አሜሪካ ስለ ኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዦች መረጃ ለሚሰጣት 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቀረበች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሕይወት ያሉ እና የሞቱ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዦችን በተመለከተ መረጃ ለሚሰጡ ግለሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታወቀ።
ከኢራን ጋር ለወራት በዘለቀ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው አሜሪካ በተለይ አራት የአብዮታዊ ዘቡ አዛዦችን በተመለከተ ጥቆማ ለሚሰጡ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
በተለይ ትኩረት የተደረገባቸው የአብዮታዊ ዘቡ አባላት አሜሪካንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በመምራታቸው መሆናቸውን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ስር የሚገኘው ጉዳዩን የሚከታተል ክፍል በኤክስ ገጹ አመልክቷል።
“እነዚህ ግለሰቦች የአሜሪካ ወታደሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ እና ወሳኝ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የበይነ መረብ ጥቃት እንዲያደርሱ የአብዮታዊ ዘቡን ክፍሎች መርተዋል እንዲሁም አዝዘዋል” ሲል ከሷቸዋል።
በዚህም በተለይ ትኩረት የተደረገባቸው የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ አህመድ ቫሂዲ፣ የኢራን ጦር ኃይሎች ዕዝ የሆነው ኻታም አል አንቢያ አዛዥ አሊ አብዶላሂ፣ የአብዮታዊ ዘቡ የበይነ መረብ ክፍል አዛዥ ሃሚድሬዛ ላሽጋሪያን ይፈለጋሉ ከተባሉት የኢራን ባለሥልጣናት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
በተጨማሪም በዝርዝሩ ውስጥ የቀድሞው የአብዮታዊ ዘቡ የአየር ምድብ አዛዥ ሳኢድ አግጃኒ እና የቀድሞው የዘቡ የመረጃ ክፍል አዛዥ ማጂድ ኻዴሚ ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት የአብዮታዊ ዘቡ የቀድሞ ከፍተኛ አዛዦች በቅርቡ ተካሄደው ጦርነት ወቅት በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።