ኢትዮጵያ ኤርትራ ወረራ እንደፈጸመችባት አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት አስታውቃ፣ የአሥመራ ወታደሮች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰበች።
በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል ውጥረቱ በተባባሰበት ወቅት ኢትዮጵያ ኤርትራን ወደ ግዛቷ ወታደሮችን በማስገባት የከሰሰች ሲሆን፤ በአፋጣኝ ግዛቷን ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቃለች።
የኤርትራ ወታደሮች ከረቡዕ መስከረም 27/2019 ዓ. ም. ጀምሮ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን የአዲግራት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮምንኬሽን ሚኒስትር የሆኑትን እናታለም መለሰ የኤርትራ ወራደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ተናግረው፤ ሁሉም የውጭ አገር ወታደራዊ ኃይሎች የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቀው መውጣት አለባቸው ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ይህም ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ብለው በዘገቡ በአንድ ቀን ውስጥ ከመንግሥት የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።
ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በላይ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የኤርትራ ወታደሮች በአዲሱ ዓመት በጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እየተሳተፉ መሆናቸውን አሳውቀው ነበር።
ኤርትራ በበኩሏ ሠራዊቷ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቀው ገብተዋል የመባሉን ክሱ አስተባብላለች።
የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል የዓይን እማኞችን ምስክርነት "ኢትዮጵያ በጎረቤቷ ላይ ጦርነት ለመክፈት የምታደርገው ጥረት አካል ነው" ሲሉ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው መግባታቸው የተሰማው የትግራይ ክልልን ተቆጣጥረው የነበሩት እና በኤርትራ ይደገፋሉ የሚባሉት የህወሓት ኃይሎች ዋና ከተማዋን መቀለን ለቅቀው ከወጡ ከቀናት በኋላ ነው።
ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ 115 ኪሎ ሜትር እና ከኤርትራ ድንበር ደግሞ 40 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የአዲግራት ከተማ ሁለት ዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት የኤርትራ ወታደሮች በበርካታ መኪኖች ተጭነው እንዲሁም በእግራቸው ሲያልፉ ተመልክተዋል።
ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጋር የተሰለፉት "የትግራይ ሰላም ኃይሎች" አዛዥ ገብረእግዚአብሔር በየነ ለኤኤፍፒ የኤርትራ ጦር ከባድ መሣሪያዎችን ታጥቆ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን ተናግረዋል።
የትጥቅ ግጭቶችን የሚሰንደው አክሌድ የኤርትራ ወታደሮች በዛላምበሳ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውን ጠቅሶ በአዲግራት እዳጋ ሀሙስ መስመር እየተጓዙ ሳለ ጉአዳ በተባለ አካባቢ ከኢትዮጵያ መንግሥት የድሮን ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ገልጿል።
ኤርትራ "ትብብር ለኅልውና" የተባለውን አዲሱን የአማጺዎች ጥምረት ትደግፋለች ተብሎ የሚጠረጠው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነም አክሌድ ጠቁሟል።
ኤርትራ ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም የዘለቀውን የትግራይ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ደስተኛ አለመሆን የመጀመሪያው ምክንያት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ወደብ ለማግኘት የያዘችውን አቋም ኤርትራ በመቃወሟ በሁለቱ አገራት መካከል መሀል ገብ መሬት ለማበጀት ትግራይ ክልልን የግጭት ቀጠና ማድረግ መሻቷ ሁለተኛው ምክንያት ነው ይላል።
እንደ አዲስ ባገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ወደ ይፋዊ ጦርነት የሚያመራ ከሆነ ከ25 ዓመታት በፊት በሁለቱ አገራት መካከል ከተካሄደው ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት የከፋ እንደሚሆን በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
አገራት፣ ቀጣናዊ እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት አገራቱ ሉዓላዊነትን እንዲያከብሩ እና ከግጭት ተቆጥበው አለመግባባቶችን በንግግር እንዲፈቱ እየጠየቁ ነው።




































