በኪየቭ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 37 ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቀሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አርብ ዕለት በኪየቭ በሚገኝ መጋዘን ላይ ሩሲያ የድሮን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ፍንዳታ በመከሰቱ 37 ሰዎች ሲገደሉ ወደ 400 የሚጠጉ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ለቅቀው እንዲወጡ ተደረገ።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ፍንዳታው በአካባቢው በሚገኙ የመኖሪያ ሕንፃዎች እና በአረጋውያን የእንክብካቤ ማዕከል ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በመጋዘኑ ውስጥ ተተኳሾች ተከማችተው እንደነበረ ለማወቅ ምርመራ ተጀምሯል።
የአካባቢው አስተዳዳሪ ቲሙር ትካቼንኮ፣ ከቆሰሉት 42 ሰዎች መካከል አራት ሕጻናት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ቅዳሜ ማለዳ ላይ በቡቻ አውራጃ በሚገኘው ሥፍራ የተጎዱ ሰዎችን የመፈለግ እና የማዳን ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ "መመሪያዎቹ ግልጽ ናቸው። ተተኳሾችን በቤቶች ውስጥ ወይም የመኖሪያ ሕንፃዎች አቅራቢያ መቀመጥ የለባቸውም። [ከምርመራ በኋላ] ተገቢ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን" ሲሉ ጽፈዋል።
ከ300 በላይ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት ማይላ መንደር መሰማራታቸውን ተናግረው በዚያም "የአረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች የእንክብካቤ ማዕከል" ከተጎዱት ሕንጻዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
“በግልጽ ቸልተኝነት በማሳየት የወንጀል ክስ ተከፍቷል” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ልጥፍ ላይ አጋርተዋል።
የዩክሬን ዋና አቃቤ ሕግ ቢሮ በመኖሪያ ሕንፃዎች አቅራቢያ "ፈንጂዎችን እና ተቀጣጣይ ቁሳቁሶችን የማስቀመጥ እና የማከማቸት ሕጋዊነት" እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
“ይህንን ውሳኔ የወሰኑ ባለሥልጣናት ድርጊት” እንደሚጣራም ጨምሮ ገልጿል።
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጦሩ በማይላ "ለኤፍፒ-1/ኤፍፒ-2 ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የሚያገለግሉ መለዋወጫዎች እና ማስተኮሻዎች" የተቀመጡበት "የተተኳሾች ማከማቻ መጋዘን" ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።





















