በአድዋ ከተማ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የእርዳታ ሠራተኞች ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአድዋ በሚገኘው ሰገን ሆቴል እና አካባቢውን ዒላማ ባደረጉ አራት ዙር ጥቃቶች 11 ሰዎች ሲገደሉ በሆቴሉ እና ሌሎች የንግድ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት ቅዳሜ መስከረም 23/2019 ዓ.ም. ሌሊት በተፈፀሙት የድሮን ጥቃቶች ዘጠኝ ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። ከሟቾቹ መካከል አራቱ ሴቶች መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ ለቢቢሲ ትግርኛ ገልፀዋል።

በሰገን ሆቴል የሚሠሩት አቶ ዘርኢት አሰፋ ጥቃቱን "አሰቃቂ" ሲሉ ገልፀውታል። እርሳቸው እንዳሉት በሆቴሉ መኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ የነበረ ተሽከርካሪን ዒላማ ባደረገው ጥቃት በሕንጻው የመሬት ወለል ላይ በነበረ መጠጥ ቤት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሞተዋል።

"ታችኛው ወለል የተከራየው ለቡና ቤት አገልግሎት ነው። እዚያ እየጠጡ የነበሩ ሰዎች ነበሩ። ጥቃቱ ሲደርስ በፍንጣሪ ሰዎች የሞቱትም እዚህ በመዝናናት ላይ የነበሩ ናቸው" ብለዋል።

ዘርኢት፣ በይበልጥ ጉዳት ያደረሰው የጥቃቱ ፍንጣሪ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የሆቴሉ መስታወቶች የተሰባበሩ ቢሆንም፣ "የሞተ አልጋ ተጠቃሚ የለም። ከሆቴሉ ሠራተኞች መካከልም የተጎዳ ሰው የለም" ሲሉ አክለዋል።

ምናልባት በሆቴሉ ባለሥልጣናት አርፈው እንደነበረ እንዲሁም ዒላማ የተደረገው መኪና የባለሥልጣን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ዘርኢት አሰፋ፣ ኢላማ የተደረገችው መኪና የማን እንደሆነችም ሆነ ባለሥልጣን በሆቴሉ ስለማረፉ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።

"ጥቃቱ ድንገተኛ እና በጣም ስሜት የሚነካ ነበር። አስከሬኖችን በዐይናችን አይተናል። ከራስህ ጋር የነበረን ሰው አስክሬን ማየት በጣም ከባድ ነገር ነው። ከባድ ድንጋጤና ከባድ ሐዘን ነው የፈጠረብን" በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።

ሌሎች ሁለት ተከታታይ የድሮን ጥቃቶች ደግሞ መሬት ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በአድዋ በሆቴል ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 9 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቦ ነበር።

በተጨማሪም እሑድ ለሰኞ አጥቢያ በሽራሮ አካባቢ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ላይ በተፈፀመ ሌላ ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የእርዳታ ሠራተኞችን ጠቅሶ የዘገበው ሮይተርስ፣ በሁለቱ ጥቃቶች በድምሩ 17 ሰዎች መሞታቸውን አብራርቷል። የዜና ወኪሉ ጥቃቱን ማን እንደፈጸመ ማረጋገጥ አልተቻለም ብሏል።

ቅዳሜ ሌሊት በአድዋ ሰገን ሆቴል ጥቃት ከደረሰ በኋላ ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ማቆሙን አቶ ዘርኢት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዕለቱ ከሰገን ሆቴል በተጨማሪ ፓን አፍሪካን እና ሸዊት ሆቴሎችም ላይ በተመሳሳይ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን ነገር ግን ከንብረት መውደም ሌላ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን እማኞች ገልፀዋል።

ቅዳሜ ምሽት በአድዋ በሚገኙት ሸዊት ኢንተርናሽናል ሆቴል እና ፓን አፍሪካ ሆቴል ላይም ጥቃቶች መፈፀማቸውን እማኞች ተናግረዋል።

ሊያ ግሪማይ የአድዋ ነዋሪ ስትሆን ከሸዊት ሆቴል ጎን የጀበና ቡና በማፍላት ኑሮዋን ትመራለች። ቅዳሜ ምሽት በሸዊት ሆቴል እና በፓን አፍሪካ ሆቴል ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች እንዳየች ተናግራለች።

ጥቃቶቹ የተፈፀሙት ቅዳሜ ምሽት ቀበሌ 06 እርሷ በምትሰራበት አካባቢ ሲሆን፣ በሆቴሎቹ ሕንጻዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቅሳ በሰው ላይ ግን ጉዳት እንዳልደረሰ ገልፃለች። ይህን ተከትሎ በከተማዋ ንግዶች መዘጋታቸውን እና ፍርሃት መንገሱንም ሊያ ተናግራለች።

የሸዊት ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ጥቃቱ መፈፀሙን ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ቢቢሲ የጥቃቱን መነሻ፣ የሟቾችን ቁጥር እና የተጎጂዎችን ማንነት በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም። በፌዴራል መንግሥት በኩልም ስለ ጥቃቱ የተባለ ነገር የለም።

የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን መቀሌ የመንግሥት ኃይሎች ባለፈው ሳምንት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ከተማዋ ቀስ በቀስ ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ እየተመለሰች መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ባንኮችን ጨምሮ የንግድ ተቋማት በአብዛኛው የተከፈቱ ሲሆን ስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶችም ከአንድ ሳምንት መቋረጥ በኋላ ተመልሰዋል።

አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ የመቀሌ እና የማይጨው ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለሳቸውን ነግረውናል።

ይሁንና በምሥራቅ ትግራይ ዞን የውቅሮ ከተማ አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ዳግም እየተደራጁ መሆናቸውን የታዘቡ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አዲስ ዙር ውጊያ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።

በሽረ እንዳሥላሰ ከተማ ያለው ሁኔታ ደግሞ ከሞላ ጎደል የተረጋጋ እንደሆነና የፌዴራል ኃይልም ሆነ የትግራይ ኃይሎች በከተማዋ እንደሌሉ ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ አስረድታለች።

መቀሌን እና በደቡባዊ ትግራይ የሚገኙ ከተሞችን ለቆ የወጣው በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥት፣ ከመስከረም 23 ጀምሮ የትጥቅ ትግሉን ከመቀሌ ውጭ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ግጭቱ አሁን ስላለበት ሁኔታ ከፌዴራሉ መንግሥት በኩል በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም።