ኢራን በኳታር የተመቱ የተዋጊ ጄት አብራሪዎቿ እንዲለቀቁ ጠየቀች

ኢራን ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ጦርነት በተጀመረበት ወቅት በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት ሁለት ተዋጊ ጄቶች በአየር መከላከያ ከተመቱ በኋላ በኳታር የተያዙት ሦስት ፓይለቶቿ እንዲለቀቁ ጠየቀች። ሦስቱ አብራሪዎች ላለፉት ስድስት ወራት በኳታር ተይዘው መቆየታቸውን ኢራን ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ኃላፊ በጻፈችው ደብዳቤ አስታውቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሆርሙዝ መከፈት ላይ ስምምነት ባለመደረሱ የነዳጅ ዋጋ መልሶ ጨመረ

    ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ ስለመከፈቱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነት ለመድረስ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ የነዳጅ ዋጋ ቅዳሜ እና እሁድ ከነበረበት ጭማሪ አሳየ።

    አሜሪካ የባሕር ላይ መተላለፊያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከፈት ብትፈልግም ኢራን ግን ከዚያ በፊት መሟላት ያለባቸው ስድስት ጉዳዮችን አቅርባለች።

    ሮይተርስ እንደዘገበው ዛሬ ሰኞ ማለዳ በእስያ ገበያ ላይ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ወደ አንድ ዶላር የሚጠጋ ጭማሪ አሳይቶ 84.46 ዶላር ሲሆን፣ የአሜሪካ ዌስት ቴክሳስ ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል 61 ሳንቲም ጨምሮ 78.79 ሆኗል።

    ኢራን እና ኦማን የሆርሙዝ ወሽመጥን መልሶ ለመክፈት ከስምምነት ይደርሳሉ በሚል ተስፋ ባለፈው ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ከሰባት ፐርሰንት በላይ ቅናሽ አሳይቶ ነበር።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ጥቃቶችን በመፈጸሟ የመርከቦች እንቅስቃሴ ተገትቶ ቆይቷል። በዚህም የነዳጅ ዋጋ ላይ ተጽእኖ ተፈጥሮ ቆይቷል።

  2. እስራኤል የትራምፕን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰላም ዕቅድ ውድቅ ማድረጓን ኔታንያሁ ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካውፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰላም ዕቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ገለጹ።

    ኔታንያሁ የሰላም ዕቅዱን ውድቅ ለማድረግ የሰጡት ምክንያት በቅድሚያ ሐማስ ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል ነው።

    የትራምፕ የሰላም ቦርድ ባለፈው ወር ሐማስ እና ሌሎች በጋዛ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች “ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈቱ” ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግሮ ነበር።

    ነገር ግን ሐማስ ከባድ መሣሪያዎቹን የሚያስረክበው እስራኤል “ማንኛውም ጥቃትን” ስታቆም እና ወታደሮቿን ከጋዛ ስታስወጣ መሆኑን ተናግሯል።

    እስራኤል በጥቅምት ወር የመጀመርያው የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ በጋዛ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።

    ኔታንያሁ እሁድ ዕለት ለተሰበሰበው ካቢኔያቸው “እስራኤል ባለ 15 ነጥብ ሰነዱን ውድቅ አድርጋለች” ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር “ሐማስ በትክክል ትጥቅ እስኪፈታ ድረስ [ከጋዛ] አይወጣም፤ እንዲሁም በዜጎቻችን እና በወታደሮቻችን ላይ የሚቃጣን ማንኛውም ስጋት ይቀለብሳል” ሲሉ ተናግረዋል።

    እሁድ ዕለት የሐማስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ቡድኑ ለስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት "እንደገና ያረጋግጣል"፤ እንዲሁም የ15 ነጥብ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ "በቁም ነገር እና በኃላፊነት ስሜት ለመሳተፍ" ዝግጁ ነው ብለዋል።

    በተጨማሪም አደራዳሪዎች “ስምምነቱን ሁሉም አካላት ተግባራዊ ማድረጋቸውን አንዲያረጋግጡ” ጥሪ አቅርበዋል።

    እስራኤል ዕቅዱን ውድቅ ማድረጓ መስከረም ወር ላይ ትራምፕ ያቀረቡት የጋዛ ዕቅድ ችግር እንደገጠመው ማሳያ ተደርጎ ተቆጥሯል።

    ዕቅዱ የሰላም ቦርድ መመስረትን፣ የሐማስ ትጥቅ መፍታትን፣ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ መውጣትን እና የጋዛን መልሶ ግንባታ የያዘ ነው።

    የኔታንያሁ አቋም ብዙዎችን ያስገረመ አልነበረም። ግን ይህንን አቋማቸውን ለማሳወቅ ትንሽ ጊዜ ወስደዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በትራምፕ ዕቅድ ደስተኛ አለመሆናቸው በግልጽ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ የቅርብ አጋራቸውን ማስቆጣት አለመፈለጋቸው አቋማቸውን ለማዘግየታቸው እንደምክንያት ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

    ትራምፕ "ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማምጣት ትልቅ እርምጃ" ብለው የጠሩትን ነገር ካሳወቁ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኖታል ።

    ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት የተስማማው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው ደግሞ እስራኤል ጦሯን ከጋዛ ማስወጣት እንዳለባት ነው።

    እሁድ ዕለት ኔታንያሁ እርሳቸው በሥልጣን ላይ እያሉ ይህ እንደማይሆን ለማሳየት ቆርጠው የተነሱ አስመስሏቸዋል።

    ሐማስ መጀመሪያ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የይስሙላ ትጥቅ መፍታት” ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።

    ኔታንያሁ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ወደፊት እንዴት መቀጠል እንደሚቻል እየተወያዩ መሆኑን ተናግረዋል።

    “ሀሳቦች አሏቸው፤ አንዳንዶቹ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ቅቡልነት የሌላቸው ናቸው፤ እናም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንዴት አቋም መያዝ እንዳለብን እናውቃለን” ብለዋል።