ተመራማሪዎች በቀላሉ የሚበሰብስ ፕላስቲክ መሥራታቸውን አስታወቁ
በለንደን የሚገኙ ተመራማሪዎቸ በዓለማቸን የመጀመሪያው የሆነ በቀላሉ የሚበሰብስ ፊኛ መሥራታቸውን አስታወቁ።
የኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪዎች የተለመደው ፊኛ ለመበስበስ እና ጎጂ ኬሚካሎችን ለመልቀቅ ዓመታት እንደሚፈጅበት ተናግረዋል።
ነገር ግን አሁን የሠሩት ፊኛ በቀላሉ በዘጠኝ ወር ውስጥ መበስበስ እንደሚችል ገልጸዋል።
ለምርምሩ ድጋፍ ያደረጉት ከድግሶች ተርፈው የሚጣሉ ፊኛዎች በውቅያኖስ እና በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ፍላጎት ያለው ቡድን ነው ተብሏል።
ይህ አዲሱ ፊኛ ‘ባዮሉን’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ከመደበኛው ፊኛ ጋር ዋጋው ተመሳሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ተመራማሪዎቹ አክለው ፊኛው በቀላሉ እንደሚፈነዳ አስረድተዋል።
በኢምፔሪያል ኮሌጅ ተመራማሪ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነችው ጁሊያና ከሚንግ “መደበኛው ፊኛዎች ጠንካራ እና ተለጣጭ እንዲሆኑ ተደርገው ነው የሚመረቱት” ብላለች።
“ነገር ግን ይህ በቀላሉ እንዳይበሰብሱ እና አካባቢን የሚበክል መርዛማ ኬሚካሎችን እንዲለቅቁ ያደርጋል” ሲሉ አስረድተዋል።
“የእኛ ፊኛ ግን በቀላሉ የሚበሰብሱ፣ ያለ ምንም ተጨማሪ ኬሚካል የሚመረቱ በመሆናቸው በቀላሉ ይበሰብሳሉ” ብላለች።
ከፍተኛ ድግሶችን በማዘጋጀት የምትታወቀው ሻርለት ሜሊያ በዝነኛ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተነሳ “በፊኛ የሚታጀቡ” ድግሶች እየተበራከቱ መጥተዋል ትላለች።
ሜሊያ እነዚህ ፊኛዎች በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሚያሰጋት ትናገራለች።
ሜሊያ አሁን ተመራማሪዎቹ በቀላሉ የሚበሰብስ ፊኛ ለመሥራት የተጠቀሙበት ቁስ ለሌሎችም የፕላስቲክ ምርቶች ላይ መጠቀም እንደሚቻል ያላትን ተስፋ ገልጻለች።