አሜሪካ ስደተኞችን ወደ አፍሪካ አገራት መላኳ ሕገወጥ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለጸ

የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉሙሩክ ፖሊስ ከአንድ ነጭ ግለሰብ ጋር ተፋጥጦ ይታያል
የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ወደ ትውልድ አገራቸው መላክ የማይችሉ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደ ሌሎች አገራት እየላከች ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሂዩማን ራይትስ ዎች አሜሪካ ስደተኞችን ዜግነት ወደሌላቸው የአፍሪካ አገራት መላኳ ሕገ ወጥ መሆኑን ገለጾ፣ እርምጃው ሌሎች ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዳይሰደዱ ለማድረግ ሲባል የሰዎችን መከራ መጠቀም ነው አለ።

"ብዙዎቹ" በእዚያ የሚገጥማቸውን ችግር ከመጋፈጥ ይልቅ ወደ አገራቸው መሄድን ይመርጣሉ ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ ላይ አስታውቋል።

ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2025 ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ ከ500 በላይ ስደተኞች ዜጋ ወዳልሆኑባቸው የአፍሪካ አገራት መላካቸውን የአሜሪካ መንግሥት መረጃን በመጠቀም የመብት ተሟጋች ቡድኑ አስታውቋል።

የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት፣ ስደተኞችን ዜጋ ወዳልሆኑበት ሦስተኛ አገራት መላክ የሕዝብ ደኅንነትን ለመጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው ብሏል።

አክሎም አደገኛ ወንጀለኛ የውጭ አገር ዜጎችን ከመንገዶቻችን ላይ ያስወግዳል ሲል ተናግሯል።

ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2024 ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት የሕገወጥ ስደተኞች ፍልሰትን መከላከል ቀዳሚ አጀንዳቸው እንደሚሆን ተናግረው ነበር።

ኢስዋቲኒ 32 ስደተኞችን ከአሜሪካ መቀበሏን እና ሦስቱ ግን "በፈቃደኝነት" ወደ ትውልድ አገራቸው የመን፣ ቤሊዝ እና ላኦስ መሄዳቸውን አስታውቃለች።

እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ከሆነ አንዳንድ ስደተኞቹን የተቀበሉ አገራት "ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስረዋቸዋል" ወይንም "እስር እና ስቃይ ወደሚጠብቃቸው" ወደ ትውልድ አገራቸው ልከዋቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመብት ተሟጋች ቡድኑ ወደ ኢስዋቲኒ፣ ጋና እና ደቡብ ሱዳን የተላኩ ስደተኞች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታስረዋል እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ እንግልት ደርሶባቸዋል ብሏል።

በካሜሮን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋና ደግሞ ስደተኞቹ "የመኖር ነጻነታቸውን ላለመጋፋት የተቀመጠውን መርህ በመጣስ" ወደ ትውልድ አገራቸው ተልከዋል ብሏል።

ቡድኑ አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሴኔት ችሎት የተናገሩትን ጠቅሶ የአስተዳደሩ ዋና ግብ "ሰዎች የሆነ ስፍራ እንደሚጣሉ ሊያስፈራራ ይችላል" በማለት "ዋናው ነገር ሰዎችን ማስፈራራት ነው" ሲል በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

"ሰዎችን እግራቸው አርፎበት ወደማያውቁት አገር ማባረር፣ ስደትን ለመግታት የሰው ልጅ ስቃይ እንዲደርስበት የተነደፈው የአሜሪካ ፖሊሲ አካል ነው" ሲሉ የቡድኑ ጊዜያዊ የአሜሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሚካኤል ጋርሲያ ቦቼኔክ ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ መስሪያ ቤት ወደዚያ የሚላኩ ሕገ ወጥ የውጭ ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንደሚሆን ከመዳረሻ አገሮች የዲፕሎማሲ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል። አንድ ግለሰብ በአይሲኢ ቁጥጥር ስር ካልሆነ፣ ስለግለሰቡ ተጠያቂ አይሆንም።"

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሎረን ቢስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወደ ሦስተኛ አገራት የሚላኩት የትውልድ አገራቸው ሊወስዷቸው ፈቃደኛ ያልሆኑ ወይም ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ የሚከለክል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተላለፈላቸው ሰዎች ናቸው።

"ወደ አገሩ መሄድ ለሚፈልግ ማንኛውም ሕገወጥ የውጭ ዜጋ ነፃ የበረራ አገልግሎት እንዲሁም 3,000 ዶላር ቼክ እንሰጣለን" ብለዋል።

ከተጠቀሱት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አንዳቸውም በሪፖርቱ ላይ አስተያየት አልሰጡም።

ይሁን እንጂ ኤስዋቲኒ በቅርቡ ሦስት ስደተኞች ወደ አገራቸው መሄዳቸውን ባስታወቀችበት መግለጫ "የሦስተኛ አገር ዜጎች መብቶች፣ ክብር እና ደህንነት መከበሩን እና መጠበቁን" ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን አስታውቃለች።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ በካሜሩን፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ 24 የሦስተኛ አገር ዜጎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

አንዳንዶቹ ወደ ሦስተኛ አገር በሚወሰዱበት ወቅት በበረራ ላይ "እንግልት የተሞላበት አያያዝ" እንደገጠማቸው ለቡድኑ ገልጸዋል። ይህም ለ18 ሰዓታት ያህል በሰንሰለት መታሰር እና መዳረሻቸውን ሳያውቁ መጓዝን ያካተተ ነው።

እንዲሁም "አስፈላጊ መድሃኒቶችን እንዳያገኙ ተከልክለዋል፣ በተጨማሪም ብዙ ጊዜ በቂ ምግብ ወይም ውሃ አላገኙም" ብሏል።

የመብት ተሟጋች ቡድኑ "እነዚህን ዝውውሮች የሚያሳልጡት ግልጽ ያልሆኑ ስምምነቶች፣ አንዳንዶቹ አሁንም ሚስጥራዊ ናቸው፤ አሜሪካ የገባችውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግን የሚጥስ ፖሊሲ አካል ናቸው" ብሏል።

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፣ ቢያንስ አስራ ሁለት የሚሆኑ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን መሆናቸውን እና ይህንን ወንጀል ወደሚያደርጉ የአፍሪካ አገሮች መላካቸውን ጨምሮ አስታውቋል።