የሀገረ-ሰብ ሙዚቃ ፈርጧ ዶሊ ፓርተን ለአጭር ጊዜ በካንሰር ታምማ ሕይወቷ አለፈ

የሀገረ-ሰብ ሙዚቃ ፈርጧ ዶሊ ፓርተን

የፎቶው ባለመብት, Gary Wolstenholme/Redferns via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሀገረ-ሰብ ሙዚቃ ፈርጧ ዶሊ ፓርተን ለአጭር ጊዜ ከካንሰር ጋር ከታገለች በኋላ እጅ ሰጠች።

የሀገረ-ሰብ (ካንትሪ) ሙዚቃ ንግሥት የሆነችው፤ በልዩ የድምፅ አወጣጧ፣ ልብ በሚነኩ ግጥሞቿ እና በተለዩ ውብ አልባሳቷ የምትታወቀው፤ ከቴነሲ ተራሮች ተነስታ የታዋቂነት ቁንጮ ላይ መድረስ የቻለችው ዶሊ ፓርተን በናሽቪል እስከወዲያኛው አንቀላፍታለች።

ተወዳጇ የሙዚቃ ኮከብ በ80 ዓመቷ ነው የሞተችው።

ቃል አቀባይዋ ማርሴል ፓሪሶ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ "ለአጭር ጊዜ ከቆየባት የካንሰር ሕመም ጋር በድፍረት ከታገለች በኋላ፣ ዶሊ ዛሬ በቫንደርቢልት-ኢን ግራም የካንሰር ማዕከል በቤተሰቦቿ እና በወዳጅ ዘመዶቿ እንደተከበበች ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች" ብሏል።

በሸንቃጣ ሰውነቷ፣ ለዚሁ የሰውነት ቅርጿ በሚስማሙ አልባሳቷ፣ በተለያዩ የዊግ ፀጉሮቿ የምትታወቀው ዝነኛዋ አርቲስት፤ በትውልድ፣ በቦታ እና በፖለቲካ አጥር ሳይገደቡ በሁሉም ዘንድ ከፍተኛ ፍቅርን ካተረፉ የሙዚቃ ባለሞያዎች አንዷ ነበረች።

ዶሊ ፓርተን፣ እንደ "ጆሊን"፣ "ኮት ኦፍ መኒ ከለርስ" እና "አይ ዊል ኦልዌይስ ላቭ ዩ" ያሉ ዘመን ያልሻራቸው ዘፈኖችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሙዚቃ ግጥሞችን ጽፋለች። እነዚህ ተወዳጅ ስራዎቿ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ በዓለም አቀፍ ሽያጭ እና በኢንተርኔት ከአንድ ቢሊዮን በላይ እይታዎችን አግኝተዋል።

በመድረክ ዝግጅቶቿ ላይ በረጅም ጣቶቿ፣ ጊታር የምትጫወተው ፓርተን፤ በትውልድ ስፍራዋ አቅራቢያ በሚገኘው የስሞኪ ተራሮች ግርጌ የሠራችውን የሕዝብ መዝናኛ (መናፈሻን) ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን ያከናወነች ለጋስ በጎ አድራጊ እንደነበረች ይነገርላታል። በንግዱም ዓለም ቢሆን የተሳካላት የንግድ ሴት ነበረች።

እሷ እንደምትለው፣ "ተራ የቴነሲ ድሃ ቤተሰብ" ውስጥ ከተወለዱ 12 ልጆች አንዷ ሆና ያደገች እንደመሆኗ፣ ይህ የኋላ ታሪኳ በሙዚቃ ሕይወቷ ላይ ዘላለማዊ ተፅዕኖ አሳርፏል።

ሕይወትን ለማሸነፍ ሲል ትምህርቱን አቋርጦ በዕርሻ ሥራ ላይ ለመሰማራት የተገደደው አባቷ ለማንበብ የሚረዳውን ትምህርት እንኳን ለማግነት ተቸግሯል።

እናም በቴነሲ ለሚገኙ ህጻናት ነጻ መጽሐፍትን በመላክ እኘዓ ላይብረሪ በማቋቋም ነው በትምህርት ላይ የምትሰራውን የበጎ አድራጎት ሥራ የጀመረችው።

የፓርተን የመጀመሪያ የሙዚቃ ሥራ የጀመረው አያቷ ሰባኪ በነበሩበት ቤተክርስቲያን ውስት ነው።

በ10 ዓመቷ ጊታር መማር ጀመረች። በአካባቢዋ ባሉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይም መዘመር ጀመረች። በ13 ዓመቷ በናሽቪል በሚገኘው ግራንድ ኦል ኦፕሪ ላይ ስትቀርብ፥ አዘጋጁ ጆኒ ካሽ "ከምሥራቃዊ ቴነሲ የመጣች አንዲት ትንሽ ልጅ" በማለት ከእድሜዋ አንጻር ጠቅሷት በማንቆለጳጰስ አስተዋውቋታል።

በ1964 ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቀች በኋላ፣ የዘፈን ስራዎችን የያዘች ቦርሳ ይዛ፣ የዘፈን ደራሲ ከሆነው አጎቷ ቢል ኦውንስጋር ወደ ናሽቪል አቀናች። ይህም የሙዚቃ ሕይወት መንገዷን ያቀና አጋጣሚ ሆኗል።

ሮይ ኦርቢሰንን፣ ዊሊ ኔልሰንን ጨምሮ እና የሌሎችንም ታዋቂ አርቲስቶች ስራዎች ያዘጋጀው ፍሬድ ፎስተር የዶሊ ፓርተንን አቅም ያየው በጊዜ ነበር። ዘፈኖቿን ቀድቶ ለአድማጮች እንዲደርስ አድርጓል። ሌሎች አርቲስቶችም የእሷን ዘፈኖች እንዲጫወቱት አድርጓል። እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ፓርተን ተቀዳሚዋ የናሽቪል ንግሥት ነበረች።

ዶሊ ፓርተን ከኬኒ ሮጀርስ ጋር እአአ በ1985 ስታቀነቅን

የፎቶው ባለመብት, PL Gould/IMAGES/Getty Images