ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወርቅ በቤቱ አከማችቶ የነበረው የቀድሞው የአሜሪካ ሰላይ 200 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበሩን አመነ
የቀድሞው የአሜሪካ ሰላይ በቤቱ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥፍጥፍ ወርቆች ተከማችተው ከተገኙ በኋላ በሐሰተኛ አካውንቶች እና በሪል ስቴት ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበሩን አመነ።
የ49 ዓመቱ ዴቪድ ራሽ ለመንግሥት ያጭበረበረውን ገንዘብ እንዲሁም የገዛውን ቅንጡ ቤት፣ መኪናዎች፣ የእጅ ሰዓቶች እና ሌሎች እንዲመልስ ተጠይቋል።
ራሽ በተጨማሪም ለውጪ አገር መንግሥታት በብሔራዊ ደኅንነት ላይ "ከፍተኛ ጉዳት" የሚያድርስ ምሥጢራዊ መረጃ ማቀበሉን አምኗል።
በችሎት ክሳቸውን ያቀረቡት ዐቃቤ ሕግ "ተጠርጣሪው ጥፋተኛ መሆኑን የሚያምነው በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ ስለሆነ ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ የራሽን ጠበቃ ቢያነጋግርም አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ራሽ መጀመሪያ ላይ የሕዝብ ገንዘብ በመስረቅ ክስ ተመሥርቶበት የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን በኤሌክትሮኒክስ ማጭበርበር ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል። በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት፣ በቤቱ ላይ በተደረገ ብርበራ "ከሥራ ጋር በተያያዙ ወጪዎች" የተቀበላቸውን 298 የወርቅ ጥፍጥፎች ተገኝተዋል።
በጉዳዮ ላይ የተከፈቱ የፍርድ ቤት ክሶች አዳዲስ ዝርዝሮችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ራሽ ለአንድ የውጭ ባለሥልጣን "ማንነቱ ያለተገለጸ ሰላይ" መኖሩን እና የግለሰቡን ማንነት መግለጹ ይገኝበታል።
"እንደዚህ ዓይነት መረጃን ይፋ ማድረግ የሰውን ምንጭ እና ከምንጩ ጋር የሚሠሩ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናትን ደኅንነት እና ሕይወት እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት በምሥጢር ምንጮችን የመቅጠር አቅም አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ሲሉ ዐቃቤ ሕጎች በክሳቸው ላይ ጠቅሰዋል።
የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ በመግለጫቸው ላይ ራሽ "ሥልጣኑን አላግባብ ተጠቅሞ የሕዝብን እምነትን አጉድሏል፤ ለድርጊቱም ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆን አለበት" ብለዋል።
የኤፍቢአይ መርማሪዎች እንዳሉት እአአ ከኅዳር 2025 እስከ መጋቢት 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ ራሽ "ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እና ከሥራ ጋር ለተያያዙ ወጪዎች በአስር ሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት ጥፍጥፍ ወርቅ" ተቀብሏል።
"ራሽ በደቡብ ፍሎሪዳ ቅንጡ መኖሪያ ቤቱን የገዛበትን መንገድ ለማሳመን ከፍተኛ ምሥጢር ያለውን ፕሮግራም ፈጥሯል፤ ከዚያም የግል ጥቅም ለማግኘት በማሰብ እንደገና ለመሸጥ ተዘጋጅቶ ነበር" ሲል የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
ራሽ የራሱን ወጪ በማጽደቅ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብን ያለምንም ተቆጣጣሪ መጠቀም መቻሉን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
በደቡባዊ ፍሎሪዳ ቅንጡ ሪል ስቴት ለመግዛት "በማጭበርበር የተገኘ" የሕዝብ ገንዘብ ተጠቅሟል ያለው ክሱ፣ በፍርድ ማጭበርበሩ አንድ ቤት በማስዋብ ላይ የተሰማራ ግለሰብን መቅጠር እንዲሁም ለአንድ ንብረት 40 ሺህ ዶላር የሚያወጡ የወጥ ቤት እቃዎችን መግዛትን ያካትታል።
ባለፈው ዓመት በጥር ወር 45 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መፈጸሙን የሚያሳይ ሰነድ የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ለወንጀል ምርመራው መነሻ በመሆን አገልግሏል። ክሱ በተጨማሪም "ለአንድ መረጃውን ለማግኘት ኃላፊነት ላልተሰጠው እና ማወቅ ለሌለበት የውጭ መንግሥት ባለሥልጣን ከፍተኛ ምሥጢራዊ መረጃ" እንደሰጠ ይናገራል።
ከጥፍጥፍ ወርቆቹ ጋር ራሽ 2 ሚሊዮን ዶላር በጥሬ ገንዘብ እና 35 የቅንጦት ሰዓቶችን ይዞ ተገኝቷል።
ዐቃቤ ሕግ ራሽ ገንዘቡን ወደ ቁሳቁሶች እየቀየረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ገንዘቡን ለመደበቅ እየሞከረ መሆኑን የሚያሳይ "ጠንካራ ማስረጃ" መኖሩን ጠቅሷል።
ራሽ ከመርማሪዎቹ ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ሰዓቶቹን እና ሁለት የቢኤምደብሊው ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም ከባንክ ሂሳቡ የተወሰደውን ወደ 39 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማስረከብ ይጠበቅበታል።
የፌዴራሉ ዳኛ የእስር ጊዜውን ወደ ሌላ ጊዜ ያስተላልፉ ሲሆን በመጪው ጥር ችሎት እንዲቀርብ ቀጠሮ ሰጥተዋል።
በክሱ መሠረት ከፍተኛው የ20 ዓመት እስራት ቅጣት የሚጠብቀው ቢሆንም፣ ዐቃቤ ሕጎች ግን በፌዴራል ሕግ መሠረት ጊዜውን መጨመር እንደሚቻል አስታውቀዋል።