የህወሓት ኃይሎች መቀለን ለቅቀው መውጣታቸው ተዘገበ

የህወሓት ኃይሎች መዲናዋን ለቅቀው መውጣታቸውን የክልሉን ጋዜጠኛ እና ነዋሪዎችን ጠቅሶ የፈረንሳይ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘገበ።
ዛሬ መስከረም 23፣ 2019 ዓ. ም. የትግራይ ኃይሎች መቀለን ለቅቀው እየወጡ መሆኑ የተዘገበው የፌዴራል ኃይሎች ወደ ከተማዋ እየተቃረቡ መሆናቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
የፌዴራል ኃይሎች ወደ ከተማዋ መጠጋታቸውን ኤኤፍፒም በዘገባው ጠቅሷል።
ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር በመሆን ከትግራይ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ያለው 'የትግራይ የሰላም ኃይሎች' በበኩሉ፤ የክልሉን ዋነኛ አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠሩን መግለጹን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህወሓትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት መመሥረታቸውን ባስታወቁ ማግሥት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግመኛ ተቀስቅሷል።
የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸው ያሳወቁት 13/2019 ዓ. ም. ነበር።
ከዚያ ወዲህ ባሉት ቀናት በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች ላይ ውጊያው ቀጥሏል።
ትናንት አርብ 'የትግራይ የሰላም ኃይሎች' በኤክስ ገጽ ላይ "የመቀ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረናል" ሲል አስታውቋል።
ይሄንን በተመለከተ ሮይተርስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ምላሽ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ በዘገባው አትቷል።
ከህወሓት በኩል አስተያየት ማግኘት እንዳልተቻለም ተጠቅሷል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግመኛ መቀስቀሱ፤ ከአራት ዓመት በፊት በፕሪቶሪያ ስምምነት ተጠናቆ ወደነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት አገሪቱን ይመልሳል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
የፌደራል ሠራዊቱ ወደ ትግራይ መዲና እየተቃረበ መሆኑ ባለፉት ቀናት ሲገለጽ ቆይቷል።
የፌዴራል ኃይሎች እና የመንግሥት አጋር የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ባሉት እርምጃ አላማጣ ከተማን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ወደ ክልሉ መዲና መቀለ እያመሩ እንደሆነ ተገልጿል።
የመንግሥት ደጋፊ ታጣቂዎች አርብ ዕለት መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
ኤኤፍፒ ያነጋገረው ጋዜጠኛ "የህወሓት ታጣቂዎች እና መሪዎች ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው" ብሏል።
ሆኖም የፌደራል ኃይሎች በከተማዋ ውስጥ አለመታየታቸውን ጠቅሷል።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ያለምንም የፀጥታ ኃይል መቅረታቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማዋ የፀጥታ ኃይሎች ባለመኖራቸው "የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረቶች ለዘረፋ ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ስጋት" እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሌላ ነዋሪም "በከተማዋ ሥርዓት አልበኝነት ሊስፋፋ እንደሚችል እና ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ" ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደምም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የረድዔት ድርጅት ምንጭም የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ሙሉ በሙሉ መውጣታቸውን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
የህወሓት ሊቀ መንበር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ሐሙስ ዕለት በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው በውጊያው ያለውን ወታደራዊ ሁኔታ ሲያብራሩ የትግራይ ጦር "በተለያዩ አካባቢዎች እየተዋጋ መሆኑን" ገልጸዋል።
አያይዘውም ውጊያው "ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ" እንደሆነ ጠቅሰው፤ የፌዴራል ኃይሎች የትግራይን "አንዳንድ ክፍሎች ሊይዙ እንደሚችሉ" ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ይህ "ሆነ ተብሎ የተደረገ ስትራቴጂካዊ እርምጃ" መሆኑን ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥቱ እና አጋሮቹ የህወሓት ታጣቂዎች ይዘዋቸው የነበሯቸውን አንዳንድ ሥፍራዎች ማስለቀቃቸው በተሰማበት ወቅት መግለጫ የሰጡት ደብረፅዮን "ጠላትን የምንወጋው እሱ በመረጠልን ቦታ ሳይሆን እኛ በመረጥነው ቦታ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል ከህወሓት ተነጥሎ የወጣው 'የትግራይ የሰላም ኃይሎች' አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ቲቢኤስ ለተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ "ጦራቸው እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በርካታ የትግራይ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደነበር" ተናግረዋል።
"አብዛኛዎቹ የራያ አካባቢዎች እና አንዳንድ የእንደርታ፣ የሰማር እና የተምቤን አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር መዋል ጀምረዋል" ብለዋል።
አክለውም "በቅርቡ ወደ ትግራይ መሃል እንገባለን" በማለት ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች ሰላምን በማረጋገጥ እና የሰዎችን ንብረት በመጠበቅ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ቢቢሲ ሁለቱም ወገኖች የተናገሩትን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ ሲመጣ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡን ቀጥሏል።
በአላማጣ እና አካባቢው ደረሰ በተባለ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ ቢያንስ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪ እና አንድ የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በአላማጣ እና አካባቢው ከመስከረም 16 እስከ 19፣ 2019 ዓ.ም. ድረስ ከባድ ውጊያ መካሄዱን ጨምረው ገልጸዋል።
ከመስከረም 12 እስከ መስከረም 15፣ 2019 ዓ. ም. ድረስ በኮረም እና አላማጣ ሆስፒታሎች የገቡ ታካሚዎች ቁጥር በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ180 ወደ 420 ከፍ ማለቱን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ገልጿል።
በተቋሙ ድጋፍ መስከረም 15፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ሽረ ወደሚገኘው ስኹል ሆስፒታል የገቡ በጦርነት የተጎዱ ታካሚዎች ከ300 በላይ እንደሚሆኑ አስታውቋል።
ጦርነቱ የኢትዮጵያ ባላሥልጣናት ታጣቂዎችን በመደገፍ በሚከሷቸው ኤርትራ እና ግብፅ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አበላሽቶታል።


































