መቀለ፣ አክሱም እና ማይጨው ባለፉት ቀናት እና አሁን ያሉበት ሁኔታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና አጋሮቻቸው የሆኑት የትግራይ የሰላም ኃይሎች ወደ ትግራይ መዲና መቀለ መግባታቸውን ተከትሎ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ፣ አክሱም እና ማይጨው ነዋሪዎች አሁን ላይ በከተሞቹ ያለው ሁኔታ በአንጻራዊነት የተረጋጋ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሆኖም ግን ለወደፊት ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን በተመለከተ ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተጀመረ እንዲሁም የትራንስፖርት እንቅስቃሴም እንደሚስተዋል ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
መስከረም 23/2019 ዓ.ም. የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ ለቅቀው ከወጡ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች ዝርፊዎች እንደነበሩም ጠቅሰዋል።
የመቀለ ነዋሪው አቶ ቴዎድሮስ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ለሁለት ሳምንታት ያህል ኢንተርኔት ከመቋረጡ ባሻገር የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ገንዘብ መለዋወጥ እንዲሁም የመብራት ካርድ መሙላት ሳይችሉ ቆይተዋል።
"ማኅበረሰቡ ከባድ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር። የትግራይ የሰላም ኃይሎች እና መከላከያ አብረው እንደገቡ ግን ኔትወርክ ተለቅቋል። ትናንት [መስከረም 24] ብር ማስተላለፍ ተችሏል" ብለዋል።
መስከረም 25 በተያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ባጃጅ እና ታክሲዎች እንደ ወትሮው መደበኛ ሥራ መጀመራቸውን እንዳስተዋሉም አክለዋል።
"ሥራ ያልጀመሩት ትልልቅ ንግዶች፣ ፋርማሲዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ መደብሮች፣ ሱፐርማርኬቶች ናቸው" ብለዋል።
ትልልቅ መደብሮች እና የንግድ ተቋማት "ዝርፊያ ሲፈጸምባቸው" እንደነበር የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ በስጋት ምክንያት እንዳልተከፈቱ ተናገረዋል።
መከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማው ከገባ በኋላ ግን ዝርፊያ አለመኖሩን ገልጸዋል።
"መጠጥ ቤትም ሰው እንደፈለገው ይዝናናል። በደኅንነት በኩል መቀለ ላይ አሁን ምንም ችግር የለም፤ እንደነበረው ሰላማዊ ሕይወት ነው ያለው።"
የመንግሥት ደጋፊ የሆኑት የሰላም ኃይሎች ታጣቂዎች መስከረም 22 መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸው ያሳወቁት መስከረም 13/2019 ዓ. ም. እንደነበር ይታወሳል።
የትግራይ የሰላም ኃይሎች አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ኃይላቸው ወደ መቀለ ከመግባቱ በፊት "በቅርቡ ወደ ትግራይ መሃል እንገባለን" በማለት ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች ሰላምን በማረጋገጥ እና የሰዎችን ንብረት በመጠበቅ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ነዋሪ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሮቹ ወደ ከተማዋ ከመግባታቸው በፊት "የተለያየ ወንጀል ፈጽመው የነበሩ ሰዎች ተፈትተው አይቻቸዋለሁ፤ ሲፈቱ ያገኙትን ነው መስረቅ የጀመሩት" በማለት ዘረፋው ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የግል ንግድ ተቋማት ላይም ዝርፊያ ሲፈጸም ነበር ብለዋል።
የህወሓት ኃይሎች ከመቀለ መውጣታቸውን ተከትሎ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ያለምንም የፀጥታ ኃይል ጥበቃ መቅረታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ነዋሪው እንዳሉትም በርዕሰ መስተዳድሩ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ዝርፊያዎች ሲፈጸሙ ነበር።
"አርብ [መስከረም 22] ወደ ቅዳሜ በነበረው ሌሊት ብዙ ቦታዎች ሲዘረፉ ነበር። ከቅዳሜ [መስከረም 23] በኋላ ግን እነሱ [መከላከያ እና የትግራይ የሰላም ኃይሎች] መቆጣጠር ጀምረዋል" ብለዋል።
አብዛኞቹ ንግዶች የተዘጉት "ከፍርሃት እና ስጋት የተነሳ" እንደሆነም አክለዋል።
ከማረሚያ ቤት የወጡ እስረኞች "መሣሪያ እና ጎራዴ" ይዘው እንደነበር የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ "ራስን ለመከላከል መሞከር ራስን አሳልፎ መስጠት ነው" በማለት ማኅበበሱ ራሱን መከላከል እንዳልቻለ ገልጸዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ በነበረበት ወቅት "የህወሓት አመራሮች መቼ፣ እንዴት፣ ወዴት እንደሄዱ የሚያውቅ ሰው አልነበረም። ሁሉም ነገር የሆነው ድንገት ነው" ሲሉም ሁኔታውን ገልጸዋል።
"ኔትወርኩን ዘግተው ስለሄዱ በማኅበራዊ ሚዲያ ምን እየሆነ እንደነበር ማወቅ አይቻልም ነበር። ሙሉ በሙሉ ዝግ ነበር። ምንም መረጃ አንሰማም ነበር። በጣም አስቸጋሪ ነበር።"

"የትግራይ እናት እምባዋን እየረጨች ባለችበት ሰዓት ተመልሶ ወደዚህ መግባት በጣም አስቸጋሪ ነበር"
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአክሱም ነዋሪ በከተማዋ የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ሰላም ኃይሎች ወታደሮችም እንደማይታዩ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የማይጨው ነዋሪ በከተማዋ የወታደሮች እንቅስቃሴ ባይኖርም ሁኔታዎች "ሰላማዊ ይመስላሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
ጦርነቱ በተጀመረበት ሳምንት በከባድ መሣሪያ "ወደ 11 ሰዎች ተጎድተው" እንደነበር የገለጹት ነዋረው "ከዚያ ወዲህ ግን ምንም አልተፈጠረም" ብለዋል።
ሐሙስ መስከረም 21 የመከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ እንደገባ ተናግረዋል።
"ከዚያ በኋላ ሕዝቡ በሰላም እየተንቀሳቀሰ ነው። አስተዳዳሪዎች እና ሰላም አስከባሪ ፖሊሶች እንቅስቃሴ ጀምረዋል። እስከ ሐሙስ ጠዋት ድረስ ውጥረቱ ከባድ ነበር፤ አስጨናቂ ነበር።"
በማይጨው ኔትወርክ እና መብራት ጠፍቶ እንደነበር እና ገበያም ተቀዛዝቆ መቆየቱን አስረድተዋል።
"ከሐሙስ በኋላ ነገሮች ተረጋግረተዋል። መብራቅ ቅዳሜ [መስከረም 23] ማታ መጥቷል። ኔትወርክ በተወሰነ መጠን ቅዳሜ ከዚያም ሰኞ ሙሉ በሙሉ ተመልሷል" ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት ያለ ፀጥታ ስጋት ግብይት ሲከናወን እንደነበር እና ነዋሪዎች ከገጠር ወደ ከተማ መጓጓዝ መቻላቸውንም አክለዋል።
እሑድ መስከረም 24 ሞባይል ባንኪንግ እንደተጀመረ እና ባንኮችም እየተከፈቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሐሙስ መከላከያ ሠራዊት ከመግባቱ በፊት እስረኞች ከማረሚያ ቤት "ለመውጣት ሞክረው ነበር" ያሉት ነዋሪው "ፖሊሶች ስለነበሩ አልወጡም፤ መከላከያም ቶሎ ገብቷል፤ ማይጨው ላይ ይፋ የወጣ ዘረፋ የለም" ብለዋል።
አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይሎች በከተማዋ ባይኖሩም የፀጥታ ማስከበር ሥራ የሚያከናውኑ ኃይሎች መኖራቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ህወሓትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት መመሥረታቸውን ባስታወቁ ማግሥት ዳግም የተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሊባባስ ይችላል የሚለው ስጋት ነዋሪዎችን አስጨንቋል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎችም አካላት ውጥረቱ እንዲረግብ ማሳሰባቸውን ቀጥለዋል።
ጦርነቱ የኢትዮጵያ ባላሥልጣናት ታጣቂዎችን በመደገፍ በሚከሷቸው ኤርትራ እና ግብፅ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አበላሽቶታል።
የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች መቋረጥ ጦርነቱ "ቀጣናዊ መልክ" ሊይዝ ይችላል የሚል ስጋትም አጭሯል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ነዋሪ እንደተናገሩት ባለፉት ሳምንታት በማኅበረሰቡ ዘንድ "አሁንስ ምን ሊውጠን ነው?" የሚል ከፍተኛ ፍርሃት ነበር ብለዋል።
"እናት አባት ልጆቻቸው ትናንት ተሰውተው፣ ከባለፈው ቁስላችን ገና ሳናገገም፣ አሁን ደግሞ ወደ ተመሳሳይ፣ ወደ ከፋ ጦርነት ነው የምንገባው?" ሲሉም ፍርሃታቸውን ገልጸዋል።
"ገና [ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት የተገደሉት] ደማቸው ሳይደርቅ፣ አሁን የሚጠይቃት ጧሪ የሌላት የትግራይ እናት እምባዋን እየረጨች ባለችበት ሰዓት ተመልሶ ወደዚህ መግባት በጣም አስቸጋሪ ነበር።"
ወጣቶች ጦርነት በመሸሽ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች መሄዳቸውንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ለወደፊት ያላቸው ስጋት እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ ያለውን መረጋጋት በማንሳት "ያንን ፍራቻ እና ስጋት እግዚአብሔር ቀለል አድርጎት መቀለ ላይ የከፋ ጦርነት እና ግጭት አልተካሄደም" ብለዋል።
"ማኅበረሰቡ ሰላም ቢሆን ይመርጣል። ከጦርነት፣ ከውጊያ የሚገኝ ጥቅም የለም። የትግራይ ሕዝብ በተግባር ነው ያየው። አሁን ባለበት ሁኔታ በሰላም እንዲያልቅ ነው የምንፈልገው" ብለዋል።
ጦርነቱ ሊስፋፋ ይችላል የሚለው ስጋት
የመቀለ ነዋሪው አያይዘውም የኤርትራ ሠራዊት "በዛላንበሳ እና በሽራሮ በኩል እየገባ ነው" በማሉ የበለጠ ስጋት ውስጥ እንደከተተቻው ተናግረዋል።
የኤርትራ ሠራዊት ድንበር ተሻግሮ ባለፉት ቀናት በተካሄዱ ውጊያዎች ውስጥ መሳተፉን በመግለጽ የኢትዮጵያ ምላሽ ከባድ እንደሚሆን የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ዶ/ር አብርሃም "በዚህ ጦርነት ላይ የሻዕቢያ መንግሥት፣ የሻዕቢያ ሠራዊት ተሳትፏል። ከእነ ትጥቁ፣ ከእነ መሣሪያው ግንባር ወስዶ ማለት ነው። የሞተም መሣሪያዎቹም የተማረኩ መዓት ናቸው" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል ባለሥልጣናት በክልሉ እየተዋጉ ነው ያሏቸው የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም ወታደራዊ ቁሳቁሶች መማረካቸውን ተናግረው ነበር።
የኤርትራ መንግሥት በተደጋጋሚ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ስለመሳተፉ ለሚቀርብበት ውንጀላ ሲያስተባብል ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ የሚገኘውን ኤምባሲውን በመዝጋት በአዲስ አበባ የሚገኙ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ማባረሩ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን አስታውቋል።
በሌላ በኩል ግብፅ እና ኢትዮጵያ አንዳቸው የሌላቸውን ዲፕሎማቶች ከየአገራቸው አስወጥተዋል።
ግብፅ ከሰሞኑ ባስተናገደችው ኤል አላሚን ጉባዔ ላይ የተገናኙት የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን መሪዎች ከግብፅ ጋር በመሆን የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና የግብፅ መካከል የተካረረው ውጥረት እንዲረግብ አሳስቧል።
የአውሮፓ ኅብረትም በኢትዮጵያ የተባባሰው ግጭት እና ከኤርትራ ጋር ያለው ውጥረት "ቀጣናዊ ግጭት ሊያስከትል እንደሚችል" አስጠንቅቋል።




































