ስለ ሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ? የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይላሉ?

ወታደሮች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በመሪነታቸው እንዲቀጥሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰየሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው ያከናውናቸዋል ስላሏቸው ዕቅዶች አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ50 ደቂቃ በላይ ባደረጉት ንግግር የባሕር በር ተደራሽነት እና የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ጨምሮ በርካታ አገራዊ ጉዳዮችን እንዲሁም ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ከኢትዮጵያ አንፃር በመቃኘት አንስተዋል። በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን እና በሌሎችም ክልሎች ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ ግን ያሉት ነገር የለም።

የትግራይ ግጭት ዳግም ከተቀሰቀሰ ከሁለት ሳምንታት በላይ ተቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያት የፌዴራሉ መንግሥት እና አጋር ኃይሎች መቀሌ ከተማን ጨምሮ በደቡብ ትግራይ የሚገኙ ከተሞችን እና የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል።

ምንም እንኳን የአፋር ክልል እና አንድ የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ኤርትራ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ እንደሆነች እየገለጹ ቢቆዩም፣ ረቡዕ መስከረም 27/2019 ዓ.ም. ደግሞ በርካታ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው መግባታቸው ተዘግቧል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ኃያላን አገራት፣ በፌዴራሉ ኃይሎች እና በሕወሓት መራሹ የትግራይ ታጣቂ ኃይል መካከል ዳግም ግጭት መቀስቀሱ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ሁኔታ መባባሱ እንዳሳሰባቸው የሚገልፁ መግለጫዎችን አውጥተዋል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኞው ንግግራቸው "የውስጥ እና የውጭ ተላላኪ" ያሏቸው ኃይሎች "አብረው እንደተነሱ" ከመጥቀስ ባለፈ ስለግጭቶች በዝርዝር አላብራሩም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ንግግር እና በሰሜን ኢትዮጵያ በቀጠለው ጦርነት ዙሪያ እርሳቸውን ጨምሮ መንግሥታቸው ዝምታን መምረጡን በተመለከተ ቢቢሲ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተያየት ጠይቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ፓርቲዎቹ እንዴት ይገልፃሉ?

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢዜማ፣ የኢሕአፓ፣ የኢሶዴፓ እና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) አመራሮች የተለያየ አቋም አንፀባርቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኞው ንግግራቸው በርካታ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ቢያነሱም "መነሳት ያለባቸው በጣም ወሳኝ ነገሮች ግን የተነሱ አይመስለኝም" በማለት "ወቅታዊ አንገብጋቢ" ጉዳዮችን አለመዳሰሳቸውን ይተቻሉ።

"የአገር እና የሕዝብ የሰላም እና ደኅንነት ችግሮች እንዲሁም በየቦታው ያሉ ጦርነቶች ስለሚፈቱበት አግባብ" ካለማንሳታቸው በተጨማሪ ስለመፍትሔው የመንግሥታቸውን ቀጣይ አቋም "በግልፅ አላስቀመጡም" ሲሉ ወቅሰዋል።

እነዚህ ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልጉ መሆናቸውን ያነሱት ራሔል፣ የመንግሥት ምሥረታው ከተጠናቀቀ በኋላ በቀዳሚነት አንገብጋቢ ያሏቸውን ችግሮችን በተመለከተ "የመፍትሔ አቅጣጫ ሊቀመጥ እንደሚገባ" ያምናሉ።

"ሕግ ቢከበር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግጭቶች አይፈጠሩም ነበር ብዬ አምናለሁ" የሚሉት ፖለቲከኛዋ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት "ከሕግ በላይ" የዴሞክራሲ ተቋማት ደግሞ "ነጻ አለመሆናቸው" ግጭቶቹ መፍትሔ አልቦ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ያብራራሉ።

ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ከመንግሥት "አሳማኝ እና ተዓማኒ ምላሽ ቢያገኙ የትጥቅ ትግሎች ይቀረፋሉ" የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደነበረበት ጠቅሰዋል።

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ መንግሥታቸው ምሥረታ ላይ "በጫካ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወደ ሰላም መንገድ ኑ" ሲሉ ጥሪ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ዶ/ር ራሔል ግን "መንግሥት ተጨማሪ ርቀት ሔዶ በቁርጠኝነት እና በሃቀኝነት ለመነጋገር እና ለመደራደር" ያለውን "እውነተኛ" ዝግጁነት ማሳየት አለበት ይላሉ።

ከ1953 ዓ.ም. ጀምሮ የቀጠለው በትጥቅ ትግል እየተሸናነፉ የመሔዱ ጉዞ ዘላቂ መፍትሔ እንዳላመጡ በማስረዳት፣ መተማመንን በመፍጠር ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ መቀየስ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት እምነታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋና ፀሐፊ ምሥጢረሥላሴ ታምራት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር ይበልጥ በጠንካራ ቃላት ይተቻሉ።

"እንደተለመደው ብዙም ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላተኮረ ነው" ያሉት ንግግራቸው "ምናልባትም ስለዜጎች ሕይወት እምብዛም ግድ እንደማይሰጣቸው ያስመሰክሩበት ነው ብዬ ነው የማምነው" ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

ከምንም በላይ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው "የንፁሃን ሕይወት እና የአገር ሰላም" እነደሆነ የሚገልፁት ምሥጢረሥላሴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አለማንሳታቸውን ነቅፈዋል።

የጠቅላይ ሚነስትሩ ንግግር "በቀጣይ ጊዜም የዜጎች ደኅንነት በአወንታዊ መልኩ ትኩረት የማይሰጠው መሆኑን የሚያመለክት ነው" ሲሉም ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አቶ ንጋቱ ወልዴ በበኩላቸው የተለየ አቋም አላቸው። አቶ ንጋቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የዳሰሷቸውን ጉዳዮች፣ የኢትዮጵያን "ፖለቲካዊ ድባብ፣ የፀጥታ ሁኔታ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በጥልቀት የዳሰሰ" ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል።

"በጣም አስፈላጊ ጉዳዮችን ያነሳ ነው" ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ ወደ ተግባር የሚለወጥ ከሆነ "በጣም መሠረታዊ የሆኑ በተለይ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያለውን የባሕር በር ጉዳይ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና ለመፍጠር ያለመ በጣም የሚያነቃቃ ነበር" ሲሉ ገልፀዋል።

ከግጭቶች አንጻር ሲታይ ግን "ንግግሩ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ እንደመሆኑ፣ በእያንዳንዱ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለው እና ምን ሊደረግ እንደታሰበ መዳሰስ የሚጠበቅ አይመስለኝም ይላሉ።

የንግግራቸው ይዘት በአጠቃላይ በአምስት ዓመት ውስጥ መንግሥት ሊያከናውናቸው የሚገቡ ዋና ዋና ስልታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚዳስስ በመሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን እንዳላካተተ ይገልፃሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የሰላም ጥሪ መሬት ላይ ሊወርድ የሚችልበት ሂደት "ዝርዝር ፕላን እና ንግግሮችን የሚፈልግ ነው" የሚሉት የኢዜማው ምክትል መሪ፣ በዚያ ደረጃ ጥልቀት ያለው ነገር "በዚህ ንግግር ላይ ይጠበቃል ብዬም አላስብም" ብለዋል።

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ አፅብሃ ደግሞ፣ ጦርነቱን በተመለከተ በመንግሥት ዝምታ ላይ ምልከታቸውን ቢያጋሩንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ግን አስተያየት መስጠት አንደማይፈልጉ ገልፀዋል።

ለዚህም ምክንያታቸው ትግራይን ሳያካትት በተካሔደ ምርጫ በሚመሠረት መንግሥት ዙሪያ "ሀሳብና አስተያየት መስጠት አንፈልግም" የሚል ነው።

ፓርቲያቸው ለትግራይ ክልል ሕዝብ መሠረታዊ እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች መከበር የሚታገል መሆኑን የተናገሩት ብርሃነ፣ እናም "ሀሳብ ምትሰጠው ትግራይ ክልል ሕጋዊ ውክልና ኖሮት ቢሳተፍ ነበር" ብለዋል።

መድፍ

ዳግም ስለተቀሰቀሰው ግጭት መንግሥት ለምን ዝመታን መረጠ?

በትግራይ ክልል ዳግም ስለተቀሰቀሰው እና እተካሔደ ስላለው ውጊያ፣ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ለመንግሥቱ ቅርበት ያላቸው አካላት በጽሁፍ እና በንግግር አስተያየት ሰጥተዋል።

መንግሥት ለዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ አባላት በትግራይ ስላለው ሁኔታ በጽሁፍ መረጃ እየሰጠ ስለመሆኑ ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆኑ መንግሥታቸው ስለጦርነቱ እስካሁን ድረስ ለሕዝብ ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም።

ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዳግም ግጭት እንዳይቀሰቀስ የተለያዩ አካላትን በደብዳቤ ሲወተውት ቆይቷል።

መንግሥት አሁን እየተደረገ ስላለው ጦርነት በይፋ ባይገልጽም፣ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው ሰዎች "ስለጦርነቱ ሁኔታ ብዙ ነገሮችን እያሉ በመሆኑ ጦርነቱ ከዓለም ሕዝብ የተደበቀ አይደለም" ይላሉ የሳወት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ ስለመንግሥት ዝምታ ሲያስረዱ። ሆኖም ግን ዝምታው ተፅዕኖ እንዳለው ያብራራሉ።

መንግሥት ዝምታ የመረጠበት ምክንያት "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ለትግራይ ሕዝብ ድምፅ እንዳይሆን" በማለም እንደሆነ ነው ብርሃነ የሚያምኑት።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባሉ ጦርነቶች ሳቢያ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በኢትዮጵያ ግጭት ላይ የሚኖረው ትኩረት ያነሰ እንዲሆን አድርጓል ብለውም ያምናሉ።

"መንግሥት በየጊዜው የሚካሔዱ ድብደባዎችን እና ጦርነቱን በይፋ ሚገልፅ ከሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይነስም እብዛ ጫና ማድረጉ ስለማይቀር በዝምታ ጦርነቱን የማስኬድ ስልት እየተከተለ ይመስለኛል" ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከህወሓት ጋር የፖለቲካ ልዩነት የፈጠሩ የቀድሞ የትግራይ ክልል መሪዎች አሁን ከመንግሥት ጋር እየሠሩ መሆናቸው የህወሓት ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ይገልፃሉ። "ህወሓት ደግሞ ሁሉንም ነገር በኃይል ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ተቀባይነቱ መውደቁም የራሱ ጫና አለው" ይላሉ።

እናም በክልሉ ካለው ድርቅ ጋር ተዳምሮ ጦርነቱ "የትግራይን ሕዝብ ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ኃይሎችን የሳበና "ቀጣናውን ወደ ለየለት ጦርነት የሚያስገባ በመሆኑ" ዓለም ትኩረት ሰጥቶ ተዋጊ ኃይሎች ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ሊያስገድድ እንደሚገባ አንስተዋል።

"ለእኔ ዝምታው አያዋጣም" የሚሉት ደግሞ የኢሶዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ናቸው።

መንግሥት ተጠሪነቱ ለሕዝብ እንደመሆኑ "በአገሪቱ እየተካሔደ ስላለው ሁኔታ ሕዝቡን ማሳወቅ አለበት" የሚሉት ራሔል፣ ነገር ግን "ሕዝቡ በፍርሃት በመታሰሩ ለየዕለት ኑሮው ከመጨነቅ ባለፈ ስለዚህ ጉዳይ ለመጠየቅ አይደለም ለማሰብም ይቸገራል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሕዝቡ ሰብዓዊ ክብሩንም መብቱንም ትቶ በሕይወት መኖሩን ከወህኒ ቤት ውጭ ሆኖ መመላለስን እንደ ጥቅም አድርጎ የሚያይበት ደረጃ ላይ መሆኑን አስተውላለሁ" ሲሉም ስለሁኔታው አስረድተዋል።

አዲሱ መንግሥት ይህ ሁኔታ የሚኖረውን ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዘዞች በማገናዘብ መፍትሔ ሊያበጅ እንደሚገባም ይመክራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግሥታቸው ስለጦርነቱ ከመናገር መቆጠባቸውን "ዝምታ ነው ብዬ አላስብም" ያሉት ደግሞ የኢሕአፓ ዋና ፀሐፊዋ ምሥጢረሥላሴ ታምራት። ይልቁንም "የሚጠፋው የሰው ሕይወት፣ የሚወድመው የአገር ንብረት መግለጫ አይገባውም ብለው ስለሚያስቡ ነው" ብል ያምናሉ።

በሌላ በኩል የመንግሥት ባለሥልጣናት "ጦርነቱን ሊያባብሱ የሚችሉ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ይገኛሉ" ሲሉ ከሰዋል።

"ጦርነቶችን ለማባባስ እና አዳዲስ ጦርነቶችን ለመፍጠር፣ አንዱን እሳት በሌላ እሳት ለማጥፋት የሚኬድበት ርቀት ብዙ አዎንታዊ ነገሮችን እንድንጠብቅ የሚያደርገን አይደለም" ብለዋል።

የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ ንጋቱ ወልዴ ግን የተለየ ሀሳብ ነው ያላቸው። መንግሥት በአሁኑ ጦርነት ዝምታን የመረጠው ከዚህ በፊት ከነበረው የሁለት ዓመቱ ጦርነት ካገኘው ተሞክሮ በመነሳት እንደሆነ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

መንግሥት "በቀድሞው ጦርነት ወቅት የነበረውን የኮሙኒኬሽን ሁኔታ ገምግሞ ይመስለኛል አሁን ተግባር ላይ ተመሠረተ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው" ይላሉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አላማጣ ከተማ ሲገቡ የሚያሳይ ምስል

የቀድሞው የሕዝብ ግንኙነት አካሔድ፣ የተለያዩ አካላት ለጦርነቱ "አሉታዊ ግብረ-መልስ" እንዲሰጡ ያደረገ እንደነበር የሚገልጡት ንጋቱ፣ በተለይ ደግሞ ጦርነቱ በሚካሔድበት አካባቢ ካለው የትግራይ ማኅበረሰብ በኩል የነበረው "ግብረ-መልስ አዎንታዊ እንዳልነበረ" አንስተዋል።

ምናልባትም መንግሥት ከቀድሞው በተቃራኒው ዝምታን የመረጠው "ከዚያ በወሰደው ትምህርት" እንደሆነ ያምናሉ።

እናም መስከረም 13 ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እስካሁን "መንግሥት ሥራውን በተግባር ከመሥራት በዘለለ ብዙ አለማውራቱን" የሚደግፉት እርምጃ እንደሆነ አቋማቸውን ገልፀዋል።

በመሆኑም መንግሥት "ሥራውን እስከሠራ ድረስ ኮሙኒኬሽኑን [የሕዝብ ግንኙነቱን] ተግባር አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ይገልፃል ብዬ ነው ማስበው" ብለዋል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት ተገትቶ የቆየው እና በዋናነት ትግራይን ማዕከል ያደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከመስከረም 13 ጀምሮ ዳግም መቀስቀሱ፣ አሁን ካለው አሰላለፍ ጋር ተደምሮ ከቀድሞው የተለየ መዘዝ እንደሚኖረው ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።

ይሁን እንጂ እስካሁን የግጭቱ ተሳታፊዎች እና በውጥረት ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ የሚጠይቁ መግለጫዎች በተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ቢወጡም፣ ችግሩን ለመፍታት የተጀመረ ድርድር ስለመኖሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።