ነው

    ነዳጅ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክን ልታግድ እያሰበች በመሆኗ የአውሮፓ አገራት ከክምችታቸው የተወሰነውን እንዲለቅቁ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የተሰማው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት፣ አውሮፓ አገራት የነዳጅ አቅርቦታቸውን ወዲያውኑ ለመልቀቅ ዝግጅት እንዲያደርጉ ካሳሰቡ በኋላ ነው።

    ቤሴንት የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ በመሆኑ፣ የአሜሪካ አርሶ አደሮች፣ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች እና ንግዶች “ጫናውን ተሸክመው መቅረት የለባቸውም” ብለዋል።

    የኢራን ጦርነት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ካደረገ በኋላ አሜሪካ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክን ልትገድብ እንደምትችል ዝታለች።

    ሐሙስ ዕለት ዩናይትድ ኪንግደም ማንኛውም ነዳጅን ወደ ውጭ መላክ ላይ እገዳ ቢጣል ምላሽ ለመስጠት የነዳጅ ክምችት ሊለቀቅ ስለሚችልበት ጉዳይ ከአውሮፓ አጋር አገራት ጋር ውይይት አድርጋለች።

    አሜሪካ ለዓለም የናፍጣ ነዳጅ ዋነኛ አቅራቢ ስትሆን፣ በቀን ከ1.2 እስከ 1.5 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጭ ትልካለች። ባለሙያዎች የአሜሪካ የናፍጣ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክ መቆሙ በሌሎች አገራት የነዳጅ ዋጋ ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት የናፍጣ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክን ስለመከልከል ሲናገሩ፣ “በደንብ እያጤንነው ነው” ብለዋል።

    ሐሙስ ዕለትም ትራምፕ የአውሮፓ አገራት ከናፍጣ ክምችታቸው የተወሰነውን እንዲለቁ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም የኢነርጂ ሚኒስትር ማርቲን ማክክሊስኪ ሐሙስ ዕለት ከአውሮፓ አቻቸው ጋር በመደዋወል ሊኖር ስለሚችለው የናፍጣ ነዳጅ እገዳ ተወያይተዋል።

    ከውይይቱ ጋር በተያያዘ መረጃ ያለው ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ዩናይትድ ኪንግደም የአውሮፓ ኅብረት አገራትን ጨምሮ ከሌሎች አገራት የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መስሎ እንደታያት ገልጿል።

    በዓለም አቀፉ የናፍጣ ገበያ ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ፣ ቻይና የአገር ውስጥ አቅርቦትን ቅድሚያ በመስጠቷ በጥቅምት ወር አንዳንድ የነዳጅ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ማቆሟ ተዘግቧል።

    ትልቅ የናፍጣ ነዳጅ አቅራቢ በሆነችው ሩሲያ የተጣለው የወጪ ንግድ እገዳም በዋጋ ላይ ያለውን ጫና ጨምሯል።

  8. ኦፕንኤአይ ስሱ መረጃን በአግባቡ ያልጠበቁ ሠራተኞችን ማባረሩን አስታወቀ

    ሳም አልትማን

    ኦፕንኤአይ ሦስት ተመራማሪዎቹ መረጃን በተገቢው መንገድ ባለመያዛቸው እንዳባረራቸው አስታወቀ።

    እነዚህ መረጃዎች ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎች ጋር በተያያዘ በውጭ ተቋም ከተሠራ ትንታኔ ጋር የሚያያዙ ናቸው ተብሏል።

    የኦፕንኤአይ ቃል አቀባይ “እነዚህ ሠራተኞች ከተቋሙ አሠራር ውጭ ስሱ መረጃን በተገቢው ሁኔታ አለመያዛቸውን ምርመራችን አረጋግጧል። ፖሊሲያችንን ጥሰዋል፤ ለሥራችን መሠረታዊ የሆነውን እምነትም አፍርሰዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የቻትጂፒቲ ፈጣሪው ኦፕንኤአይ ያባረራቸውን ሠራተኞች ማንነት ይፋ አላደረገም።

    ቢያንስ ሁለቱ ሠራተኞች ከተቋሙ የኤአይ ደኅንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ ይሠሩ ነበር።

    ሠራተኞቹ የተባረሩት ኤአይ ለሰው ልጆች ደኅንነት አደጋ ጋርጧል የሚለው ስጋት እየተስተጋባ ባለበት ወቅት ነው።

    ኤአይ እየተሠራበት ያለው ፍጥነት መገታት አለበት በሚል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችም አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

    የኦፕንኤአይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎች የአውስትራሊያ መንግሥትን ድረ ገጽ ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ኩባንያው እየተተቸ ነው።

    ከዚህ በፊትም የኤአይ ሞዴሎች የሌላ ኩባንያን የበይነ መረብ ጥበቃ ጥሰው ማለፋቸው ይታወሳል።

  9. የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አል ባሽር "አስቸኳይ" የውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተዘገበ

    የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር አል ባሽር
    የምስሉ መግለጫ, አል-ባሽር ሱዳንን ለ30 ዓመታት ያህል መርተዋል

    ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል ባሽር ለሕክምና ኻርቱም ወደ’ሚገኘው ወታደራዊ ሆስፒታል መላካቸውን እና ከአገር ውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ጠበቃቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    የ82 ዓመቱ ባሽር ለወራት ከቆየ ተቃውሞ በኋላ በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ትብብር ከሥልጣን የተወገዱት እአአአ ሚያዝያ 2019 ነበር።

    በኋላ ላይ ግን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሽግግር ሥርዓት በሚደረግበት ወቅት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የአገሪቱ ጦር ኃይላቸውን ለማዋሃድ በነበራቸው ዕቅድ ላይ መስማማት ባለመቻላቸውን ከሦስት ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ።

    ባሽር ጦርነቱ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ከእስር ቤት ወጥተው ወደ ሆስፒታል ተወስደው የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ በሰሜን ሱዳን ወደምትገኘው ሚሮው ከተማ ተወስደው በወታደራዊ ጥበቃ ሥር ቆይተዋል።

    የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ ለሕክምና ምርመራ ወደ ኻርቱም የተወሰዱ ሲሆን የተሻለ የውጭ አገር ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሯቸው ጠበቃቸው መሐመድ አልሃሳን አላሚን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ሮይተርስ እንደዘገበው የባሽር ቤተሰቦችም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባሽር ከሱዳን ውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው እና “ወሳኝ እና አስቸኳይ እንደሆነ እንዲሁም ብዙ መቆየት እንደማይችሉ” ተናግረዋል። ሆኖም ወደ ውጪ እንዲሄዱ ፈቃድ አላገኙም።

    ባሽር ያጋጠማቸው የጤና ችግር ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

    ሮይተርስ የሱዳን ጦርን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል። በርካታ የሱዳን እስላማዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ውጪ ተልከው ሕክምና እንዲያገኙ በማኅበራዊ ሚዲያ እየጠየቁ ነው።

    ሆኖም አል ባሽር በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ስለሚፈለጉ እና በሱዳን ውስጥም ክሶች ስላሉባቸው ከአገር እንዲወጡ ማድረጉ በሱዳን አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል።

    በባሽር የሦስት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ሱዳን በአሜሪካ የሽብርተኛ ደጋፊ ዝርዝር ውስጥ ተካትታ ማዕቀብ ተጥሎባታል።

    በሕዝባዊ አመጽ ወቅት ተቃዋሚዎች እርሳቸውን እና ‘እስላሚክ ናሽናል ኮንግረንስ’ ፓርቲያቸውን በሙስና እና በጭቆና ከስሰዋል።

    አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላም የተለያዩ ክሶች ቀርቦባቸው በሙስና እና በሕገ ወጥ ገንዘብ ድጋፍ ጥፋተኛ ሆነው ተፈርዶባቸዋል። በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅትም እስር ላይ ነበሩ።

  10. ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት የአየር ጥቃቶችን ፈፀመች

    ጥቃት የተፈፀመበት ሥፍራ

    ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ዘጠኝ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 11 ሰዎች መቁሰላቸውን የታሊባን መንግሥት አስታወቀ።

    የኢዝላማባድ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጦ፣ 22 ታጣቂዎችን መግደሉን ገልጿል።

    አፍጋኒስታንን የሚመራው ታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ግን በጥቃቱ ከፓኪስታን ጋር አዋሳኝ በሆኑት በኩናር እና ሄልማንድ ግዛቶች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ተመትተዋል ብለዋል። ቃል አቀባዩ በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚገኙበትም ጠቅሰው፣ ጥቃቱን አውግዘዋል።

    ፓኪስታን በበኩሏ "በደንብ የታቀደው እና ትክክለኛ የሆነ" ባለችው ጥቃት ዒላማ የተደረገው በአፍጋኒስታን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች የተከማቹበት “የሽብር ካምፖች” እንደሆኑ ገልጻለች።

    የአገሪቷ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ጥቃቱ ዒላማውን እንዳይስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል ብሏል።

    የዓይን እማኞች የአየር ጥቃቱ ትናንት ሌሊት 8:00 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ደቂቃ መዝለቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    "ተኝተን ነበር፤ የመጀመሪያው ቦምብ ሲፈነዳ ከእንቅልፋችን ተነሳን፣ ከሁለተኛው ጥቃት በኋላ ልጆቻችንን ይዘን ከአካባቢው ሸሸን። ሦስተኛው ቦምብ የጎረቤቶቻችን ቤት ላይ አረፈ። አራት እና አምስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ተገደሉ። ሌሎቹ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።" ብለዋል።

    ፓኪስታን፤ አፍጋኒስታን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን የሚፈፅሙ ቡድኖችን ታስጠልላለች የሚል ክስ ለረጅም ጊዜ ስታሰማ ቆይታለች። የታሊባን መንግሥት ግን ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

  11. ካሊፎርኒያ በ32 የአሜሪካ ግዛቶች አሁንም ሕጋዊ የሆነውን ያለ እድሜ ጋብቻ አገደች

    ቢርትኒ ቢ ታዳጊ ሳለች ነበር የተዳረችው
    የምስሉ መግለጫ, ቢርትኒ ቢ ታዳጊ ሳለች ነበር የተዳረችው

    የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም በግዛታቸው ተግባራዊ እየሆነ ያለውን ያለ እድሜ ጋብቻ የሚከለክል ሕግ ፈረሙ።

    ሕጉ እአአ ከጥር 1 2027 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን ማንኛውም ሰው ትዳር ለመመስረት እድሜው 18 መሙላት አለበት ተብሏል።

    ኒውሶም ሕጉን ሕጻናት እና ታዳጊዎችን ለመከላከል “ለረዥም ጊዜ የዘገየ እርምጃ” ሲኡ ገልጸውታል።

    አስተዳዳሪው ሕጉን ፈርመው ሲያጸድቁ ከአጠገባቸው በ16 ዓመቷ ለ50 ዓመት የሆሊውድ ተዋናይ የተዳረችው ኮርትኒ ስቶደን ነበረች።

    ስቶደን ያለ እድሜ ጋብቻ በካሊፎርኒያ እንዲቀር ስትወተውት ነበር ተብሏል። አዲሱን ሕግ “ድል ነው” ያለችው ስቶደን፣ ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ሴቶች የሚደርስባቸውን ስቃይ ብቻቸውን መሸከም የለባቸውም ስትል ተናግራለች።

    ስቶደን “በሁሉም 50 ግዛቶች ሕጻናት ከካለ እድሜ ጋብቻ መጠበቅ እስኪቻል ድረስ ትግሌን እቀጥላለሁ” ብላለች።

    ከአስር ዓመታት በፊት ይህ አሰራር በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች ይፈቀድ የነበረ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ግዛቶች ሕጎቻቸውን እየቀየሩ ይነው።

    ካሊፎርኒያ እአአ ከ2018 ወዲህ ያለ እድሜ ጋብቻን የከለከለች 18ኛዋ ግዛት ሆናለች።

    በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ለጋብቻ የተቀመጠ የዕድሜ ገደብ አልነበረም፤ ይህም ወላጆች ፈቃዳቸውን ከሰጡ እና በጋብቻው መስማማታቸውን ህጻናት እንዲያገቡ ያስችል ነበር።

  12. የመንግሥታቱ ድርጅት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በጦርነት የተፈናቀሉትን ጨምሮ ሲቪሎችን ለአደጋ ያጋለጠ ነው አለ

    በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)

    በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የቀደመው ጦርነት ተፈናቃዮችን ጨምሮ ሲቪሎችን ለአደጋ እያጋለጠና ተጨማሪ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው አለ።

    ኦቻ ትናንት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የእርዳታ ሠራተኞችን እና ንብረቶችን ደኅንነት እንዲጠብቁና ለተጋላጭ ወገኖች ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት የሕይወት አድን እርዳታ እንዲደርስ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

    የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በኃይል የያዟቸውን ሁሉንም የረድኤት ድርጅቶች ተሽከርካሪዎች በአስቸኳይ እንዲመልሱም ኦቻ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

    የድርጅቱ አስተባባሪ ኦዞኒያ ኦጂሎ (ዶ/ር) በመግለጫቸው በተለይም በቀደመው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ለተደራራቢ የደህንነት ስጋት መጋለጣቸው እና አዳዲስ መፈናቀሎች መከሰታቸው በሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ብለዋል።

    ​ኃላፊው አክለውም የሰብዓዊ እርዳታ ማኅበረሰብ በተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ መስጠቱን ቢቀጥልም፣ በተለይ በቅርቡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ውጥረት መባባስ ጋር ተያይዞ በእርዳታ ሠራተኞች፣ በንብረቶች፣ በቢሮዎች እንዲሁም በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሳሰቧቸው ገልጸዋል። ​

    ኦቻ በመግለጫው በታጣቂ ቡድኖች ቢያንስ 10 የሰብዓዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን አስታውቆ እስካሁን የተመለሱት ሁለት ብቻ ናቸው ብለዋል። ​

    ​አስተባባሪው የእርዳታ ሠራተኞችና ንብረቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ መሰረት ከጥቃት የተጠበቁ መሆናቸውንና መቼም ቢሆን ዒላማ መደረግ እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

    ኃላፊው አክለውም ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርሆዎችን እንዲያከብሩ፣ የእርዳታ ስራዎችን ከማደናቀፍ እንዲቆጠቡ እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ያለምንም እንቅፋት እርዳታ እንዲደርስ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል።

  13. ሩቢዮ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ለውጥ አለማምጣቱን ተከትሎ የልዑካን ቡድኑ ኒው ዮርክን ለቅቆ እንዲወጣ አዘዙ

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የኢራን ልዑካን ቡድን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ከአሜሪካ እንዲወጣ ማዘዛቸውን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እና የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሲቢኤስ ኒውስ ገለጹ።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሩቢዮ የልዑካን ቡድኑ እንዲወጣ ያዘዙት በሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት መካከል ከተደረጉ ቴክኒካዊ ውይይቶች በኋላ ሰኞ ዕለት መሆኑን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የሚመሩት ልዑክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመካፈል ባለፈው ሳምንት ወደ ኒውዮርክ የሄደ ሲሆን፣ የሆርሙዝ ባህር ወሽመጥን ዳግም ለመክፈት ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

    አራግቺ ከዚህ ቀደም ለሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጹት ከአሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ለመውጣት አቅደው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግግር ካደረጉ በኋላ በሚቀጥለው ቀን ከኒው ዮርክ ቢወጡም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ግን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ስለመክፈት እና ግጭቱን በዘላቂነት በማስቆም ዙሪያ በሚደረጉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ በዚያው ቆይተው ነበር።

    አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የተመደቡትንና በግዛቷ ውስጥ የሚገኙትን የኢራን ዲፕሎማቶች በሙሉ ከአገር እንዲወጡ አላደረገችም።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮን ትዕዛዝ ተከትሎ ሰኞ ዕለት ምሽት አራግቺ እና ልዑካን ቡድናቸው ኒው ዮርክን “ወዲያውኑ” ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።

    ኢፒ በበኩሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ፣ የልዑካን ቡድኑ “ከተፈቀደለት ጊዜ በላይ ቆይቷል” እንዲሁም “የመንግሥታቱ ድርጀት ጉባዔ አብቅቷል፤ ስለዚህ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው” መባሉን ዘግቧል።

    የኢራን የልዑካን ቡድን ማክሰኞ ዕለት ከኒው ዮርክ ወደ ዶሃ ጉዞውን ጀምሯል።

    እንደዘገባው ከሆነ፣ ዋይት ሐውስ ሰኞ ጠዋት ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ የተወሰነ መሻሻል ይኖራል ብሎ ጠብቃ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ከሰዓት በኋላ ድርድሩ ለውጥ አለመሳየቱን ግልጽ ሆኗል።

    የኳታር አደራዳሪዎች ከሁለቱም አገራት ተወካዮች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ሊደረስበት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በተናጠል እየተወያዩ ናቸው።

    እስራኤል እና አሜሪካ በጋራ በመሆን የካቲት 28 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት የከፈቱ ሲሆን በምላሹም ኢራን ወደ ባህረ ሰላጤው አገራት ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ የሚጓጓዝበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ተስተውሏል።

  14. ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በአዲስ አበባና አካባቢው ላልተወሰነ ጊዜ ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደማይሰጥ አስታወቀ

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት በአዲስ አበባ እና አካባቢው ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደማይሰጥ አስታወቀ።

    ዛሬ መስከረም 20/2019 ዓ. ም. በማኅበራዊ ድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ የተሰጠውን ማሳሰቢያ በመጣስ “የሚነሱ እንዲሁም በየትኛውም አካባቢ እና ከፍታ የሚበሩ ድሮኖችን በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የአብራሪዎቹን ትክክለኛ መገኛ ቦታ በመለየት እና በቁጥጥር ሥር በማዋል ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብሏል።

    “እንደ ወትሮው ሁሉ በአዲስ አበባ እና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ ድሮኖችን እና ሌሎች ተመሳሳይ በራሪ አካላትን የሚቆጣጠር የተቀናጀ የፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል” ሲልም አክሏል።

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ማሳሰቢያውን የሰጠው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ባገረሸበት ወቅት ነው።

    የፌደራል ሠራዊት እና የትግራይ ኃይሎች ከባለፈው ሳምንት አንስቶ ውጊያ እያካሄዱ ይገኛሉ።

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ባወጣው መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም በሥራ ምክንያት ድሮኖች መጠቀም የሚፈልጉ አካላት “የበረራውን ዓላማ፣ የሚበርበትን ቦታ፣ የድሮኑን ዓይነት እና የሞዴል ቁጥር በመጥቀስ” ፈቃድ ጠይቀው ይሰጣቸው እንደነበር ጠቅሷል።

    አያይዞም “የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ላልተወሰነ ጊዜ ፍቃድ መስጠቱን እና የበረራ ክልከላውን ተግባራዊ ማድረጉን” አብራርቷል።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የመጡ ድሮኖች እና “መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች” የሚፈጥሯቸውን የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ “የረቀቁ ቴክኖሎጂዎች መታጠቁን” በመግለጫው አመልክቷል።

    አክሎም ማሳሰቢውያውን “ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት እንዳለው” አትቷል።

  15. ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሠረተ ድንጋይ በማኖር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል

    በሰሜን ኬንያ የወደብ ከተማ ላሙ ለሚገነባው የነዳጅ ማጣሪያ ዛሬ ረቡዕ መሠረተ ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።

    የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የሆኑት ናይጄርያዊው ቢልየነር አሊኮ ዳንጎቴ የሚያስገነቡት የነዳጅ ማጣሪያ 16 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ መሠረተ ድንጋይ በማኖር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

    የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅ በቀን 700,000 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማጣራት ይችላል። በዚህም የፋብሪካው የኢንዱስትሪ አቅም በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚው ይሆናል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ለላሙ ነዳጅ ማጣሪያ መሠረተ ድንጋይ መጣሉ “የአፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም በማሳደግ አንድ እርምጃ ነው” ብለዋል።

    “በምሥራቅ አፍሪካ ዕድል የሚፈጥር፣ ለትልቅ የምጣኔ ሃብት እና ኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት መሠረት የሚጥል” እንደሆነም ገልጸዋል።

    ባለ ሃብቶች አፍሪካ ላይ እምነት ጥለው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የአፍሪካ የወደፊት ዓለም በጋራ የምንገነባው ነው” ብለዋል።

    የፋብሪካው የመሠረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊት የተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ፋብሪካው ለሚገነባበት መሬት ተጨማሪ ካሳ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

    ዳንጎቴ ግን ተቃውሞውን አጣጥለው የፋብሪካው ግንባታ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እንደሚከናወን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የፋብሪካው ግንባታ በአውሮፓውያኑ 2030 እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ የኡጋንዳ፣ ቶጎ እና ቤኒን መሪዎች ተገኝተዋል።

    ዳንጎቴ ለቀጣናው መንግሥታት በአጠቃላይ በፋብሪካው የ30% ድርሻን ይፋ ማድረጋቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የፋብሪካው ግንባታ ሲጀመር ዳንጎቴ ባደረጉት ንግግር “አፍሪካውያን አፍሪካን ለመገንባት ተሰባስበዋል። ዛሬ እየጀመርን ያለነው ነዳጅ ማጣሪያ ብቻ አይደለም፤ አፍሪካ ብሩህ ተስፋ እንዲኖራት የኢንዱስትሪ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ እየከፈትን ነው” ብለዋል።

    በናይጄርያ ያላቸውን የነዳጅ ማጣሪያ ‘ሌኪ’ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ “በላሙም እንደሚደገም” ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ
    የምስሉ መግለጫ, የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ መሠረተ ድንጋይ በማኖር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል
    አሊኮ ዳንጎቴ
    የምስሉ መግለጫ, የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የሆኑት ናይጄርያዊው ቢልየነር አሊኮ ዳንጎቴ
  16. ወደ እስራኤል እየተጓዘ በነበረው አውሮፕላን ላይ ፓይለቱን በስለት የወጋው አብራሪ መታሰሩ ተገለጸ

    ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን

    ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ በነበረ አውሮፕላን ላይ ፓይለቶች በመጣላታቸው በረራው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲለወጥ ተደርጓል።

    ዋና አብራሪው እና ምክትል አብራሪው ተጣልተው ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ተገልጿል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “የስለት ጥቃት የፈጸመው ፓይለት በቁጥጥር ሥር ውሎ በሳዑዲ ባለሥልጣናት ጥያቄ እየቀረበለት ነው” ብለዋል።

    አውሮፕላኑ ወደ እስራኤል ሲቃረብ አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን ፓይለት በስለት እንደወጋው እና አውሮፕላኑን ለመከስከስ እንደሞከረ ተገልጿል።

    ከዱባይ የተነሳው የፍላይዱባይ አውሮፕላን በረራውን በጀመረ በሁለት ሰዓታት ውስጥ የድንገተኛ ጊዜ ምልክት ማሳየቱን በረራዎችን የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 ድረ ገጽ ጠቁሟል።

    ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አውሮፕላን ሲጠለፍ የሚሰጠውን ምልክት አውሮፕላኑ ማሳየት ጀምሯል።

    ዋና አብራሪው እና ምክትሉ “መጋጨታቸውን” የእስራኤል መከላከያን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    በኤፍዜድ1073 በረራ ላይ 150 ተሳፋሪዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ እስራኤላውያን ናቸው።

    ሁሉም ተሳፋሪዎች ደኅና እንደሆኑ እና አውሮፕላኑም በታቡክ አየር ማረፊያ እንደደረሰ ተገልጿል።

    ልጇ ሚርያም በረራው ላይ እንደነበረች የተናገረችው ያስሚን አቡካሲስ፣ ስለት የያዘ ግለሰብ ከፓይለቶቹ አንዱ መሬት ላይ እንዲወርድ እንዳስገደደው ገልጻለች። አውሮፕላኑ ውስጥ ደም ይታይ እንደነበርም ተናግራለች።

    ጀሩሳሌም ፖስት ያነጋገረው ተጓዥ እንዳለው አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን በስለት ወግቶታል። አውሮፕላኑ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ተሳፋሪዎች ጥቃት አድራሹን ከጀርባው እንዳነቁትም ተናግረዋል።

    አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሁለት ፓይለቶች አውሮፕላኑን በማሳረፍ እንደተባበሩ ተገልጿል።

    ሁለቱም ፓይለቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

  17. “ለቀናት የጥይት እና ከባድ መሣሪያ ድምጽ ይሰማናል”- ከላሊበላ መውጣት ያልቻሉት ቱሪስቶች

    የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊ

    የአውሮፕላን በረራ በመቋረጡ ምክንያት ከላሊበላ ለመውጣት ያልቻሉ ቱሪስቶች 33 እንደሚደርሱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቱሪስቶች ተናገሩ።

    በታሪካዊቷ ከተማ ዙሪያ ግጭት እየተባባሰ በመሄዱ ለቀናት የጥይት እና ከባድ መሣሪያ ድምጽ እየሰሙ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ጎብኚዎቹ በረራ እስከሚጀመር ድረስ በጭንቀት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ኒውስደይ አስረድተዋል።

    እንግሊዛዊ ቱሪስት ትናንት ማክሰኞ እንደተናገረው 33 ቱሪስቶች ከላሊበላ መውጣት አልቻሉም።

    14 እስራኤላውያን ቱሪስቶች በወታደራዊ ሄሊኮፕተር፣ ሌሎች አምስት ቱሪስቶች እና አንድ የእርዳታ ሠራተኛ ደግሞ በተራድኦ ድርጅት ተሽከርካሪ ከከተማዋ ወጥተዋል።

    ሁለት እንግሊዛውያንን ጨምሮ አሜሪካውያን፣ እስራኤላውያን፣ ደቡብ ኮሪያውያን፣ ደቡብ አፍሪካውያን፣ ሜክሲኳውያን እና የሌሎችም አገራት ቱሪስቶች አሁንም በከተማዋ ይገኛሉ።

    በላሊበላ ዙርያ ውጊያ ቢኖርም ከተማዋ ሰላም መሆኗን እንግሊዛውያኑ ቱሪስቶች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    ከአስጎብኚዎች፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከአየር መንገድ፣ ከኤምባሲዎች እና ከቀይ መስቀል መረጃ እንደሚጠባበቁም ተናግረዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገረው እንግሊዛዊ ቱሪስት “ውጊያ ይሰማናል፤ ሙሉ ሳምንቱን ጥይት እና ከባድ መሣሪያ ሲተኮስ እንሰማለን” ሲል ገልጿል።

    ከትናንት በስትያ በነበሩት 48 ሰዓታት ውስጥ ውጊያው ጋብ በማለቱ በረራ ሊጀመር ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም አክሏል።

    መስከረም 21/2019 ዓ. ም. በረራ ሊጀመር ይችላል የሚል መረጃ ቢደርሳቸውም “እርግጠኛ እንዳልሆነ” ጎብኚዎቹ ገልጸዋል።

    ባለፈው ሳምንት በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ አቋርጧል።

  18. ዓለሚቱ ኡሞድ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

    ዓለሚቱ ኡሞድ

    የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 20/ 2019 ዓ. ም. 7ኛ የሥራ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ 1ኛ መደበኛ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን፤ ዓለሚቱ ኡሞድ ​በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል።

    የክልሉ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ዓለሚቱ፤ ነሐሴ 2016 ዓ. ም. ላይ ኡመድ ኡጁሉን ተክተው ርዕሰ መስተዳደር መሆናቸው ይታወሳል።

    ከዚያ ቀደም የክልሉን ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮም በኃላፊነት መርተዋል።

  19. አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

    ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

    የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደር መንግሥት ምሥረታ እና 4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባዔውን ዛሬ መስከረም 20፣ 2019 ዓ. ም. ያደረገ ሲሆን፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው በድጋሚ ተሹመዋል።

    የደሴ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የፕላን ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ተሹመዋል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከንቲባዋ “በቀጣዩ ምዕራፍ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል” ብለዋል።

    ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር “የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ የከተማውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል” ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  20. ኢራን በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል የአሜሪካን ምላሽ መቀበሏን ገለጸች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ያስችላል በሚል በኳታር በኩል ላቀረቡት ዕቅድ የአሜሪካን ምላሽ መቀበላቸውን የመንግሥት ቃል አቀባይ ፋጢመህ ሞሃጄራኒ ረቡዕ ዕለት መግለጻቸውን የመንግሥት የዜና አገልግሎት ኢሪብ ዘገበ።

    ሞሃጄራኒ የዋሽንግተንን ምላሽ ይዘት ወዲያውኑ ይፋ ያላደረጉ ሲሆን የቴህራን ቀጣይ እርምጃ ምን እንደሚሆንም አልገለጹም።

    አራግቺ ረቡዕ ዕለት በቴህራን በአሜሪካ ምላሽ ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

    ኢራን ባለፈው ሳምንት በሰባት ቀናት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት ያስችላል ያለችውን ዕቅድ አቅርባ ነበር። በዚህም መሰረት አስፈላጊዎቹ ሁኔታዎች ከተሟሉ የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ እንደገና ሊከፈት እና መርከቦች በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አራግቺ ገልጸው ነበር።

    ሆኖም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዕቅዱን ውድቅ በማድረጋቸው፣ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ኳታር ተጨማሪ ጥረት እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።

    በሌላ በኩል፣ የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቴህራን የኢዝላማባዱን የመግባቢያ ስምምነት ስኬታማ ለማድረግ የሚቻላትን ሁሉ ጥረት እያደረገች መሆኑን ኢስና የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፕሬዚዳንቱ ከድርድሩ ስለተገኙት ጥቅሞች እና ውጤቶች ማብራራት እንደ እጅ መስጠት ወይም ለኢራን ተቃዋሚዎች መገዛት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ ይልቁንም እንደ ግልጽነት መገለጫ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን በተጨማሪም ኢራን በኢዝላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ በተካተተ በማንኛውም ድንጋጌ ላይ ከመሠረታዊ መርሆቿ አለማፈግፈጓን ገልጸዋል።

    ይህንን ስምምነት በኢራን ታሪክ ውስጥ “የኩራት ምንጭ” እንዲሁም “ወሳኝ እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰነድ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ይህ የተከሰተው የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት ኢራን ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የኳታር አደራዳሪዎች ለዋሽንግተን እንደሚያቀርቡ አራግቺ ሰኞ ዕለት ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ከአደራዳሪዎቹ ጋር ከተደረጉት ውይይቶች በኋላ የአሜሪካ ምላሽ ለኢራን እንደሚደርስ እንደሚጠብቁም ገልጸው ነበር።

    ኢራን፤ የአሜሪካን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማስቆም፣ የታገዱ የኢራን ንብረቶችን መልቀቅ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመርከብ መተላለፊያ መስመር ላይ ስምምነት መድረስ የሚሉ ነጥቦችን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች።

    ቴህራን እነዚህን አቋሞቿን ለዋሽንግተን ያቀረበችው ባለፈው ሳምንት ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረገ የሁለት ሰዓት ውይይት ወቅት በኳታር በኩል ነው።