ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 12 አዳዲስ ሚኒስትሮችን በመሾም ካቢኔያቸውን አዋቀሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በካቢኔ አባላቱ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል "ከፍተኛ ሚኒስትራዊ ክትትል ሲደረግባቸው ነበር" አሉ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 12 ሚኒስትሮችን ሹም ሽር አድርገው በአዲስ ሚኒስትሮች ተኩ።

አዲስ የመንግሥት ምሥረታውን ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት "በመፈጸም ዕቅም" እና "በሥራ ልምድ" ብቁ ናቸው ያላቸውን 23 የካቢኔ አባላት ሹመት አጽድቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክትላቸውን ጨምሮ 23 ሚኒስትሮችን ለመሾም መመዘኛ ናቸው ያሏቸውን መስፈርቶች ከዘረዘሩ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ከሚኒስትሮች ውስጥ ዘጠኙ በነበሩበት የሚኒስትርነት መደብ ሲቀጥሉ፤ ሁለት ሚኒስትሮች ደግሞ ወደ ሌላ ተቋም ተዘዋውረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 12 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሹም ሽር በማድረግ በአዲስ ሹመት የቀየሩ ሲሆን፤ ከተፎካካሪ ፓርቲው አብን የተሾሙት በለጠ ካሳ ተነስተዋል።

በእርሳቸው ምትክ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ፍሬሕይወት ታምሩ አዲሷ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩት ሙሳ አደም የሰላም ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል።

ዐቢይ አሕመድ ሹመታቸው "የብሔር፣ ፆታ እና የሃይማኖት ስብጥርን ከግምት ውጥ ያስገባ" እንደሆነ ጠቅሰው፤ ተሿሚዎቻቸው "ከወትሮው በተለየ ባለ እዳ" መሆናቸውን አስምረዋል።

የቀድሞ ሚኒስትሮች (ከላይ ከግራ ወደ ቀኝ) መላኩ አለበል፣ አይሻ መሐመድ፣ አለሙ ስሜ፣ ጫልቱ ሳኒ፣ በለጠ ሞላ፣ ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ካሳሁን ጎፌ፣ አብረሃም በላይ፣ ሃብታሙ ተገኝ
የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ ሚኒስትሮች (ከላይ ከግራ ወደ ቀኝ) መላኩ አለበል፣ አይሻ መሐመድ፣ አለሙ ስሜ፣ ጫልቱ ሳኒ፣ በለጠ ሞላ፣ ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ካሳሁን ጎፌ፣ አብረሃም በላይ፣ ሃብታሙ ተገኝ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቧቸው የካቢኔ አባላት ላይ አስተያየት የሰጡ አንድ የምክር ቤት አባል፤ የካቢኔ አባላትን ለመሾም መመዘኛ ተብለው የቀረቡ መስፈርቶችን "አንጻራዊ" ብለዋቸዋል።

"አምስት ዓመት እዚህ ምክር ቤት ነው የነበርኩት። ሰዎች በትምህርት ደረጃቸው በተነጻጻሪነት የተሻለ ሆነው፤ የተሻለውን በተሻለ ወስደን ስንገመግም፤ ድክመት ባለበት ጉዳይ ላይ በስትራቴጂክ ዕቅድ፣ በዓመታዊ ዕቅድ ማስፈጸም ሊሆን ይችላል ድክመት አለ ብለን ስንገመግም የሚገጥመን ስኬታማውን እንጂ ለምን ድክመቱን ታነሳላችሁ የሚል ጭቅጭቆች ነበሩ።

"ድክመቱን ላለመቀበል ብቻም ሳይሆን 'አይ እኔ ከዚህ ሰፈር ስለመጣሁ ነው፤ ልታጠቁኝ ስለፈለጋችሁ ነው' በሚል የፖለቲካ ሽፋን ታኮ ይደረጋል። አንዳንድ ሰዎች በአሁኑ ሹመት ላይ ባይካተቱ" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ለዚህ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በካቢኔ አባላቱ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል "ከፍተኛ ሚኒስትራዊ ክትትል ሲደረግባቸው ነበር" በማለት ከሙስና የፀዱ መሆናቸው መረጋገጡን ጠቁመዋል።

"በኢንተለጀንስ [በደኅንነት መረጃ] የተደገፈ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያላቸው እንቅስቃሴ፤ በልጆቻቸው፣ በሚስቶቻቸው፣ በአጎቶቻቸው፤ ከሚገናኟቸው ሃብታሞች ጋር በሙሉ የመረጃ ክትትል ይደረግ ነበር። በዚህ መሠረት ብርቱ ግምገማዎች አድርገናል" ብለዋል።

"ሹም ሽሩ ዝም ብሎ አይደለም የተደረገው" በማለት አዲሱ ካቢኔያቸውን ተከላክለዋል።

ከዚህ ባለፈም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔያቸው የአገሪቱን መልክ እንዲያንፀባርቅ "የአማራ እና የኦሮሞ ኮታ እንዲቀንስ ተደርጓል" በማለት አካታችነቱንም አወድሰዋል።

ከአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ዘጠኙ ብቻ ሴት ስለመሆናቸው አስተያየት ለሰጡ የምክር ቤት አባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ በመጀመሪያ ካቢኔያቸው 50 በመቶ ሴቶችን መሾማቸው "በአሰብነው ደረጃ የተሳካ አልነበረም" ብለዋል።

"ባለፈው ጊዜ ሴት ሴት ብለን ከየቦታው ለማምጣት የሞከርነው ጉዳይ ባሰብነው ደረጃ የተሳካ አልነበረም። አሁን የሄድነው ሴት እና መሥራት የምትችል፤ መፈጸም የምትችል የሚለው ታሳቢ ተደርጓል። . . .ሴትነት ሚኒስትር ለመሆን የመጨረሻው መመዘኛ አይደለም፤ ሴቶች ካልፈጸማችሁ ትነሳላችሁ፤ በወንድ ይተካል። ዋናው ነገር መፈፀም ነው።"

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲሱ ካቢኔቸያው "መቶ በመቶ በሚፈለገው ደረጃ የተሟላ አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ ሚኒስትሮቹ "ውጤታማ ካልሆኑ እርምጃ ይወሰዳል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

420 አባላት የተገኙበት 7ተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ መደበኛ ስብሰባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የካቢኔ ሹመት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።