በኢትዮጵያ የሚከሰሱት የግብፅ፣ የሱዳን እና የኤርትራ መሪዎች ምክክር በኤል አላሚን

በአፍሪካ ቀንድ ያለው ግጭት እና ውጥረት በበረታበት በአሁኑ ጊዜ ግብፅ የአካባቢውን ወዳጅ አገራት መሪዎችን በመሰብሰብ እየመከረች መሆኑ ተዘግቧል።
የግብፅ፣ የሱዳን፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ መሪዎች የሚገኙበት ይህ የአራትዮሽ ስብሰባ መሠረቱን ያደረገው ከጥቂት ዓመታት በፊት ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ አሥመራ ላይ የመሠረቱትን ትብብር ነው።
ግብፅ በኢትዮጵያ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ በተቃረበበት እና ኢትዮጵያ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ጋር በባሕር በር ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ በገባችበት ጊዜ ነበር የአገራቱ የጋራ ትበብር የተመሠረተው። ይህም የሦስቱ አገራት ጥምረት ከኢትዮጵያ አንጻር መፈጠሩ በስፋት ሲነገር ነበር።
አሁን ደግሞ ላለፉት ዓመታት ሲካሄድ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የተዳከመችው ሱዳን ወደ ስብስቡ ተካትታ ተሳታፊ ሆናለች።
የሱዳን ጦር ኃይል ኢትዮጵያ ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትደግፋለች የሚል ቅሬታ ያለው ሲሆን፣ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲያሰማ ቆይቷል።
ይህ ስብስብ የአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ አገር የሆነችው ኢትዮጵያን አለማካተቱ እና ከኢትዮጵያ በኩል በአብዛኞቹ የስብሰቡ አባላት ላይ የሚቀርበው ክስ፣ የአገራቱን ጥምረት ከኢትዮጵያ አንጻር የሚደረግ ምክክር አስመስሎታል።
ከዚህ ቀደም ግብፅ በተደጋጋሚ ባወጣቻቸው መግለጫዎች ላይ አጽንኦት የምትሰጠው የቀይ ባሕር ጉዳይ የተጎራባች አገራትን ብቻ የሚመለከት መሆኑ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ግልጽ ነው። እንዲሁም በሶማሊያ ውስጥ ሠራዊቷን የማሰማራት ፍላጎቷ የኢትዮጵያን ሚና ለመገዳደር ያለመ ነው ሲባል ቆይቷል።
በኢትዮጵያ በኩል ከሶማሊያ በስተቀር ሌሎቹ አገራት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ታጣቂ ቡድኖች በመደገፍ እና በማስታጠቅ ከበድ ያለ ክስ ይቀርብባቸዋል።
ግብፅ፣ ሱዳን እና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ በዐይነ ቁራኛ የሚጠባበቁ አገራት ሆነዋል።
ዛሬ እሁድ መስከረም 24/2019 ዓ.ም. ኤል አልአሚን በተባለችው የሰሜናዊ ግብፅ ከተማ አራቱ አገራት ምክክራቸውን የሚያደርጉት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ከኤርትራ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ከገባች ከቀናት በኋላ ነው።
የግብፁ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቀው የአራቱ አገራት መሪዎች "የጋራ በሆኑ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር እና ለመተባበር" ይወያያሉ።
ከዚህ አንጻር በቀዳሚነት ይነሳሉ ተብለው የሚጠበቁት በሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ የሶማሊያ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም የአብዛኞቹ ትኩረት የሆነችው የኢትዮጵያ ፍላጎት እና ወቅታዊ ሁኔታዋ ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, https://www.presidency.eg
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ 10 የኤርትራ እና አንድ የግብፅ ዲፕሎማቶችን ከአገሯ ስታባርር፣ በአጸፋው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ እንዲሁም ግብፅ የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ማስወጣቷ በስብሰባው ኢትዮጵያን የመነጋገሪያው ርዕስ ሊያደርጋት እንደሚችል ይገመታል።
ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ኤርትራን፣ ሱዳንን እና ግብፅን በተደጋጋሚ ስትከስ ብትቆይም አገራቱ አስተባብለዋል።
ነገር ግን በተለይ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት ተበላሽቶ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት በምዕራባውያን አገራት እና ተቋማት በኩል ተፈጥሯል።
በአገራቱ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ንግግሮች እና እርምጃዎች እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
በቀጣናው ያለው ውጥረት ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ከተገነባው ግዙፍ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ በሁሉም አቅጣጫ ተጽእኖ ማድረግ የምትፈልግ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከ35 ዓመታት በፊት ያለአግባብ አጣሁት ከምትለው የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የሚያጠነጥን ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሱዳን ጦር ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ እንዳያገኝ፣ ኤርትራ ደግሞ ሉዓላዊነቷ እንዲከበር ይፈልጋሉ።
ነገር ግን በሕዳሴው ግድብ ላይ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ሁለቱንም የሚያስማማ ነጥብ ላይ የሚደርሱበት ዕድል በቅርቡ የሚታይ አይደለም። በኢትዮጵያ በኩል ያለው የባሕር በር ፍላጎትም በቀላሉ የሚቀለበስ ካለመሆኑ በተጨማሪ ሉዓላዊ የባሕር በር የማግኘቱም ነገር ቀላል አይመስልም።
እየተጠናከረ የመጣው የግብፅ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን ትብብርም ወደ ቀጣናዊ ፍጥቻ እና ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት እየተስተጋባ ነው።
በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ተጠናክሮ የፌደራሉ ኃይሎች ወደ ትግራይ ዋና ከተማ ዘልቀው መግባታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት የሚቀሰቀስበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል እየተነገረ ነው።
አሥመራ ብታስተባብልም የፌደራሉ መንግሥት እና የአፋር ክልል ባለሥልጣናት የኤርትራ ኃይሎች ባለፉት ሳምንታት ውጊያዎች ውስጥ በግልጽ መሳተፋቸውን በመግለጽ የመንግሥት ምላሽ ቀላል እንደማይሆን እየተናገሩ ነው። ይህ ደግሞ ግጭቱ ድንበር ሊሻገር የሚችልበት ዕድል እንዳለ ጠቋሚ ነው።
ከእሁዱ ስብሰባ በፊት ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ግብፅ ለኤርትራ "ደኅንነት፣ መረጋጋት እንዲሁም ሉዓላዊነቷ እና ለግዛት አንድነቷ" ያላትን ድጋፍ እንደምትቀጥል በድጋሚ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ እንዳረጋገጡላቸው የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከሱዳን እና ከግብፅ ድጋፍ ያገኛሉ የምትላቸው የትግራይ ኃይሎች ከደቡባዊ እና ማዕከላዊ ትግራይ ገብተው ወደ ተራራማ እና ከኤርትራ ጋር ወደሚዋሰኑ የክልሉ አካባቢዎች በማፈግፈግ ፍልሚያቸውን እንደሚቀጥሉ እየተናገሩ ነው።
በእርግጥም ጦርነቱ እየገፋ ወደ ኤርትራ ድንበር የሚቃረብበት ሁኔታ ከተፈጠረ የሁለቱ አገራት ወደታሮች ወደ ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ የሚገቡበት ዕድል ሊፈጥር ይችላል። ይህ ደግሞ ከ30 ዓመታት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ከጀርባው ሌሎች አገራትን ያሰለፈ ከባድ ጦርነትን ሊያስከትል የሚችልበት አደጋ ይኖረዋል።



































