ትራምፕ ኢራን ሎስ አንጀለስን እና ሳን ዲያጎን "ልታወድማቸው" ትችላለች ማለታቸው ትችት ቀሰቀሰ

ኒውሶም እና ትራምፕ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ ኢራን፣ ሎስ አንጀለስ እና ሳን ዲያጎን ከተሞችን "ልታወድም" ትችላለች በማለት የሰጡት አስተያየት ከካሊፎርኒያ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ትችት አስከተለባቸው።

ዋይት ሐውስ በበኩሉ በጠንካራ ቃላት የታጀበ የአጸፋ ምላሽ ሰጥቷል።

የካሊፎርኒያ ገዥ ጋቪን ኒውሰም ትራምፕ በኔብራስካ በተካሄደው የምርጫ ዘመቻ ላይ የሰጡትን አስተያየት "የተዛባ እና አደገኛ" ሲሉ አውግዘዋል።

የሎስ አንጀለስ ከንቲባ ካረን ባስ ደግሞ "በአሜሪካውያን ሕይወት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማበረታታት የተወሰዱ ማስፈራሪያዎች" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

እንደ ዋይት ሐውስ ምላሽ ግን ትራምፕ በየካቲት ወር ኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ባይከፍቱ ኖሮ የአሜሪካ ከተሞች አደጋ ላይ ይወድቁ ነበር ማለታቸው ነው ሲል አስተባብሏል።

ሎስ አንጀለስ እና ሳን ዲያጎ የባሕር ኃይል ወደቦችን እና የአየር ኃይል ጦር ሠፈሮችን ጨምሮ ዋና ዋና የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ይገኙባቸዋል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በኔብራስካ ግዛት ስለ ኢራን ግጭት ሲናገሩ "የዓለምን ደኅንነት ለመጠበቅ፣ የአገራችንን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚከፈል አነስተኛ ዋጋ ነው። ከተማን ሊያወድሙ ይችላሉ። ሎስ አንጀለስን እና ሳን ዲያጎን ያውድሙ ነበር" ብለዋል።

ስለ ሁለቱ የካሊፎርኒያ ግዛት ከተሞች ፕሬዝዳንቱ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የተወሰኑ ተመልካቾች ደስታቸውን ሲገልጹ ተሰምቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ መግለጫውን ከሰጡ በኋላ የግዛቱ አስተዳዳሪ ኒውሰም "ክህደት ብቻ ሳይሆን አደገኛ ጭምር ነው" በማለት የፕሬዝዳንቱን ንግግር ኮንነው፣ የካሊፎርኒያ መንግሥት የስጋት ግምገማ ማዕከል "ሌሎች አገራት ንግግሮቹን ግዛቲቱን ዒላማ ለማድረግ እንደ ግብዣ ተርጉመውት እንዳይሆን ሁኔታውን እንዲከታተል" ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።

ኤጀንሲው በግዛቱ ውስጥ የፀጥታ ስጋቶችን ለመለየት እና ለመከላከል የተቋቋመ ነው።

የሳን ዲያጎ ከንቲባ ቶድ ግሎሪያ በኤክስ ገጻቸው ላይ በሰፈሩት ጽሑፍ "ከተማዋ የጦርነቱ ሰለባ አትሆንም" በማለት ትራምፕ "ቸልተኛ ከሆነ የጦርነት ንግግራቸው" እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

ትራምፕ የካሊፎርኒያ መሪዎች ላወጧቸው መግለጫዎች እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

የዋይት ሐውስ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ስቴፈን ቼንግ በኤክስ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የትራምፕን አስተያየት በተመለከተ "የሚዲያ ግርግር" በማለት "በእውነታ ላይ የተመሠረተ አይደለም" ሲሉ ገልጸውታል።

"የአሜሪካ ከተሞች ኒውክሌር ያላት ኢራን ላይ ጥቃት ባይከፈት ኖሮ ስጋት ውስጥ ይወድቁ ነበር" ሲሉ ቼንግ ጽፈዋል። "አሜሪካ በፕሬዝዳንቱ ምክንያት የበለጠ ደኅንነቷ የተጠበቀ ሆናለች። ኢራን የኒውክሌር ኃይል፣ የባሕር ኃይል፣ የአየር ኃይል እና ገንዘብ የላትም" ሲል አክለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2028 ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ የሚችሉት የካሊፎርኒያው አስተዳዳሪ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በይፋ ሲወዛገቡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም።

ባለፈው ዓመት ትራምፕ በሎስ አንጀለስ ሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ተቃውሞ ሲገጥመው እና ወደ አመጽ ሲቀየር ብቃት የለውም በማለት በቂ ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ኒውሰም በተቃውሞ ሰልፎቹ ወቅት የፌዴራል ሕንፃዎችን ለመጠበቅ ወታደራዊ ኃይሎች ከተሰማሩ በኋላ ትራምፕን "ኃይልን አላግባብ ተጠቅመዋል" ሲሉ ከስሰዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ ኒውሰምን ባለባቸው ተፈጥሯዊ እክል (ዲስሌክሲያ) ላይ በማፌዛቸው ፕሬዝዳንቱ በጉዳዩ ላይ ከሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ትችት እንዲሰነዘርባቸው አድርጓል።