ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ግብፅ መጓዛቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, YEMANE G/MESKEL/X
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ግብፅ ማቅናታቸው ተገለጸ።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንደገለጹት፤ ፕሬዝዳንቱ ወደ ካይሮ የሚጓዙት ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታሕ አል-ሲሲ በቀረበላቸው ግብዣ ነው።
ዛሬ መስከረም 23፣ 2019 ዓ. ም. ወደ ግብፅ የተጓዙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ "የጋራ ደኅንነት፣ መረጋጋት እና አጋርነትን" በሚመለከተው የመንግሥታት ጉባዔ ላይ ይሳተፋሉ።
ፕሬዝዳንቱ በሁለቱ አገራት መካከል በሚካሄደው ቀጣናዊ የደኅንነት ውይይት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ግብፅ ከትናንት ጀምሮ 'አልአሜን አፍሪካ ፎረም' የተባለው ጉባዔ እያስተናገደች ትገኛለች። እስከ ነገ በሚዘልቀው ጉባዔ ላይ ለመታደም ከተገኙ መሪዎች መካከል የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ ይገኙበታል።
ግብፅ በዓመት ሁለት ጊዜ በምታስተናግደው ጉባዔ ላይ የሚታደሙት የኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ አንጎላ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄርያ፣ ሶማሊያ፣ ቡሩንዲ፣ ሊቢያ፣ ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ ናይጄርያ፣ ሴኔጋል፣ ቻድ እና ጋና መሪዎች መሆናቸውን የጉባዔው ድረ ገጽ ያመለክታል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ግብፅ ያቀኑት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደ አዲስ ባገረሸበት ወቅት እና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን ካስታወቀች በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን ካስተወቀች በኋላ ነበር ኤርትራም ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በማቋረጥ ምላሽ የሰጠችው።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የግብፅ ዲፕሎማት አሕመድ ሞሐራን አሕመድ ሶሊማን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ስትወስን ግብፅ በበኩሏ የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን ይፋ አድርጋለች።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳስታወቁት፤ አሁን ላይ የሚካሄደው ጉባዔ የቀይ ባሕር፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤ፣ የአረብ ባሕረ ሰላጤ እና የናይል ተፋሰስ አጎራባች አገራት ጉባዔ አካል ነው።
"በጉብኝቱ ወቅት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ፕሬዝዳንት አብደል ፋታሕ አል-ሲሲ የሁለትዮሽ ትብብርን ስለማሳደግ ይወያያሉ" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ እና ከግብፅ ጋር የዲፕሎማሲ ውዝግብ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሦስቱ አገራት መካረር እንዳሳሰበው እና በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ ለምትፈፅመው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት ስትል አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከአገሪቱ እንዲለቁ ትዕዛዝ መስጠቷን ገልጸለች።
የኤርትራ ኤምባሲ ይህንን ተከትሎ በሰጠው ምላሽ፤ ኢትዮጵያ "እነዚህን ያልተገቡ የጠብ አጫሪነት ድርጊቶች ምክንያታዊ ለማድረግ ኤርትራን ከስሳለች" ብሏል።
ኢትዮጵያ "ዲፕሎማሲያዊ ጥሰት" ፈጽመዋል ያለቻቸው የግብፅ ዲፕሎማት አሕመድ ሞሐራን አሕመድ ሶሊማን ከአገር እንዲወጡ አዝዛለች።
ኢትዮጵያ የግብፁ ዲፕሎማት ከአገር እንዲወጡ ላስተላለፈችው ውሳኔ በምላሹ ግብፅም በካይሮ ያሉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ከአገር እንዲወጡ አሳስባለች።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ኤርትራን እንዲሁም ግብፅን መክሰሳቸው አይዘነጋም።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱትን ጥምረት በመደገፍ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የግብፅ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡትም፤ ኢትዮጵያ "የውጭ ኃይሎችን ለውስጣዊ ውድቀቶቿ እና ዘላቂ ቀውሶቿ ተጠያቂ ታደርጋለች" ሲሉ የካይሮ ባለሥልጣናት ወንጅለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፤ ሦስቱ አገራት ልዩነታቸውን በአፍሪካ ኅብረት መርሕ መሠረት "በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች እና በሰላማዊ ንግግር እንዲፈቱ" አሳስቧል።



































