የሲአይኤ ኃላፊ ይፋ ላልሆነ ውይይት ወደ ሞስኮ መሄዳቸው ተዘገበ
የአሜሪካ ደህንነት መስሪያ ቤት፣ሲአይኤ፣ ኃላፊ ይፋ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ወደ ሞስኮ ማምራታቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገበ።
ጆን ራትክሊፍ ማክሰኞ ዕለት በወታደራዊ አውሮፕላን ወደ ሩሲያ ዋና ከተማ መጓዛቸው ተዘግቧል።
ዋሺንግተንም ሆነች ሞስኮ ኃላፊው ስላደረጉት ጉዞ እና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።
ኃላፊው በሞስኮ ቆይታቸውም ከማን ጋር እንደሚነጋገሩም የታወቀ ነገር የለም።
ብዙ ጊዜ የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለሥልጣናት በአካል ተገናኝተው አይወያዩም።
በረራን የሚከታተሉ ድረ-ገፆች ማክሰኞ ዕለት ከአሜሪካ የተነሳ ግዙፍ አውሮፕላን በላቲቪያ በኩል ወደ ሩሲያ ማምራቱን አሳይተዋል።
ቢቢሲ ሲአይኤን፣ ዋይት ሐውስን እና ፔንታጎንን አስተየየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች ሲ-17 የተሰኘ አውሮፕላን ሞስኮ ወደሚገኘው ቭኑኮቮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲቃረብ ያሳያል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ሌሎች ምስሎች ደግሞ ዲፕሎማቶችን የሚያጅቡ መኪኖች እና ሞተሮች በሞስኮ ጎዳና ላይ ሲያልፉ አሳይተዋል።
ከጉዞው በፊት አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ሞስኮ እንደሚጓዝ መናገሯን አንድ የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
ራትክሊፍ የሲአይኤ ዳይሬክተር ከሆኑ በኋላ ወደ ሩሲያ ሲጓዙ የመጀመሪያቸው ነው።
ሲአይኤ ከሞስኮ የደህንነት ኃላፊዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው።
ሩሲያ እአአ በ20222 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የተነሳ ከዓለም ተገልላ የምጣኔ ሃብት ማዕቀቦች ተጥለውባታል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ሞስኮ ካመሩ የአገሪቱ ባለሥልጣናት መካከል ራትክሊፍ አንዱ ሆነዋል።