ኢትዮጵያ "ለተፈጸመባት ወረራ ራሷን ከመከላከል ውጪ አማራጭ እንደሌላት" ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አባላት አሳወቀች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ
የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በደብዳቤ አሳወቀች።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት በጻፉት ደብዳቤ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ደብዳቤውን የጻፈችው በትግራይ ጦርነት ዳግም ከተጀመረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ረቡዕ ዕለት መስከረም 27/2019 ዓ.ም. የኤርትራ ወታደሮች በብዛት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች መታየታቸው በስፋት ከተዘገበ በኋላ ነው።

ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ የዜና ምንጮች የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸውን በተመለከተ ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገው ቢዘግቡም፣ ኤርትራ ግን ኢትዮጵያ ልትከፍተው ለምትፈልገው ወረራ ሰበብ እየፈለገች ነው በማለት ክሱን ውድቅ አድርጋዋለች።

ቢቢሲ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጭ እንደተረዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በጻፉት ደብዳቤ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት በላከችው ደብዳቤ "ኤርትራ በተደጋጋሚ በፈጸመችው ጸብ አጫሪነት እና ድንበር ጥሶ የመግባት እርምጃ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ መደቀኑን" በመጥቀስ ትኩረት እንዲሰጠው መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።

"ኤርትራ ወራሪ፣ ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን በመጣስ ወረራ ፈጽማለች፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የወረራው ሰለባ ናት" በማለትም ከስሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በደብዳቤያቸው ኤርትራ የፀብ አጫሪነት ድርጊቷን በአሁኑ ጊዜ ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግራ "ሜካናይዝድ ክፍሎችን ጨምሮ ወታደሮቿን በጥልቀት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት አሰማርታለች። ይህም ሦስት የትግራይ ዞኖችን በማካተት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ከ30 አስከ 60 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ወደ ውስጥ ገብተዋል" ብለዋል።

ሚኒስትር ጌዲዮን የኤርትራ ድርጊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ውስጥ የሰፈሩትን መሠረታዊ መርሆዎች በግልጽ የሚጥስ ነው በማለት "ይህም ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል ሕጋዊ መብት እንድትጠቀም የሚያስገድድ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለፀጥታው ምክር ቤት የጻፉት ደብዳቤ ተፈጸመ ያሉትን ወረራ ለማሳወቅ ብቻ ሳይሆን አገራቸው ለምትወስደው የመከላከል እርምጃም ድጋፍ ጠይቀዋል።

"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያ ራሷን ከመከላከል በቀር ሌላ አማራጭ የላትም" በማለት ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ የገጠማትን ሁኔታ በመረዳት ድጋፍ እንዲደያርግላት እና ከጎኗ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ኢትዮጵያ ከኤርትራ በኩል ለረዥም ጊዜ ሲፈጸሙ ለነበሩ ትንኮሳዎች በትዕግሥት እና ራስን በመቆጠብ መቆየቷን አመልክተዋል።

ስለዚህም "ሁለቱን አገራት በእኩል ሚዛን ለማስቀመጥ የሚሞክር ማንኛውም አቋም ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደኅንነት አይጠቅምም። ኤርትራ ወራሪ ናት፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የወረራ ሰለባ ናት። ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እየጣሰች ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነና ኤርትራ ከ25 ዓመታት በፊት በድንበር ይገባኛል ሰበብ ለሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ከስምንት ዓመት በፊት ግንኙነታቸው ቢታደስም በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎተወን ካስታወቀች በኋላ ውዝግቡ የበረታ ሲሆን ወደ ግጭት ይገባሉ ተብሎ ስነገር ቆይቷል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከህወሓት ኃይሎች ጋር በአማራ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ወደ ግጭት ከገቡ በኋላ የኤርትራ ኃይሎች በግጭቶቹ ተሳታፊ ናቸው የሚል ክስ ቢቀርብም ኤርትራ ስታስተባብል ቆይታለች።

የኤርትራ ሠራዊት በብዛት ወደ ትግራይ ክለል ዘልቀው መግባታቸውን ነዋሪዎች መግለጻቸውን ተከትሎ ለወጡት ዘገባዎች ኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በሰጡት ምላሽ "ኢትዮጵያ በጎረቤቷ ላይ ጦርነት ለመክፈት የምታደርገው ጥረት አካል ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።