በጃፓን በተከሰተ ከዚህ ቀደም “ታይቶ የማይታወቅ” ከባድ ዝናብ ምክንያት ስምንት ሰዎች ሞቱ
በምሥራቃዊ ጃፓን ያጋጠመ ከባድ ዝናብ ቢያንስ የስምንት ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጓዦች በረራ እንዲስተጓጎል አደረገ።
ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት "ታይቶ የማይታወቅ" ሲሉ የገለጹት ይህ ከባድ ዝናብ፣ ቺባ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ከ20,000 በላይ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪል ኃይል እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል።
የቺባ ግዛት አስተዳዳሪ ቶሺሂቶ ኩማጋይ "ይህ ሁኔታ በጃፓን ታሪካዊ የአየር ሁኔታ እንኳ ሲታይ እጅግ ያልተለመደ ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ከዚህ ቀደም ለበርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ ሰጥቻለሁ፤ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ግን አጋጥሞኝ አያውቅም" ሲሉም አክለዋል።
የጃፓን ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲም “ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ዝናብ” እንደሚሆን አስቀድሞ ተንብዮ ነበር።
በዚህ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከሞቱት መካከል አንዷ በጎርፍ በተሸፈነ መንገድ ላይ ሳለች መኪናዋ ውስጥ ውሃ ገብቶ ሕይወቷ ማለፉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ሁለት ሰዎች ደግሞ መንገድ ላይ ወድቀው ሕይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነውን ‘ደረጃ አምስት’ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። ዛሬ አርብ ይህ ማስጠንቀቂያ ወደ ደረጃ አራት ዝቅ ቢደረግም፣ መሬት መንሸራተት እና ጎርፍ ሊፈጠር ይችላል የሚለው ስጋት አሁንም ቀጥሏል።
ይህ ከፍተኛ ዝናብ የተከሰተው በዚህ ሳምንት ጃፓን እና ጎረቤት አገራት ውስጥ ተከታታይ አውሎ ነፋሶች ከታዩ በኋላ ነው። የሚቲዮሮሎጂ ባለሙያዎች በዚህ ወቅት ባልተመደ መጠን የሚንቀሳቀስ አውሎንፋስ (ታይፉን) እንደሚከሰት ተንብየው ነበር።
አሁኑ ከፍተኛ ዝናብ፣ ወደ አገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የነፈሰው ሞቃት እና እርጥበታማ አየር ከላይ ካለው ቀዝቃዛ አየር ጋር መቀላቀሉ በፈጠረው ከፍተኛ የሆነው የአየር ሁኔታ መዛባት የተከሰተ መሆኑን የጃፓን ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።