ቀጥታ, አሜሪካ በኢራን ሰርግ ላይ ተፈጽሟል የተባለውን የሚሳዔል ጥቃት እየመረመረች መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ተናገሩ

በደቡባዊ ኢራን እየተካሄደ በነበረ ሰርግ ላይ በተፈጸመ የአሜሪካ የሚሳዔል ጥቃት ሁለት ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ የአራት ሰዎች ተገድለዋል ስለመባሉ የአሜሪካ ጦር ምርመራ እያደረገ መሆኑን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ አስታወቁ። ማክሰኞ ዕለት ሰርግ እየተደረገበት በነበረ በሲሪክ ከተማ የሚገኝ መኖሪያ ቤት በሚሳዔል ስብርባሪዎች መመታቱን የሰብአዊ ድርጅት የሆነው የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየመን ቀይ ባሕር አካባቢዎች በተካሄዱ ውጊያዎች ከ80 በላይ ተዋጊዎች ተገደሉ

    በየመን ሁቲ አማጺያን እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተሰጠው የአገሪቱ መንግሥት ኃይሎች መካከል ከሐሙስ ጀምሮ በቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች እና በታይዝ አውራጃ በተካሄዱ ውጊያዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ።

    የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ሁለት የጦር ኃላፊዎችን እና የሕክምና ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተካሄደው ውጊያ 41 የሁቲ ታጣቂዎችን ጨምሮ ቢያንስ 81 ተዋጊዎች ተገድለዋል።

    በቀይ ባሕር ዳርቻ ያለ አንድ ወታደራዊ ባለሥልጣን 24 ወታደሮቹ መሞታቸውን ሲገልጽ፣ ታይዝ በሚባለው አካባቢ በሚገኝ ስፍራ የሚገኝ ባለሥልጣን ደግሞ 15 ሰዎች መገደላቸውን ተናግሯል።

    በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የሕክምና ምንጮች እንዳሉት፣ ቢያንስ 42 የሁቲ ተዋጊዎች በውጊያው ተገድለዋል።

    ውጊያው የተቀሰቀሰው ሐሙስ ዕለት የሁቲ ኃይሎች በቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች እና በታይዝ ዙሪያ በሮኬቶች እና በድሮኖች የታገዘ የእግረኛ ተዋጊዎች ጥቃት ከከፈቱ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

  2. አሜሪካ ስለ የኢራን የሳይበር ዘመቻዎች ከፍተኛ አዛዥ መረጃ ለሚሰጥ 10 ሚሊዮን ዶላር ልትከፍል ነው

    አሜሪካ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሳይበር እና ኤሌክትሮኒክስ ዘመቻዎች ዕዝ ውስጥ ከፍተኛ አዛዥ የሆነው አሚር ያሪያብን ማንነት ወይም አድራሻውን የሚጠቁም መረጃ ለሚሰጥ ሰው እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት እንደምትሰጥ አስታወቀች።

    የአብዮታዊ ዘቡ ዕዝ ከፍተኛ አዛዥ ላይ የመረጃ ጥያቄ የቀረበው፣ “ሽልማት ለፍትህ” በሚባለው እና የአሜሪካ መንግሥት በወንጀል ስለሚፈልጋቸው ሰዎች ጥቆማ ለሚሰጡ የገንዘብ ሽልማት የሚያቀርብበት መርሃ ግብር አካኝነት ነው።

    በዚህም “በውጭ መንግሥታት ቁጥጥር ወይም መመሪያ ሥር ሆነው በአሜሪካ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ ጎጂ የሳይበር ጥቃቶችን የፈጸሙ ግለሰቦችን ለመለየት ወይም ለማግኘት የሚያስችል መረጃ ለሚያቀርብ ሰው እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ሽልማት ይሰጣል” ብሏል።

    የአሜሪካ መንግሥት አሁን ዝርዝር መረጃውን ለማግኘት ጥሪ ያቀረበበት አሚር ያሪያብ፣ በኢራን አብዮታዊ ዘብ ሥር የበይነ መረብ እና ኤሌክትሮኒክስ ወታደራዊ ጉዳዮችን በሚከታተለው ዕዝ ውስጥ "የበይነ መረብ ዘመቻዎች" ምክትል አዛዥ እንደሆነ ተገልጿል።

    ዋሽንግተን እንደምትለው ያሪያብ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በመከላከያ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በባሕር ትራንስፖርት፣ በጉዞ እና ቱሪዝም (ሆቴሎችና አየር መንገዶች)፣ በኃይል፣ በፋይናንስ እና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ላይ የተፈጸሙ አደገኛ የበይነ መረብ ጥቃቶችን ይመራ እንደነበር አሳውቃለች።

    ከሁለት ዓመታት በፊትም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተፈላጊዎችን የሚመለከት መረጃ ለማግኘት የኢራን አብዮታዊ ዘብ የበይነ መረብ ጥቃት የዕዝ ማዕከል ስድስት ከፍተኛ ኃላፊዎችን በሚመለከት ጥቆማ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

    በዚህም የስድስቱን አዛዦች ፎቶግራፎች በማውጣት እነዚህ ግለሰቦች የት እንደሚገኙ ወይም ማንነታቸውን ለማጋለጥ የሚያስችል ዝርዝር መረጃ ለሚሰጥ ሰው 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለማቅረብ ቃል ገብቶ ነበር።

  3. ብሪታኒያ ገንዘብ መቆጠብ እንዲቻል ወሳኝ ያልሆኑ ወታደራዊ ልምምዶች እንዲቆሙ አዘዘች

    የብሪታኒያ ሠራዊት ወጪን ለመቀነስ ሲባል “ወሳኝ ያልሆኑ” ወታደራዊ ልምምዶች እንዲቆሙ ትዕዛዝ መተላለፉን የመከላከያ ምንጮች ገለጹ።

    ነገር ግን እንደ ኢስቶኒያ፣ ፎክላንድ ወይም ቆጵሮስ ባሉ ግዛቶች ለመሰማራት የሚዘጋጁ ወይም ለተሰማሩ ወታደሮች የሚሰጠው ሥልጠና እንደሚቀጥል ተገልጿል።

    ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ የሚገኙ እና ለአንዳች ተልዕኮ ዝግጀት የማያደርጉ የጦር ክፍሎች ግን በፋይናንስ ጫና ምክንያት የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን እንዲቀንሱ ተነግሯቸዋል።

    ይህ ትዕዛዝ የተላለፈው አዲሱ ዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ለመከላከያ የሚያዘውን በጀት እንዲያሳድጉ ግፊት እየተደረገባቸው ባለበት ወቅት ነው።

    የአገሪቱ መንግሥት እስከ በሚቀጥለው ዓመት ለመከላከያ ወጪ የሚመደበው በጀት ከአገራዊ ጠቅላላ ገቢ ውስጥ 2.5 በመቶ ድርሻ እንዲይዝ የማድረግ ዕቅድ አለው። ነገር ግን ይህንን በጀት እስከ 2030 ድረስ 3 በመቶ የማድረስ ግብ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ የሚደረገው ጫና ጨምሯል።

    የአሁኑ ውሳኔ “ቢደረጉ ጥሩ የሆኑትን” እንደ ትላልቅ የቀጥታ ተኩስ ልምምዶች እንዲሁም በዊልትሻየር እና ዌልስ በሚገኙ የሥልጠና ስፍራዎች እንደሚደረጉ የማጥቃት ዝግጅቶችን የመሳሰሉ ሥልጠናዎች እንዲታጠፉ እንደሚያደርግ አንድ የመከላከያ ምንጭ ተናግረዋል።

    ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ልምምዶች አሁን እንደተቋረጡ ቢቢሲ ተገንዝቧል። ከተሰረዙት ዕቅዶች መካከል የሮያል ታንከኛ ክፍለ ጦር በዌልስ የሚያካሂደው የቀጥታ ተኩስ ልምምድ እንዲሁም ታንኮችን እና አፓቺ ሄሊኮፕተሮችን ያካተተ ሌላ ልምምድ ይገኙበታል።

    እንድ ምንጭ እንደሚናገሩት፣ ይህ ውሳኔ ሠራዊቱ የሚፈልገው ዓይነት አይደለም። ልምምዶች ላይ የተጣለው ገደብ የተያዘው አውሮፓውያን ዓመት እስከሚጠናቀቅ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

    ጦሩን የማዘመን ግብ ያላቸው እና የድሮን እና የፀረ ድሮን ውጊያ ልምምዶችን የመሳሰሉ ልዩ ሥልጠናዎች ግን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።

  4. አሜሪካ በኢራን ሰርግ ላይ ተፈጽሟል የተባለውን የሚሳዔል ጥቃት እየመረመረች መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ተናገሩ

    በደቡባዊ ኢራን እየተካሄደ በነበረ ሰርግ ላይ በተፈጸመ የአሜሪካ የሚሳዔል ጥቃት ሁለት ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ አራት ሰዎች ተገድለዋል ስለመባሉ የአሜሪካ ጦር ምርመራ እያደረገ መሆኑን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ አስታወቁ።

    ማክሰኞ ዕለት ሰርግ እየተደረገበት በነበረ በሲሪክ ከተማ የሚገኝ መኖሪያ ቤት በሚሳዔል ስብርባሪዎች መመታቱን የሰብአዊ ድርጅት የሆነው የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ገልጿል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ ድርጊቱን “የጦር ወንጀል” ሲሉ ጠርተውታል።

    በዕለቱ ኢራን የአሜሪካ ኃይሎች ላይ “የጥቃት ሙከራ” በማድረጓ፤ ዋሽንግተን ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን አስታውቃ ነበር። ይሁን እንጂ የአሜሪካ ጦር ዕዝ ቃል አቀባይ ሠራዊታቸው “መቼም ሲቪሎችን ዒላማ እንደማያደርግ” ተናግረዋል።

    ትናንት ሐሙስ መግለጫ የሰጡት ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ስለጥቃቱ በሚወጡ ዘገባዎች ላይ “እጅግ ከፍተኛ ጥርጣሬ” እንዳላቸው ገልጸዋል። ነገር ግን አሜሪካ ስለ ጉዳዩ ምርመራ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

    ቫንስ “እስካሁን በግጭቱ የተፈጠሩ ክስተቶችን በትክክል መከተብ ላይ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጥሩ አልነበሩም። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ” ሲሉ በዋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    ክስተቱን “እየመረመርነው እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉም አክለዋል።

    ኢራን ተፈጽሟል ለተባለው ለዚህ ጥቃት በሰጠችው ምላሽ፣ በኩዌት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ አዲስ ጥቃት ከፍታለች።

    የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር እንደገለጸው በቤተሰብ የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ባረፈው የሚሳዔል ስብርባሪ ምክንያት አራት ሰዎች ሲገደሉ 67 ሰዎች ቆስለዋል። አንዲት የ22 ዓመት ወጣት ሆስፒታል ውስጥ መሞቷት የገለጹት የኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር ወደ አምስት ከፍ አድርገውታል።

    በጥቃቱ የተገደሉት አራቱ ሰዎች የአራት ዓመቱ አሚራሊ ካሪሚ፣ የ16 ዓመቱ መሐመድ ማላሂ፣ የ46 ዓመቷ ኮልሱም ማላሂ ናዝድኒያ፣ እና የ50 ዓመቱ ዛርካቱን ታሄሪ እንደሆኑ ተገልጿል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ ማክሰኞ ዕለት በኩሄስታክ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የተቀረጸ ቪዲዮ እና ሁለት ፎቶዎች ያደረገው ምርመራ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ማማ ሲወድም አሳይቷል። ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት የተቀረጹ ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ ከማማው በስተሰሜን 130 ሜትር ርቀት ላይ እጅጉን የተጎዱ ቤቶችን ያሳያሉ።

    በተጨማሪም ቢቢሲ ፐርሺያን ፎረንሲክስ ባደረገው ምርመራ ሰርጉ ሲካሄድበት ከነበረው ቤት 112 ሜትር ርቀት የቴሌኮሙኒኬሽን ማማ መኖሩን ደርሶበታል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት መጨረሻ ኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የተጀመረው ይህ ጦርነት ከስድስት ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ እየተካሄደ ነው።

  5. የኬንያው ፕሬዝዳንት በአነስተኛ ንግድ ላይ በተሰማሩ የውጭ ዜጎች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘዙ

    የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ አገራቸው ውስጥ በአነስተኛ ንግዶች ላይ የተሰማሩ የውጭ አገራት ዜጎችን ለመቆጣጠር እርምጃ እንዲወሰድ አዘዙ።

    ፕሬዝዳንቱ “ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በእነዚህ አነስተኛ ንግዶች ላይ የተሰማሩ ሁሉም የውጭ አገራት ዜጎች ሥራቸውን ማቆም አለባቸው” ብለዋል።

    በተጨማሪም የውጭ ዜጎች በተወሰኑ የንግድ ዘርፎች ላይ እንዳይሰማሩ የሚያግድ ረቂቅ ሕግ እንዲፀድቅ ትኩረት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ኬንያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መሆኗን አረጋግጠው፣ ነገር ግን ቻይናውያን ነጋዴዎችን ጨምሮ ባለሀብቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እና ምርት ማሳደግ እንጂ በአነስተኛ ንግድ ላይ ከኬንያውያን ጋር መወዳደር አይገባቸውም ብለዋል።

    በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ወይም በዚህ እርምጃ ምን ያህሉ ተጎጂ እንደሚሆኑ ግን ግልጽ አይደለም።

    ኬንያ በርካታ ስደተኞችን የምታስተናግድ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ከስደተኞች ማቆያ ካምፖች ውጪ በመኖር እና በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

    የመንግሥት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ በኬንያ 857 ሺህ የሚጠጉ የተመዘገቡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 14 በመቶ የሚሆኑት በከተሞች አካባቢ ይኖራሉ።

    የኬንያ ሕግ ለስደተኞች የመሥራ እና የመነገድ መብት ይሰጣል፤ ሆኖም አስፈላጊውን ምዝገባ እና ሰነድ ማግኘት እንዲሁም ልዩ ፈቃድ ሊጠይቁ ይችላሉ።

    በናይሮቢ እና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች፣ ከአካባቢው አገራት የመጡ ስደተኞች በፀጉር ቤቶች እና በውበት ሳሎኖች፣ በግንባታ፣ በሞተር ሳይክል ታክሲ አገልግሎት፣ በጎዳና ላይ ንግድ እንዲሁም ልብስ፣ ምግብ እና የቤት ቁሳቁሶች በመሸጥ ላይ ተሰማርተዋል።

  6. ኢራን ከዚህ በኋላ ለአሜሪካ ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ ከሚጠበቀው በላይ የከፋ ይሆናል አለች

    አሜሪካ በዚህ ሳምንት በኢራን ዒላማዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት መልሳ መጀመሯን ተከትሎ ከዚህ በኋላ ኢራን ለሚፈጸምባት ጥቃት የምትመልሰው አጸፋ ከሚጠበቀው በላይ እንደሚሆን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ተናገሩ።

    የኢራን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሬዛ አሬፍ፣ አሜሪካ ባለፉት ቀናት በኢራን ላይ የፈጸመቻቸውን ጥቃቶች “ወንጀል” ሲሉ ገልጸው፣ “ከእንግዲህ በኋላ የእኛ ምላሽ ሚዛናዊ አይሆንም” ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “አሜሪካ በኢራን ሕዝብ ላይ የፈጸመቻቸው አዳዲስ ወንጀሎች የእኛን የደኅንነት ስሌቶች እና የመከላከያ መርኅን ቀይረውታል” ሲሉ ጽፈዋል።

    ይህንንም ተከትሎ በአሜሪካ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች “ከዚህ በኋላ የምንሰጠው ምላሽ ሚዛናዊ ያልሆነ፣ በበርካታ ደረጃዎች የሚፈጸም እና የአጥቂውን ደኅንነት የሚያሳጣ ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

    የኢራኑ የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት በመጨረሻም “አሜሪካውያን ቤንዚን እና ሌሎች ነዳጆችን ስለማከማቸት ማሰብ ይኖርባቸዋል” በማለትም አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ ኢብራሂም አዚዚ፣ ኢራን እስካላፈቀደች ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ተናገሩ።

    የአገሪቱ ምክር ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን ፈቃድ አይከፈትም፤ ይህም በግልጽ የሚታይ ነው” በማለት በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ ጠቅሰዋል።

    አዚዚ እንዳሉት፣ አሜሪካ ባለፉት ስድስት ወራት ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ለማስከፈት ያደረገቸው ጥረት ስላልተሳከ በአሁኑ ጊዜ “ክፉ ድርጊቶችን እየፈጸመች ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    አሜሪካ በወታደራዊ ጥቃት በኢራን ላይ ጫና ለማሳደር ከምደታርገው ዘመቻ በተጨማሪ ሌሎች ማዕቀቦች እና እገዳዎችን ተግባራዊ በማድረግ ኢራንን በምጣኔ ሀብት ለማዳከም አዲስ ዘመቻ ጀምራለች።

    እንዲሁም ባለፉት ቀናት አሜሪካ፣ በተለያዩ የኢራን ግዛቶች ውስጥ ጥቃቶችን ስትፈጽም ኢራንም በአጸፋው በዮርዳኖስ፣ በኩዌት እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት አድርሳለች።

  7. አገራት ከኢራን እንዲርቁ አሜሪካ ያወጣችውን ማስጠንቀቂያ ሩሲያ ውድቅ አደረገች

    አገራት ለኢራን የሚሰጡትን ድጋፍ እና የንግድ ግንኙነታቸውን በማቆም እራሳቸውን ከቴህራን እንዲያርቁ አሜሪካ የሰጠችውን ማስጠንቀቂያ ሩሲያ ውድቅ አደረገች።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በቅርቡ፣ “በኢራን ላይ ከዚህ በፊት ያልታዩ ቅጣቶችን እየጣልን ነው። ግጭቱን በፍጥነት ለማቆም የሚረዳውን መንገድ በሚያደናቅፍ ሁኔታ ማንም ለኢራን አገዛዝ እንዳያደርግ” ሲሉ አሳስበው ነበር።

    ስድስት ወራት በሞላው ጦርነት አሜሪካ በኢራን ላይ ከምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማሳደር ያላትን ዕቅድ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጋለች።

    በዚህም በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እና ዕገዳዎችን መጣል እንዲሁም ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው አገራት እና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰድን ዓላማ አድርጋለች።

    አገራትም ከኢራን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ አሜሪካ በይፋ ጥሪ ብታቀርብም ኃያላኑን ቻይናን እና ሩሲያን ጨምሮ ከአንዳንድ አገራት ጠንካራ የተቃውሞ ምላሽ ገጥሟታል።

    አሁን ሩሲያ በይፋ እንዳስታወቀችው በአሜሪካ ጫና ከኢራን ጋር የሚኖራት ግንኙነት ላይ ለውጥ እንደማይኖር ገልጻለች።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ እንደሉት “አጋሮች እና ወዳጆች አሉን፤ እነዚህን የወዳጅነት እና የሽርክና ግንኙነቶች ጠብቀን እናስቀጥላለን፣ ከዚያም በላይ እናጠናክራቸዋለን” ሲሉ ኢንተርፋክስ ለተባለው የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ፔስኮቭ አክለውም፣ አሜሪካ “ከሌላ አገር ጋር ያሉ ግንኙነቶችን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ወይም ለመጠቅለል የምትችል አይደለችም” ሲሉ የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ አጣጥለውታል።

  8. የኢራን ጦር በኩዌት በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

    የኢራን ጦር ሠራዊት በኩዌት የሚገኙ የሳተላይት መገናኛ ሥርዓቶችን፣ የመሳሪያ ማከማቻ ቦታዎችን እና የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ማቆሚያ መጠለያዎችን ዒላማ አድርጎ መምታቱን አስታወቀ።

    የኢራን ጦር ሐሙስ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፣ በኩዌት በሚገኘው አህመድ አል ጃበር የጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ ቁልፍ ወታደራዊ ዒላማዎችን በሚሳኤሎች እና ከፍተኛ የፍንዳታ አቅም ባላቸው ድሮኖች መምታቱን ገልጿል።

    የኢራን ጦር በፈጸመው ጥቃት በጦር ሰፈሩ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት “በመገናኛ ሥርዓቶች እና በተዋጊ አውሮፕላኖች መጠለያ ላይ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።

    በተመሳሳይ መግለጫው የኢራን ጦር፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሚገኘው አል ሚንሃድ የጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ “የአሜሪካ ጦር ኃይሎች መገኛ እና የራዳር ሥርዓቶችም” መምታቱን አስታውቋል።

    የኢራን ሠራዊት መግለጫውን ከማውጣቱ ከአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የኩዌት ጦር ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ ከኢራን የተነሱ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን ለመከላከል የአየር መከላከያ ሥርዓቶቿን በተጠንቀቅ ማቆሙን አሳውቆ ነበር።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በኢራን ላይ መፈጸም የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በአጸፋው በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት እየፈጸመች መሆኗን አስታውቃለች።

  9. ዓለም በኤል ኒኖ ምክንያት አደገኛ ሁኔታ እንደገጠማት የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ

    የኤል ኒኖ ተጽእኖዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መታየት እየጀመሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ዓለም “ወደ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች አደገኛ ቀጣና ውስጥ ገብታለች" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሳቡ።

    የዓለም የአየር ንብረት ድርጅት ስለዚህ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ባወጣው አዲስ ሪፖርት በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ኤል ኒኖ ከ70 ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ከታዩት እጅግ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል እና እስከ የካቲት 2019 ዓ.ም. ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ገልጿል።

    ኤል ኒኖ በዓለም ዙሪያ የአየር ሁኔታ ለውጥ በማስከተል አንዳንድ አካባቢዎችን ወደ ድርቅ ሲገፋ ሌሎች አካባቢዎችን ደግሞ ከፍተኛ የአውሎ ነፋስ እና ጎርፍ እንዲያጋጥማቸው ያደርጋል።

    የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ኤል ኒኖ በአንዳንድ ስፍራዎች የሙቀት መጠንን የበለጠ ከፍ ያደርጋል፤ ይህም በሰው ልጅ ተግባራት ምክንያት እየጨመረ ካለው ዓለም አቀፍ ሙቀት ጋር ተደምሮ ይከሰታል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ “ኤል ኒኖ እያየነው በእጅጉ እየተባባሰ ነው። ሳይንሱ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለውም፤ ምድራችን ያልተለመዱ ሁኔታዎች ውስጥ ገብታለች፣ በዚህም ውቅያኖሶች እየሞቁ ነው” ብለዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ከኤል ኒኖ ጋር የተያያዙ ሊከሰቱ የሚችሉ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን በተመለከተ የሚያወጣቸውን ትንበያዎች በተቻለ መጠን ለብዙ ማኅበረሰቦች ለማድረስ “ሰፊ የማስተባበር እንቅስቃሴ” ማካሄዱን ገልጿል።

    የኤል ኒኖ ክስተት በዓለም አቀፍ የአየር ሁኔታ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እስከ ቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ድረስ ሊቀጥል ቢችልም፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የዝናብ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ ለውጦች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

    በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመደበኛው በታች የሆነ ዝናብ እና ሞቃት የአየር ሁኔታ የድርቅ እና የደን ቃጠሎ አደጋዎችን ይጨምራል።

    በተጨማሪም በባሕር እና በውቅያኖሶች ውሃ ላይ ለውጥ ስለሚኖር እንደ ፓናማ ቦይ በመሳሰሉ መተላለፊያዎች ላይ በሚደረጉ የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።

  10. በኢራን ጥቃት መርከቧ መመታቱን እና ሁለት ሠራተኞች መገዳላቸውን ሳዑዲ ገለጸች

    ሳዑዲ አረቢያ፤ ኢራን በግዙፍ የነዳጅ ማጓጓዣ መርከቧ ላይ ጥቃት ፈጽማ ሁለት ፊሊፒናውያን የመርከቡ ሠራተኞች መገደላቸውን አወገዘች።

    ባህሪ የተባለው የሳዑዲ ብሔራዊ የመርከብ ማጓጓዣ ተቋም በበኩሉ “ሲድር” የተሰኘች የአገሪቱ መርከብ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ስትጓዝ የደኅንነት አደጋ ገጥሟታል ሲል ትናንት ረቡዕ አረጋግጧል።

    የባሕር ትራንስፖርት ደኅንነት ድርጅቶች እንዳሳወቁት ሲድር የተባለችወ መርከብ ከኦማን ሙሳንዳም ሰርጥ በስተሰሜን በተወንጫፊዎች ተመትታለች።

    በተመሳሳይ ሰዓት “ሴኔጋል ፕሮስፐሪቲ” የተባለች በደቡብ ኮሪያ ባለቤትነት የምትተዳደር ሌላ ግዙፍ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ከሙሳንዳም በስተምሥራቅ ተመትታ እንደነበር ተዘግቧል።

    የፊሊፒናውያን መርከበኞቹ ሞት የተገለጸው አሜሪካ በኢራን ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ካካሄደች በኋላ ነው። በምላሹም ኢራን በዙሪያዋ ባሉ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ኢላማ አድርጋለች። ይህም ካለፈው ሐምሌ ወዲህ በሁለቱ ወገኖች መካከል የታየ ከፍተኛው ግጭት መሆኑ ተጠቅሷል።

    ኢራን ሳዑዲ ባቀረበችው ክስ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ባልተፈቀደ መስመር ለማቋረጥ ሲሞክሩ በባሕር ላይ ፈንጂዎች ተመትተው ቃጠሎ እንደደረሰባቸው ገልጻ ነበር።

    የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአገሪቱ መርከብ ላይ ኢራን ፈጽማዋለች ያለውን ጥቃት በማውገዝ፣ ኢራን በዮርዳኖስ፣ በባህሬን እና በኩዌት ላይ የፈጸማቻቸውን ጥቃቶችን በመቃወም የባሕር ትራንስፖርት፣ የኃይል አቅርቦት እና የአገራት ሉዓላዊነት እንዲከበር አሳስቧል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ሁለት የነዳጅ ማጓጓዣ መርከቦች “በአሜሪካ ጦር ግፊት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ሕገ-ወጥ መስመር ላይ እንዲጓዙ ከተደረገ በኋላ የተጠመዱ ፈንጂዎች ተመትተዋል” ብሏል።

    መግለጫው አክሎም፣ እነዚህ መርከቦች “በአሁኑ ወቅት በእሳት እየተቃጠሉ ናቸው” ብሏል።

    የአሜሪካ ጦር በኢራን የተሰጠውን መግለጫ በተመለከተ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

    ሆኖም በኢራን ላይ የተፈጸሙት የቅርብ ጊዜ የአየር ድብደባዎች “በሆርሙዝ ወሽመጥ በንግድ መርከቦች ላይ እና በአሜሪካ ሠራዊት ላይ በኢራን አብዮታዊ ዘብ ለተወሰደው እርምጃ ምላሽ ነው” ሲል ገልጿል።

    አሜሪካ በኢራን በደቡባዊቷ ክፍል በፈጸመችው ጥቃት በአንድ የሰርግ ዝግጅት ላይ ሁለት ሕፃናትን ጨምሮ አራት ሰዎችን ገድላላች በማለት ጥቃቱን “የጦር ወንጀል” ስትል ኢራን ከስሳለች። የአሜሪካ ጦር በበኩሉ ክስተቱን እየመረመረ መሆኑን ገልጿል።

    ረቡዕ ዕለት የኢራን ጤና ሚኒስትር በአሜሪካ በተፈጸሙ ጥቃቶች 18 ሰዎች መገደላቸውን እና 108 ሰዎች መቁሰላቸውን አሳውቀዋል።

  11. ተመድ የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ ልውውጥ መባባሱ እንዳሳሰበው ገለጸ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደ አዲስ የተጠናከረው የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ ልውውጥ “እጅግ እንዳሳሰባቸው” የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናገሩ።

    የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ “ባለፈው ምሽት አሜሪካ እና ኢራን መካከል የነበረው የተኩስ ልውውጥ እጅግ እንዳሳሰባቸው ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል” ብለዋል።

    በተለይም የንጹኃን ዜጎች ግድያ እና በሰርግ ላይ የደረሰው ጥቃት እንዳሰጋቸው ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።

    ጉቴሬዝ “ንጹኃን ላይ የሚፈጸም ግድያ ተቀባይነት የለውም” ማለታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ዋና ጸሐፊው “ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ ሥር ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እንዲሁም ግጭትን ከሚያባብስ ድርጊት እንዲቆጠቡ” አሳስበዋል።

    የድርጅቱ ቃል አቀባይ እንደገለጹት ጉቴሬዝ “ለቀውሱ ወታደራዊ መፍትሔ እንደማይመጣ” ያምናሉ።

    “ብቸኛው መንገድ ዲፕሎማሲ ነው። ሁሉም ወገኖች ወደ ንግግር መመለስ አለባቸው” ሲሉም አሳስበዋል።

  12. አሜሪካ በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 19 መድረሱ ተዘገበ

    መልሶ ባገረሻው የኢራን እና የአሜሪካ ጥቃትን ተከትሎ ማክሰኞ ምሽት አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 19 ከፍ ማለቱን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    በጥቃቱ ኮሁስታክ በተባለው የኢራን ግዛት ቢያንስ አራት ሰዎች፣ በኹዜስታን ግዛት ሰባት ሰዎች፣ በከርማንሻህ አራት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሠራዊት አባላት የተገደሉ ሲሆን፤ በላቫን ደሴት ሦስት የባሲጅ ሚሊሻ አባላት እንዲሁም በፋርስ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ጃህሮም ውስጥ አንድ ሰው ተገድሏል።

    የኢራን ባለሥልጣናት በአሜሪካ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን በመግለጽ የአሜሪካንን እርምጃ እያወገዙ ይገኛሉ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል በሲሪክ ከተማ በነበረ የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የአሜሪካ ጥቃት ሁለት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

    ነገር ግን በኢራን ላይ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻን የሚመራው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) የተፈጸሙት ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ደያረጉ አይደሉም ሲል አስተባብሏል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት ከሞቱት 19 ሰዎች በተጨማሪ ከ50 በላይ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

  13. ግብፅ ውስጥ በደረሰ የመኪና አደጋ የ22 ሰዎች ሕይወት አለፈ

    በግብፅ ምሥራቃዊ ክፍል በደረሰ የአውቶቡስ አደጋ ቢያንስ 22 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በደቡብ ሲናይ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን ዳሃብ እና ኑዌይባ የቀይ ባሕር ዳርቻ ከተሞችን በሚያገናኘው መንገድ ላይ ዛሬ ረቡዕ በደረሰው አደጋ ሌሎች 28 ሰዎች ቆስለዋል።

    የግብፅ እና የዮርዳኖስ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ በአደጋው ከሞቱት መካከል እስከ 10 የሚደርሱ የዮርዳኖስ ዜጎች ሊኖሩ ይችላል።

    የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት የዚህ አደጋ መንስኤ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

    አካባቢው ከዓለም ዙሪያ በርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ ነው።

    አደጋው በደረሰበት ጊዜ በአውቶቡሱ ውስጥ ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ አልታወቀም።

    የግብፅ ጤና ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፣ የቆሰሉት ሁሉም ሰዎች በሦስት የተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና እያገኙ ነው።

    በግብፅ አደገኛ የመንገድ አደጋዎች የተለመዱ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በመኪና አደጋ መሞታቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

    እንደዚህ ያሉ አደጋዎች በአብዛኛው ጥንቃቄ በጎደለው ማሽከርከር እና በደካማ የመንገድ ጥገና ምክንያት እንደሚከሰቱ ይነገራል።

    ባለፈው ወር በሰሜን ምሥራቅ ግብፅ ኢስማኢሊያ ግዛት ውስጥ ሁለት ጭነት መኪኖች ተጋጭተው 18 ሰዎች ሲሞቱ 30 ሰዎች ቆስለው ነበር።

  14. በጊኒ ቢሳው የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን የሚያሰፋ አዲስ ሕገ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔ ጸደቀ

    ከወራት በኋላ አጠቃላይ ምርጫ በሚደረግባት ጊኒ ቢሳው በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን በከፍተኛ መጠን የሚያሰፋ አዲስ ሕገ መንግሥት ጸቀደ።

    ሕዝበ ውሳኔውን ያዘጋጀው ታኅሣሥ ላይ በተደረገው ምርጫ የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ የአገሪቱን ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት ነው።

    በሕዝበ ውሳኔው ድምፅ የሰጡ መራጮች ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ካቢኔውን እንዲሾም እና እንዲሽር እንዲሁም ከባድ የፖለቲካዊ ቀውስ ከተፈጠረ ፓርላማውን እንዲበትን የማድረግ ሥልጣን የሚሰጠውን ማሻሻያ ደግፈዋል።

    የጊኒ ቢሳው ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ በቂ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ገለልተኝነት የሌለው እንዲሁም አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ በመግለጽ ራሱን ከሕዝበ ውሳኔው አግልሏል።

    በዓለም ላይ ከሚገኙ ደሃ አገራት አንዷ የሆነችው ጊኒ ቢሳው በአውሮፓውያኑ 1974 ከፖርቱጋል ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ቢያንስ ዘጠኝ የተሳኩ እና የከሸፉ መፈንቅለ መንግሥቶችን አስተናግዳለች።

    አገሪቱ ሰዎች የማይኖሩባቸው በርካታ ደሴቶች ስላላት ለአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የተመቸች ሆናለች። የተባበሩት መንግሥታት “የናርኮ መንግሥት” የሚል ስያሜ ሰጥቷታል።

    በአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ የተደረገው የሕዝበ ውሳኔው ጊዜያዊ ውጤት እንደሚያሳየው፣ እሁድ ዕለት በተሰጠው ድምጽ ከተሳታፊዎቹ መካከል 70 በመቶው ለውጡን ደግፈዋል፤ 30 በመቶዎቹ ደግሞ ተቃውመውታል።

    ከተመዘገቡ መራጮች ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ ድምጻቸውን እንደሰጡ ተገልጿል።

    አዲሱ ሕገ መንግሥት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ተሸርሽሮ፣ የፕሬዝዳንቱ ኃይል እንዲጠናከር ያደርጋል። ጊኒ ቢሳው በምትከተለው ከፊል-ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት አማካነኝት የተዘረጋን የሥልጣን ክፍፍል ሚዛንንም ይቀይራል።

    ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚሾመው ፓርላማው ሲሆን የሚመረጠውም በምክር ቤቱ አብላጫውን መቀመጫ ከያዘው ፓርቲ ነው።

    አሁን አገሪቱን የሚመሩት የወታደራዊው መንግሥት ባለሥልጣናት ይህ አሠራር በአገሪቱ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አስተዋፅዖ እንዳለው በመግለጽ ይከራከራሉ።

    የአሁኑ ለውጥ ፕሬዝዳንቱ በመንግሥት ውስጥ ከፍ ያለ ሥልጣን እንዲኖረው ያደርጋል።

    በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ለአምስት ዓመት የሚቆይ የሁለት የሥልጣን ዘመን ገደብ ግን አልተነካም።

    የወታደራዊው አስተዳደር ባለሥልጣናት፣ እነዚህ ማሻሻያዎች መደረጋቸው በፕሬዝዳንቶች እና በጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከል በተደጋጋሚ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለማስቆም አስፈላጊ ናቸው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

    ይሁን እንጂ ሕዝበ ውሳኔው በአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሆነው የጊኒ እና ኬፕ ቨርዴ የነፃነት አፍሪካዊ ፓርቲ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል። ፓርቲው ደጋፊዎቹ ድምፅ እንዳይሰጡ አሳስቧል።

    የሚደረጉት ማሻሻያዎች በፕሬዝዳንቱ እጅ ከልክ ያለፈ ሥልጣን እንዲከማች ሊያደርግ ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል።

  15. ግዙፉ የአሜሪካ የጦር መርከብ ለ250 ቀናት መልሕቁን የጣለበት በወሲብ ንግድ የምትታወቀው የታይላንድ ከተማ

    በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በወደብ ሳያርፍ 250 ቀናትን ባሕር ላይ ያሳለፈው ‘ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን’ የተባለው የአሜሪካ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ በታይላንድ መልሕቁን ጣለ።

    የጦር መርከቡ መቆም ለስምንት ወራት በላይ መሬት ሳይረግጡ የከረሙት 5,000 ገደማ የባሕር ኃይል አባላቱ እጅግ ሲፈልጉ የነበረውን እረፍት የሰጠ ሆኗል።

    መርከቡ ያረፈው በግርግር በተሞላ የምሽት ሕይወት እና በወሲብ ቱሪዝም በሚታወቀው የታይላንድ ፓታያ ከተማ የሚገኝ የባሕር ዳርቻ ሪዞርት አቅራቢያ ነው።

    የአሜሪካው የጦር መርከብ ለስድስት ወር ለሚቆይ የፓስፊክ እና የደቡብ ቻይና ባሕር ግዳጅ ነበር ታኅሣሥ ላይ ከሳን ዲዬጎ የተነሳው።

    ይሁን እንጂ የካቲት መጨረሻ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈታቸውን ተከትሎ መርከቡ ጉዞውን ወደ ባሕረ ሰላጤው አድርጓል።

    የመርከቡ ስምሪት ከታሰበው የበለጠ ጊዜ በመውሰዱ የምግብ እጥረት እንዲሁም በሠራተኞቹ ላይ የአእምሮ መወጠር እንዳጋጠመ የተወሰኑ አሜሪካ የኮንግረስ አባላት በቅርቡ ተናግረው ነበር።

    አሜሪካ ባሕር ኃይል አባላቱ አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ቢያምንም፣ በቂ አቅርቦት እንዳላቸው ገልጿል።

    ከ286 ቀናት አጠቃላይ የባሕር ላይ ቆይታ በኋላ ታይላንድ የደረሱት የመርከቡ አባላት ለአምስት ቀናት እረፍት እንደሚያደርጉ እና እንደሚያገግሙ የታይላንድ ባለሥልናት መናራቸው ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካ ሠራዊት አባላቱ የታይላንድ ፓታያ ማረፋቸው በኢራን ጦርነት የተቀዛቀዘውን የከተማውን ኢኮኖሚያ ያነቃቃል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

    በአካባቢው የሚገኙ ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ሠራዊት አባላት መምጣት አስቀድሞ በተወሰኑት የከተማው የወሲብ ቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እርምጃ እንደወሰዱ ተዘግቧል።

    ታይላንድ ውስጥ የወሲብ ንግድ የተከለከለ ነው። ባለሥልጣናት አልፎ አልፎ እርምጃ የሚወስዱ ቢሆንም እንደ ፓታያ ያሉ ከተሞች በግልጽ በሚታይ ደረጃ ዋነኛ የወሲብ ቱሪዝም ማዕከል ናቸው።

    የአሜሪካ እና ታይላንድ ባለሥልጣናት ፓታያ ታዋቂ የሆነችበት ወሲብ ነክ ጉዳይ የዜና ርዕስ ሳይሆን የሠራዊት አባላቱ ቆይታ እንዲጠናቀቅ እየሞከሩ ነው።

    የአሜሪካ ወታደሮች መሄድ የማይችሉባቸው የተወሰኑ ቦታዎች እንዳሉ የታይላንድ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ከእነዚህ ስፍራዎች አንዱ ወደ ዋናው የባሕር ዳርቻ የሚወስደው እና በርካታ መጠጥ ቤቶች የሚገኙበት ‘ሶይ 6’ የተባለ አካባቢ ነው።

    የታይላንድ ፖሊስ የወሲብ ንግድ በአገሪቱ ሕግ የተከለከለ መሆኑን ለአሜሪካውያኑ ጎብኚዎች እየገለጸ ቢሆንም፣ ፓታያ ውስጥ 25,000 እስከ 50,000 የሚደርሱ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እንዳሉ ይታመናል።

    ብዙዎቹም የሚገኙት በመጠጥ ቤቶች ደጃፍ ላይ ቆመው ወንዶችን ወደ ውስጥ ለማስገባት በሚሞክሩበት ሶይ 6 ነው።

  16. ዩክሬን በሩሲያ አየር ክልል ላይ የሚበሩ አየር መንገዶችን አስጠነቀቀች

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎዲሚር ዜሌንስኪ አገራቸው በሩሲያ ላይ የምትፈጽመውን የድሮን ጥቃት በማጠናከሯ የሩሲያ የአየር ክልል “ይዘጋል” ሲሉ አየር መንገዶች አስጠነቀቁ።

    ዜሌንስኪ፤ “የሩሲያን የአየር ክልል የሚጠቀም ማንኛውንም አየር መንገድ፣ ኢንሹራንስ ሰጪዎች እና የሩሲያ ዋና ዋና አውሮፕላን ማረፊያዎችን የሚጠቀሙ ሁሉንም ማስጠንቀቅ እንፈልጋለን፤ የሩሲያ የአየር ክልል በእጅጉ አደገኛ እየሆነ ነው” ብለዋል።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደችው ባለው ወረራ ምክንያት አብዛኞቹ የምዕራብ አገራት የንግድ አየር መንገዶች በሩሲያ ሰማይ አይበሩም። እንደ ቻይና ያሉ አገራት አየር መንገዶች ግን አሁንም በሩሲያ ሰማይ ላይ ይጓዛሉ።

    ለዚህ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ማስጠንቀቂያ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሰጡት ምላሽ፣ የዜሌንስኪን አስተያየት “መንግሥታዊ የሽብርተኝነት አዋጅ” ሲሉ ገልጸውታል። ሩሲያም በዩክሬን ላይ እያጠናከረች ያለውን ጥቃት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የአየር ክልሉ ላይ ስለተደቀነው አደጋ ከፍተኛነት ሲያስረዱ፣ “ዩክሬን አንድም የሲቪል አየር ማረፊያ ላይ ስጋት አትደቅንም" ብለዋል።

    "ነገር ግን በሩሲያ ሰማይ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ድሮኖች ይኖራሉ፤ ይህም ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባ ጉዳይ ነው” በማለትም አሳስበዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ምሽት ባሠራጩት የቪዲዮ መልዕክት፣ “በሩሲያ የተጀመረው ጦርነት የራሷን የአየር ክልል እየዘጋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    የዜሌንስኪ ማስጠንቀቂያ በተለይ እንደ ሞስኮ እና ሴንት ፒተርስበርግ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ወደሚገኙ የሩሲያ አውሮፕላ ማረፊያዎች በረራዎችን ማካሄዳቸውን ለሚቀጥሉ የአየር መንገዶች የተሰጠ ነው።

    አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የሩሲያን ወረራ ተከትሎ የቀሰቀሰው ጦርነት ከድንበር አካባቢዎች ባይሻገርም ሁለቱ አገራት በሚፈጽሟቸው የድሮን ጥቃቶች ታላላቅ ከተሞች ድረስ ዘልቋል።

    በዚህም ዩክሬን በተለያዩ ጊዜያት የሩሲያ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ እስከ ሞስኮ የዘለቁ ጥቃቶችን ስትፈጽም፣ ሩሲያም በኪየቭ እና በሌሎችም ከተሞች ላይ ጥቃት እያደረሰች ነው።

    የአሁኑን የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ "ድርድር እንዲጀመር እየጠየቁ ነው... ነገር ግን ከሽብርተኞች ጋር አንደራደርም" ብለዋል።

  17. ከአሜሪካ ጋር የሚተባበሩ አገራት "አደገኛ ምላሽ" እንደሚጠብቃቸው ኢራን አስታወቀች

    አሜሪካ በኢራን ላይ ዳግም የከፈተችውን ጥቃት ተከትሎ ማክሰኞ ምሽት ሌላ ዙር ጥቃት ካደረሰች በኋላ ኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ዕዝ የአሜሪካ ወዳጅ የሆኑትን የአካባቢው አገራት አስጠነቀቀ።

    ኻታም አል አንቢያ የተባለው ኢራን ከአሜሪካ ጋር የምታካሂደውን ጦርነት የሚመራ ዋና ማዘዣ፣ አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ከአሜሪካ ጦር ጋር የሚተባበሩ የቀጣናው አገራት “አደገኛ ምላሽ ይጠብቃቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቋል።

    ዕዙ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት በወጣው መግለጫ፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና የአገሪቱ ጦር ኃይል ለአሜሪካ ጥቃት አጸፋ መስጠቱን ጠቅሶ፣ በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ ተቋማት እና ጦር ሰፈሮች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።

    ጨምሮም የአሜሪካ ኃይሎችን የሚያስተናግዱ የአካባቢው አገራት “ከጥቃት ፈጻሚው የአሜሪካ ጦር ጋር የሚያደርጉት ትብብር የሚያስከትለውን አደገኛ ውጤት መቀበል አለባቸው” ብሏል።

    አሜሪካ ማክሰኞ ምሽት በኢራን ደቡባዊ የባሕር ጠረፍ አካባቢዎች የአየር ጥቃት መፈጸም ከጀመረች ከአንድ ሰዓት በኋላ፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና ጦሩ በዮርዳኖስ፣ በባህሬን እና በኢራቅ የኤርቢል ከተማ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚሳዔል እና በድሮን ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል።

    በተጨማሪም የኩዌት ጦር ኃይል ከኢራን በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የአገሪቱ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ መደረጋቸው ተገልጿል።

    በማክሰኞው ምሽት በሲሪክ አካባቢ በሚገኘው የኮህስታክ መንደር በተፈጸመ የአሜሪካ የአየር ጥቃት፣ በሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበሩ ቢያንስ አምስት ሲቪሎች መገደላቸውን እና ከ60 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

    በኢራን መገናኛ ብዙኃን መረጃ መሠረት ከሟቾቹ መካከል አንድ ሕፃን ይገኛል፤ ከቆሰሉት አብዛኞቹም ከደህስታክ መንደር የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው።

  18. የአሜሪካ ጥቃት ሰርግ ላይ የነበሩ አራት ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ ኢራን የአጸፋ እርምጃ መውሰዷ ተገለጸ

    የአሜሪካ ጦር ማክሰኞ ምሽት በድጋሚ ኢራንን መምታቱን ተከትሎ፣ ቴህራን ኢራቅ እና ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኙ የዋሽንግተን ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት መክፈቷን የአገሪቱ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን እና የዮርዳኖስ ጦር አስታወቁ።

    አሜሪካ ደቡባዊ ኢራን ውስጥ ሲሪክ ከተማ የፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት ስብርባሪ ሰርግ እየተካሄደ የነበረበት ቤት ላይ በማረፉ ሕጻን ልጅን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ገልጿል። ከ50 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውንም ማኅበሩ ተናግሯል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፣ ኢራን ላይ ጥቃት የተፈጸመው፣ እስላማዊው አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ “በቅርቡ ያደረቸጋውን የጥቃት ሙከራዎች” ተከትሎ እንደሆነ ገልጿል።

    የአሜሪካ ተተኳሾች በኢራን ቻባሃር እና ኮናራክ የተባሉ አካባቢዎችን እንዲሁም ጂሮፍት ውስጥ የሚገኝ አየር ማረፊያን መምታታቸውን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ቃሽም ደሴት እና የወደብ ከተማው ባንዳር አባስ ውስጥም ፍንዳታ መሰማቱን በዘገባቸው ጠቅሰዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አሜሪካ ጥቃቶቹን በመፈጸሟ “ትጸጸታለች” ሲል ዝቷል። ዘቡ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ላይ ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ በርካታ የባለስቲክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፉን ከፊል ይፋዊ የሆነው ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የዮርዳኖስ ጦር 13 ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ማክሸፉን ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ 10 ያህሉ ሲወድሙ፣ ሦስቱ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ መውደቃቸውን አስታውቋል። ኢራን በፈጸመችው ጥቃት የሞተም ሆነ የተጎዳ ሰው የለም።

    የኩዌት ጦር ደግሞ የአገሪቱ አየር መከላከያ ስርዓት ዛሬ ረቡዕ ንጋት ላይ ከኢራን ለተወነጨፉ ሚሳዔሎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

    የኢራንን ጥቃት ተከትሎ ባህሬን ውስጥም በርካታ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የኢራኑ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ምሽት አሜሪካ ጥቃት መፈጸሟ በተገለጸበት ሰዓት፣ ኢራን የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች “እጅግ በጠነከረ እና ከፍተኛ ደረጃ” በድጋሚ እንደምትመታ አስጠንቅቀው ነበር።

    ሁለቱ አገራት በድጋሚ ግጭት ውስጥ የገቡት፣ አሜሪካ ከሐምሌ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ ምሽት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚገኘው የኢራኑ ላራክ ደሴት ውስጥ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ነው።

    ኢራንም በዮርዳኖስ የሚገኙ የአሜሪካ አየር ኃይል ጦር ሰፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ እና ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድሮን በመላክ የአጸፋ እርምጃ ወስዳ ነበር።

  19. የኬንያ አቪዬሽን ሠራተኞች ለሁለት ቀናት በረራዎች እንዲስተጓጎሉ ያደረገውን አድማ አቆሙ

    በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከሚገኘው ዋና አየር ማረፊያ እና ከሌሎች አገሪቱ ስፍራዎች የሚነሱ በረራዎች ለሁለት ቀናት እንዲስተጓጎሉ ያደረጉት የኬንያ የአቪዬሽን ሠራተኞች አድማቸውን አቆሙ።

    አድማው የቆመው ሠራተኞቹን የወከለው ማኅበር የደመወዝ ጥያቄ እና ሌሎች ቅሬታዎች እንዲፈቱ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ስምምነት በመድረሱ ነው።

    ማኅበሩ እና የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሠራተኞች ወዲያውኑ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚያደርግ ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ተፈራርመዋል።

    እሁድ ዕለት ቀስ በቀስ በተጀመረው አድማ ምክንያት በቀጣናው ቁልፍ የትራንስፖርት ማዕከል በሆነው የናይሮቢው በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ተስተጓጉለው ታይቷል።

    ሠራተኞቹ የተሻለ የሥራ ሁኔታ እንዲኖር እና ከዚህ ቀደም መግባባት የተደረበት ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ሲጠይቁ ነበር።

    የሠራተኞች ማኅበሩ መሪ ሞስ ንዲዬማ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የአድማ እርምጃው እንዲቆም እንዲሁም መደበኛው የሥራ እንቅስቃሴ እንዲመለስ እና አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አባሎቻችንን እየጠየቅን ነው” ብለዋል።

    “ሥራ ላይ ያሉ [ሠራተኞች] የተከማቹ በረራዎችን ማቃለል እንዲጀምሩ እየጠየቅን ነው” ሲሉም አክለዋል።

    የኬንያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴቪስ ቺርቺር አድማው እንዲካሄድ ምክንያት የሆኑ ቅሬታዎች የሚፈቱበትን መንገድ በተመለከተ ከማኅበሩ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

    “እዚህ መድረሳችን አሳዛኝ ነበር፣ ነገር ግን ከዚህ ወጥተናል። አሁን ቁጥሩ የለንም፤ ነገር ግን በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑ ያሳዝናል” ብለዋል።

    ሰኞ ዕለት በረራ የተስተጓጎለባቸው ተጓዦች በናይሮቢው ዋና አየር ማረፊያ ተሰብስበው ታይተዋል። የተወሰኑትም አዲስ ዜና ጥበቃ ምሽቱ በአየር ማረፊያው አሳልፈዋል።

    ኬንያ ኤርዌይስ ለስድስት ሰዓታት የቆየ የበረራ መዘግየት እንዳጋጠመ እና ያልተነሱ በረራዎች በመጠራቀማቸው የተወሰኑት እንዲሰረዙ መደረጉን አስታውቋል።

    ለመስተጓጎሉ ይቅርታ የጠየቀው አየር መንገዱ፣ ተጓዦች ያለ ቅጣት በረራቸውን መቀየር እንደሚችሉ ገልጿል።

  20. አሜሪካ ወደ ስምምነቱ ከተመለሰች ኢራንም በትግበራው እንደምትሳተፍ አስታወቀች

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤኪያን፤ አሜሪካ መግባቢያ ሰነዱን ወደ መተግበር ከተመለሰች ቴህራንም ወደ ስምምነቱ እንደምትመለስ ተናገሩ።

    የኢስላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ላይ የተቀመጡ ኃላፊነቶችን አሜሪካ የምትወጣ ከሆነ ኢራንም በምላሹ በአፋጣኝ ስምምነቱን እንደምትተገብር ገልጸዋል።

    በቢሽኬክ የሻንጋይ ትብብር ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢራን ፕሬዝዳንት “አሜሪካ የፕሬዝዳንቷ ፊርማ ያረፈበትን ስምምነት ከሁለት ሳምንት በላይ አልጠበቀችም። ስምምነቱን በመጣሷ በአጸፋው ከኢራን ተገቢው ምላሽ ተሰጥቷታል” ብለዋል።

    አሜሪካ ወደ ስምምነቱ ከተመለሰች ኢራንም የመግባቢያ ሰነዱን እንደምትተገብር አስረድተዋል።

    ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኢራን ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ ኃላፊዎች እንደተናገሩት ከሆነ አሜሪካ ወደ ስምምነቱ ከተመለሰች ቴህራንም ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ የምትደርስ ይሆናል።