የኬንያ አቪዬሽን ሠራተኞች ለሁለት ቀናት በረራዎች እንዲስተጓጎሉ ያደረገውን አድማ አቆሙ

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከሚገኘው ዋና አየር ማረፊያ እና ከሌሎች አገሪቱ ስፍራዎች የሚነሱ በረራዎች ለሁለት ቀናት እንዲስተጓጎሉ ያደረጉት የኬንያ የአቪዬሽን ሠራተኞች አድማቸውን አቆሙ።
አድማው የቆመው ሠራተኞቹን የወከለው ማኅበር የደመወዝ ጥያቄ እና ሌሎች ቅሬታዎች እንዲፈቱ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ስምምነት በመድረሱ ነው።
ማኅበሩ እና የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሠራተኞች ወዲያውኑ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚያደርግ ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ተፈራርመዋል።
እሁድ ዕለት ቀስ በቀስ በተጀመረው አድማ ምክንያት በቀጣናው ቁልፍ የትራንስፖርት ማዕከል በሆነው የናይሮቢው በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ተስተጓጉለው ታይቷል።
ሠራተኞቹ የተሻለ የሥራ ሁኔታ እንዲኖር እና ከዚህ ቀደም መግባባት የተደረበት ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ሲጠይቁ ነበር።
የሠራተኞች ማኅበሩ መሪ ሞስ ንዲዬማ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የአድማ እርምጃው እንዲቆም እንዲሁም መደበኛው የሥራ እንቅስቃሴ እንዲመለስ እና አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አባሎቻችንን እየጠየቅን ነው” ብለዋል።
“ሥራ ላይ ያሉ [ሠራተኞች] የተከማቹ በረራዎችን ማቃለል እንዲጀምሩ እየጠየቅን ነው” ሲሉም አክለዋል።
የኬንያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴቪስ ቺርቺር አድማው እንዲካሄድ ምክንያት የሆኑ ቅሬታዎች የሚፈቱበትን መንገድ በተመለከተ ከማኅበሩ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
“እዚህ መድረሳችን አሳዛኝ ነበር፣ ነገር ግን ከዚህ ወጥተናል። አሁን ቁጥሩ የለንም፤ ነገር ግን በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑ ያሳዝናል” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት በረራ የተስተጓጎለባቸው ተጓዦች በናይሮቢው ዋና አየር ማረፊያ ተሰብስበው ታይተዋል። የተወሰኑትም አዲስ ዜና ጥበቃ ምሽቱ በአየር ማረፊያው አሳልፈዋል።
ኬንያ ኤርዌይስ ለስድስት ሰዓታት የቆየ የበረራ መዘግየት እንዳጋጠመ እና ያልተነሱ በረራዎች በመጠራቀማቸው የተወሰኑት እንዲሰረዙ መደረጉን አስታውቋል።
ለመስተጓጎሉ ይቅርታ የጠየቀው አየር መንገዱ፣ ተጓዦች ያለ ቅጣት በረራቸውን መቀየር እንደሚችሉ ገልጿል።












