ዓለም በኤል ኒኖ ምክንያት አደገኛ ሁኔታ እንደገጠማት የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ
የኤል ኒኖ ተጽእኖዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መታየት እየጀመሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ዓለም “ወደ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች አደገኛ ቀጣና ውስጥ ገብታለች" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሳቡ።
የዓለም የአየር ንብረት ድርጅት ስለዚህ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ባወጣው አዲስ ሪፖርት በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ኤል ኒኖ ከ70 ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ከታዩት እጅግ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል እና እስከ የካቲት 2019 ዓ.ም. ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ገልጿል።
ኤል ኒኖ በዓለም ዙሪያ የአየር ሁኔታ ለውጥ በማስከተል አንዳንድ አካባቢዎችን ወደ ድርቅ ሲገፋ ሌሎች አካባቢዎችን ደግሞ ከፍተኛ የአውሎ ነፋስ እና ጎርፍ እንዲያጋጥማቸው ያደርጋል።
የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ኤል ኒኖ በአንዳንድ ስፍራዎች የሙቀት መጠንን የበለጠ ከፍ ያደርጋል፤ ይህም በሰው ልጅ ተግባራት ምክንያት እየጨመረ ካለው ዓለም አቀፍ ሙቀት ጋር ተደምሮ ይከሰታል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ “ኤል ኒኖ እያየነው በእጅጉ እየተባባሰ ነው። ሳይንሱ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለውም፤ ምድራችን ያልተለመዱ ሁኔታዎች ውስጥ ገብታለች፣ በዚህም ውቅያኖሶች እየሞቁ ነው” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ከኤል ኒኖ ጋር የተያያዙ ሊከሰቱ የሚችሉ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን በተመለከተ የሚያወጣቸውን ትንበያዎች በተቻለ መጠን ለብዙ ማኅበረሰቦች ለማድረስ “ሰፊ የማስተባበር እንቅስቃሴ” ማካሄዱን ገልጿል።
የኤል ኒኖ ክስተት በዓለም አቀፍ የአየር ሁኔታ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እስከ ቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ድረስ ሊቀጥል ቢችልም፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የዝናብ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ ለውጦች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመደበኛው በታች የሆነ ዝናብ እና ሞቃት የአየር ሁኔታ የድርቅ እና የደን ቃጠሎ አደጋዎችን ይጨምራል።
በተጨማሪም በባሕር እና በውቅያኖሶች ውሃ ላይ ለውጥ ስለሚኖር እንደ ፓናማ ቦይ በመሳሰሉ መተላለፊያዎች ላይ በሚደረጉ የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።