13 ባልደረቦቹን የገደለው የቀድሞ የአሜሪካ ወታደር የሞት ቅጣት በቀጥታ ሊተላለፍ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
እንደ አውሮፓውያኑ በ2009 በፎርት ሁድ ያልታጠቁ 13 የአሜሪካ ወታደሮችን በጥይት በገደለው የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አባል ላይ በጥይት ተኩስ የሚፈፀምበት የሞት ቅጣት በቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ እንደሚተላለፍ ፔንታጎን አስታወቀ።
የሞት ቅጣቱ በቀጥታ ስርጭት እንዲተላለፍ መወሰኑን የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ተናግረዋል።
አንድ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣንም ባልደረቦቹን በገደለው ኒዳል ሐሰን ላይ በተኩስ የሚፈፀመውን የሞት ቅጣት ሕዝብ በቀጥታ እንዲከታተል ይደረጋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ውሳኔው ተግባራዊ ከሆነ፣ በአንድ ምዕተ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ በይፋ የሚታይ የመጀመሪያው የሞት ቅጣት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
የሞት ፍርድ ለተፈረደባቸው እስረኞች ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት ጆን ሚልስ፣ ቅጣቱን በቀጥታ ማሰራጨት "በዚህ ዘመን ያልተለመደ" እና "በሕጋዊ አተገባበሩ አከራካሪ በሆነ መልኩ የሚፈፀም ነው" ብለዋል።
"ሰዎች ማየት እንዲችሉ፣ ሂደቱም ግልፅ እንዲሆን እናደርጋለን" ሲሉ ሄግሴት ተናግረዋል።
"ሰዎች እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ከባድ ውጤት እንዳላቸው ሊገነዘቡ ይገባል" ሲሉም አክለዋል።
ፔንታጎን ሐሰንን በሞት እንደሚቀጣ ያስታወቀው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር። ይህም በአሜሪካ ጦር ታሪክ ከ60 ዓመታት በኋላ የሚፈፀም የመጀመሪያው ወታደራዊ የሞት ቅጣት ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Bell County Sheriff's Office/Reuters
ሄግሴት ለወግ አጥባቂው የቴሌቪዥን ጣቢያ 'ሪል አሜሪካስ ቮይስ' በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ሐሰን "በወታደሮች የተኩስ ቡድን የሚፈፀም የሞት ቅጣት ይጠብቀዋል። መሆን ያለበትም ይኸው ነው" ብለዋል።
ሐሰን የመጨረሻ ጥያቄ አቅርቦ እንደሆነ ወይም ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የላከው መልዕክት ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት ሄግሴት "ይህ አያገባኝም። ታኅሣሥ 3 እናየዋለን" ሲሉ መልሰዋል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሾን ፓርኔል ሰኞ ዕለት እንዳሉት፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ምክረ-ሃሳብ ፕሬዚዳንት ትራምፕም አጽድቀውታል።
ቢቢሲ ትራምፕ ይህን በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ የሞት ቅጣት ይደግፉ እንደሆነ ዋይት ሀውስን አስተያየት ጠይቋል።
ባለፈው ዓመት በ17 አገሮች ከ2,700 በላይ የሞት ቅጣቶች የተፈፀሙ ሲሆን፣ በይፋ ሕዝብ እየተመለከተ ቅጣቱን የፈፀሙት ሁለት አገሮች ብቻ ናቸው።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2025 በኢራን 11 በአፍጋኒስታን ደግሞ 6 የሞት ቅጣቶች በይፋ ተፈፅመዋል።
በሐሰን ላይ የሚፈፀመው የሞት ቅጣት በቴክሳስ ፎርት ሁድ እአአ ታኅሣሥ 3 ተግባራዊ እንደሚሆን የአሜሪካ ጦር አስታውቋል። ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በተኩስ የሚፈፀም የመጀመሪያው ወታደራዊ የሞት ቅጣት ይሆናል።
በአሜቲካ ጦር የአእምሮ ሐኪም የሆነው የቨርጂኒያው ኒዳል ሐሰን፣በአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር ላይ ከውጊያ ውጭ የተፈፀመውን በታሪክ ከፍተኛውን ግድያ ስለመፈፀሙ በፍርድ ቤት አምኗል።



































