ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በአውሮፓ ላይ ከፍታዋለች የተባለው የድሮን፣ የበይነ መረብ እና የሐሰተኛ መረጃ ጥቃት
በጀርመን ሊፕዚግ አውሮፕላን ማረፊያ ለደረሰው የድሮን ጥቃት ተጠያቂዋ ሩሲያ መሆኗ መገለጹን ተከትሎ በሞስኮ እና በምዕራባውያን መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት እንደተናገሩት፤ ፈንጂ የጫነ ድሮን በአውሮፕላን ማረፊያው መሰማራቱ "ሩሲያን በአውሮፓ ከምትፈጽማቸው ቅይጥ ኦፕሬሽኖች ጋር ተመሳሳይነት ያለው" ነው።
ከድሮን ጥቃቱ በኋላ ጀርመን እና ሩሲያ አንዳቸው በሌላቸው አገር ያላቸውን የባህል ማዕከላትን ዘግተዋል።
በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) የአሜሪካ አምባሳደር ማቲው ዊትከር የአውሮፕላን ማረፊያውን ክስተት፣ አውሮፓ ውስጥ ከተፈጠሩ "በጣም አስጊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች የከፋው" ብለውታል።
አውሮፕላን ማረፊያው ለዩክሬን በሚሰጠው የሎጅስቲክስ ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ በመላው አውሮፓ እየተስተዋለ ካለው አካሄድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ክስተት እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ሩሲያ በጥቃቱ እጇ እንደሌለበት አስተባብላለች። የጀርመን ክስ መሠረተ ቢስ እንደሆነ ገልጻለች። ከዚህ ቀደም በነበሩ ክስተቶች መወንጀሏንም አልተቀበለችም።
ስሎቫኪያ የሚገኘው የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ) ግሎብሴክ ባወጣው መረጃ፤ ከአውሮፓውያኑ ጥር 2022 እስከ ጥር 2026 ባሉት ዓመታት ውስጥ በሩሲያ አውሮፓ ላይ የተቃጡ 151 ድርጊቶች መመዝገቡን አስታውቋል።
ትክክለኛው ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
የተመዘገቡት ጥቃቶች የግድያ ሙከራ፣ ፍንዳታ፣ ማደናቀፍ፣ ውድመት እና ሕዝባዊ ነውጦችን ያካትታሉ።
በፖላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሊትዌኒያ፣ ኢስቶኒያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ላይ የደረሱት ጥቃቶች ሩሲያ የጥቃት ዒላማ የምታደርገው "ለዩክሬን ድጋፍ የሚሰጡትን እየለየች" መሆኑን እንደሚያሳይ ተገልጿል።
የአሜሪካ ምክር ቤት የጥናት ክፍል ነሐሴ ላይ ያወጣው ሪፖርት፣ ሩሲያ በአውሮፓ አገራት ላይ ያደረሰቻቸውን ጥቃቶች ይዘረዝራል።
በባቡር ጣቢያዎች እና ባሕር ሥር የተዘረጉ ኬብሎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ይገኙበታል።
በተጨማሪም "ግድያዎች፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ተጽዕኖ፣ የበይነ መረብ ጥቃት እንዲሁም የአየር ክልል ጥሰት" እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ሩሲ ቲንክ ታንክ ባለሙያ ኤምሊ ፌሪስ እንደምትለው ጥቃቶቹ ከ2022 ወዲህ መጠናቸው እና የሚደርሱበት ፍጥነት ጨምሯል።
ሞስኮ "በምዕራቡ ዓለም ቀውስ እና ነውጥ መፍጠር" እንደምትፈልግ ባለሙያዋ ታስረዳለች።
ይህም ኔቶ ለዩክሬን ከሚሰጠው ድጋፍ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ እና "ከጦርነት በታች የሆነ" ጥቃት ሊባል እንደሚችል ትናገራለች።
በግሎብሴክ የሚሠራው ማክሲም ቤዚኖሲክ እንደሚለው፤ ክሬምሊን "የኔቶን ዝግጁነት እየፈተሸ እንዲሁም በአጋር አገራት መካከል ያለውን ፖለቲካዊ እና የሕግ ክፍተት እየበዘበዘ" ነው። ሆነ ብሎ "ዓለም አቀፍ ጥርጣሬ" እየፈጠረ እንደሆነም ይናገራል።
በዩክሬን ከሚከሰተው "ከፍተኛ ሞት"፣ በጦርነቱ አንዳች አይነት ውጤት ካለማግኘት እንዲሁም እየበረታ ካለው ምጣኔ ሃብታዊ ጫና በመነሳት ሩሲያ ቅይጥ የጦርነት መንገድ እየተከተለች እንደሆነ ይናገራል።
"በአውሮፓ ላይ እየደረሱ ያሉት ቅይጥ ኦፕሬሽኖች ዓላማቸው ለዩክሬን የሚሰጠውን ድጋፍ መቀነስ እና በአነስተኛ ወጪ እንዲሁም አነስተኛ ተጋላጭነት የአውሮፓን መከላከያ ማዳከም ነው። ያልተመጣጠነ ቀውስ እና የፖለቲካ ስጋት መፍጠር ይፈልጋሉ" ሲል ያስረዳል።
ሩሲያ ፈጽማቸዋለች የተባሉ ጥቃቶች እስካሁን ድረስ ውስን ጉዳት ነው ያስከተሉት። ሆኖም ግን በደኅንነት ግብዓት ስምሪት ላይ ጫና ማሳደራቸው አልቀረም።
ኔቶ ለዩክሬን የሚሰጠው ድጋፍ የጀርባ አጥንት የሆነችው ፖላንድ ለዚህ ማሳያ ናት።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2025 ላይ የፖላንድ መንግሥት በግብዓት አመላላሽ ባቡር ጣቢያ ላይ የደረሰውን ጥቃት "ያልተጠበቀ የማሰናከል ተግባር" ሲል ገልጾታል።
ሁሉም የተገኙ መረጃዎች ለዚህ ተጠያቂዋ ሩሲያ መሆኗን እንደሚያሳዩ ፖላንድ ብትገልጽም ሞስኮ ግን ይሄንን አስተባብላለች።
ከዚህ ክስተት በኋላ ፖላንድ ቁልፍ መሠረተ ልማቶቿን ለመጠበቅ ወደ 10,000 ሠራዊት አሰማርታለች።
ታኅሣሥ ላይ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ድንበር የፀረ ድሮን መከላከያ ለመገንባት ከ4 ቢሊዮን በላይ የሚያስወጡ ስምምነቶች ተፈራርማለች።
በጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፈረንሳይ፣ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በአውሮፓ አገራት ወታደራዊ ተቋማት፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ቁልፍ መሠረተ ልማቶች አቅራቢያ ከሩሲያ ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው ተብለው የሚገመቱ የድሮን እንቅስቃሴዎች መከናወናቸው ተመልክቷል።
ቅይጥ ኦፕሬሽኖች መሬት ላይ በሚፈጸም ጥቃት ብቻ የተገደቡ አይደሉም።
የአውሮፓ መንግሥታት ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች የውሸት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በመፍጠር ሐሰተኛ መረጃን አሰራጭተዋል ሲሉ ከስሰዋል። በተጨማሪም ሐሰተኛ ሪፖርት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ ይዘት ማሰራጨታቸው ተገልጿል።
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በ2027 ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ሩሲያ ጫና አሳድራ ሊሆን ይችላል በሚል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ምርመራ አድርገዋል።
በጀርመን ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ ያለውን መተማመን ለመሸርሸር ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና በክልላዊ ምርጫዎች በመራጮች ድምጽ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ረገድ ሩሲያ ክስ ቀርቦባታል።
ማክሲም እንደሚለው የሩሲያ "መሠረታዊ ግብ" አልተለወጠም።
"ሩሲያ በርካታ ቁጥር ያላቸው መራጮችን ማሳመን አያስፈልጋትም። አሁን ያለውን መከፋፈል ልትጠቀምበት ትችላለች። ሩሲያን የሚተቹ ፖለቲከኞች ላይ ያለውን እምነት ትሸረሽራለች። በአጠቃላይ በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ ጥርጣሬ እንዲሰፋ ይደረጋል" ይላል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሩሲያ ከምታደርሰው ጥቃት ራሷን ለማራቅ መሞከር ጀምራለች።
ከዩክሬን ወረራ በኋላ የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖች "መጠነ ሰፊ በሆነ መንገድ ስለላ ለማከናወን" እንደሚውሉ የአውሮፓ መንግሥታት ደምድመዋል። በዲፕሎማትነት ስም የሚሰልሉ ያሏቸው ባለሥልጣናትንም ከግዛታቸው አባርረዋል።
ከዚህ በኋላ ሞስኮ ከሌሎች አገራት ሦስተኛ ወገን ሰዎችን በበይነ መረብ እየመለመለች በማሰማራት ውጤታማ መሆኗን ተንታኞች ይናገራሉ። ይህም የአውሮፓ አገራትን የፀረ ስለላ እንቅስቃሴን ለመገዳደር ነው።
ኤምሊ "አሁን ላይ የሚጠቀሙት ኤምባሲዎችን ሳይሆን እነዚህን ሦስተኛ ወገን ኃይሎች ነው" ስትል ታስረዳለች።
ከርዕዮ ዓለም ይልቅ ለገንዘብ ሲሉ ስለላውን የሚያከናውኑትን የውጭ ዜጎች ከክሬምሊን እንቅስቃሴ ጋር ለማስተሳሰር ቀላል አይደለም።
ያለፈው ታኅሣሥ ላይ የሉትዌንያ ባለሥልጣናት የሩሲያዊ ወታደራዊ የስለላ ተቋም በ2024 ከተሞከረ የፍንዳታ ጥቃት ጀርባ አለበት ሲሉ ከስሰዋል።
የእሳት ፍንዳታ ለማድረስ የተሞከረው ለዩክሬን የራድዮ መገናኛ መፈተኛ በሚመረትበት ፋብሪካ ላይ ነው።
ስድስት ስፔናውያን እንዲሁም የኮሎምቢያ፣ ኩባ፣ ሩሲያ እና ቤላሩስ ዜጎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ የሚፈረድባቸው ከሆነ እስከ 15 ዓመታት የሚደርስ እስራት ይጠብቃቸዋል።
ግሎብሴክ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፤ አውሮፓ ውስጥ ከደረሱ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት አላቸው ከተባሉ 172 ጥቃቶች መካከል 95 በመቶ ያህሉ የተፈጸሙት "ከሩሲያ የስለላ ተቋም ጋር ይፋዊ ግንኙነት በሌላቸው መደበኛ ዜጎች" አማካኝነት ነው።
"ይህም ነገሩን በተወሰነ ደረጃ ከሩሲያ ያርቀዋል" በማለት ባለሙያዋ ታስረዳለች።
በሩሲያ የተቃጣ ነው ብሎ ለመፈረጅ ጊዜ እንዲወስድ እና ከሕግ አንጻርም ውስብስብ እንዲሆን የሚያደርግም ነው።
"አብዛኞቹ ዝርዝር መረጃዎች የወጡት ዘግይተው ነው። ይህም ከባድ ያደርገዋል" ትላለች።
ማክሲም እንደሚናገረው ሩሲያ በምዕራባውያን የተጣለባትን የነዳጅ ማዕቀብ ለማለፍ የሌላ አገራት ሰንደቅ ዓላማ እና የወረቀት ላይ ኩባንያዎች በመጠቀም ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ታንቀሳቅሳለች።
ከ2004 ወዲህ እነዚህ መርከቦች ከባሕር በታች ባሉ ኬብሎች እና ቧንቧ ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመሩ ተገልጿል። በባለስቲክ እና የሰሜን ባሕር ቀጣናዎች ከሚታየው የድሮን እንቅስቃሴ እና ስለላ ጋርም ይገናኛሉ።
ሩሲያ ግን ይህንን ክስ አስተባብላለች።
ኔቶ እና የአውሮፓ ኅብረት ስጋት መፈጠሩን ከሚገልጹ ትርክቶች ባሻገር፤ ሩሲያ ስለምትፈጽመው የማሰናከል ተግባር ግልጽ መረጃ መስጠት እንዳለባቸው ማክሲም ይናገራል።
የማሰናከል ተግባር እንደ ነውጠኛ ድርጊት መታየት እንዳለበት እና በዲፕሎማሲው ረገድ ጥብቅ መርሕ መተግበር እንዳለበት ያስረዳል።
ማዕቀብ በመጣስ በሚንቀሳቀሱ የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ እንዲሁም ሩሲያ ከምርጫ በፊት በመገናኛ ብዙኃን ላይ ፈሰስ የምታደርገው ገንዘብ ላይ ጥብቅ ክልከላ መጣል አለበት ሲልም ይከራከራል።
ኔቶ እና የአውሮፓ ኅብረት ቁልፍ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ሲባል የስለላ ትብብራቸውን እያጠናከሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከሩሲያ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚባሉ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና መርከቦች ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦችም ጨምረዋል።
ነገር ግን ቅይጥ ጥቃትን ለመመከት ተጨማሪ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ኤምሊ እንደምትናገረው በአውሮፓውያኑ 2018 ሩሲያዊው ሰላይ ሰርጌ ስካይፓል እና ልጁን ኢንግላንድ ውስጥ ለመግደል ከተደረገው ሙከራ በኋላ የአውሮፓ አገራት ትብብር ጨምሯል።
በትብብር የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ማባረር አንደኛው እርምጃ ነው። ይህም በአውሮፓ ያለውን የሩሲያ የስለላ መረብ የፈተነ መሆኑን ትናገራለች።
ሁለቱ ተንታኞች ሩሲያ በቀጥታ ኔቶ ላይ ጦርነት የምከፍትበት ዕድል ጠባብ መሆኑን ያምናሉ።
የዩክሬን ጦርነት ሲያከትም ሩሲያ ሌላ ጠላት እስከምትፈጥር ዓመታት እንደሚቆጠሩ ኤምሊ ትናገራለች።
ማክሲም በበኩሉ ሩሲያ በኔቶ ምሥራቃዊ አካባቢ የተወሰነ እና አወዛጋቢ የሆነ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ትንኮሳ ልታደርስ እንደምትችል ያምናል።
ተንታኞቹ ሩሲያ የምትጠቀመው ቅይጥ ጦርነት እንደሚስፋፋ ይናገራሉ።
ሩሲያ ከኔቶ ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ማሰናከል፣ የበይነ መረብ ጥቃት እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እንደምትጠቀም ይናገራሉ።
እነዚህ ኦፕሬሽኖች ብዙ ወጪ የማያስፈልጋቸው እና በፍጥነት ሩሲያ ላይ የማይላከኩ እስከሆኑ ድረስም ይቀጥላሉ።
"ሞስኮ ከመጠን ያለፈ የፖለቲካ ነውጥ እስካልተፈጠረ ድረስ አውሮፓን መፈታተን አታቆምም" ሲል ተንታኙ ይናገራል።
ነገር ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ መካረሩ ሊባባስ ይችላል።
ለምሳሌ አደጋ ወይም ንጹኃን ላይ የሚደርስ ጉዳት አልያም ደግሞ ስሱ የሆነ ክስተት ከሁለቱም ወገኖች ፍላጎት ውጭ የሆነ መካረር ያስከትላል።
ኤምሊ ከሩሲያ ጋር ንግግር መቀጠል አለበት ብላ የምታምነውም ለዚህ ነው። ሐሳቡ ብዙም ተቀባይነት ባይኖረውም "አለመግባባት ተፈጥሮ ሞት ከመከተሉ በፊት" አስፈላጊነቱን ትጠቅሳለች።
የኔቶ እና ሩሲያ ምክር ቤትን ውይይትን በድጋሚ ማስጀመርን እንደ ምሳሌም ታነሳለች። ምክር ቤቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተወያየው በታኅሣሥ 2022 ነበር።