በሳዑዲ የሚደገፉት የየመን መንግሥት ኃይሎች የቀይ ባሕር መተላለፊያን "እንደተቆጣጠሩ" አስታወቁ

የየመን መንግሥትን የሚደግፉ ወታደሮች ከታይዝ ከተማ በስተምስራቅ በሚገኝ አካባቢ ቆመው
የምስሉ መግለጫ, የየመን መንግሥት በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ግዛቶችን መልሶ ለመቆጣጠር ያለመ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን ገልጿል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የየመን መንግሥት ደጋፊ የሆኑት ኃይሎች በቀይ ባሕር ደቡባዊ መስመር ላይ የባብ ኤል-መንዳብ ወሽመጥን "እንደተቆጣጠሩ" አስታወቁ።

ሳዑዲ አረቢያ የምትደግፋቸው ኃይሎች ይህንን አካባቢ መቆጣጠራቸው በኢራን ለሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ከፍተኛ ውድቀት ነው።

የየመኑ ጦር እንዳለው ናሽናል ሺልድ፣ ጃያንትስ ብርጌድስ እና ቲሀማ ሬዚስታንስ የተባሉት ኃይሎች ትናንት ሰኞ ከሰዓት የቀይ ባሕር ከተማ የሆነችውን ሞክሀ ተቆጣጥረተዋል።

እነዚህ ኃይሎች ከተማዋን በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉት ሳዑዲ የአየር ጥቃት በመፈጸም በሰጠችው ድጋፍ ነው ተብሏል።

ሆኖም ግን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ያነጋገሯቸው ስማቸው ያልተጠቀሰ የየመን መንግሥት እና ወታደራዊ ምንጮች እንዳሉት፤ እነዚህ ኃይሎች በከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ ብቻ ነው የደረሱት።

ሁቲዎች ሪያድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቢገልጹም፤ ሞክሀ ከተማን በተመለከተ አስተያየት አልሰጡም።

ሳዑዲ የደረሰባትን ጥቃት አውግዛለች። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የየመንን መንግሥት እንዲደግፉም ጥሪ አቅርባለች።

አራት የመንግሥት ምንጮች ለሮይተርስ እንደገለጹት የየመን ኃይሎች ወደ ሞክሀ ከተማ ተጠግተዋል። የሁቲ ተዋጊዎች እየሸሹ መሆኑንም ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የመንግሥት ምንጮች "ኃይላችን ድሁባብ የጦር ሰፈርን ተቆጣጥሯል። ከድሁባብ ወደ ባብ ኤል-መንዳብ የሚወስደውን መንገድም ቆርጧል" ብለዋል።

ከዚህ በፊት የየመን ጦር ድሁባብ አውሮፕላን ማረፊያን እንደተቆጣጠረ እና በአቅራቢያው ባለው ከተማ ያሉ የሁቲ አማጺያንን እንደከበበ ገልጿል።

በሁቲዎች የሚመራው ሚዲያ እንደዘገበው ከሆነ የመንግሥት ኃይሎች ወደ ከተማዋ አልተቃረቡም።

የየመን መንግሥት መዲናዋን ሰንዓን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ኦፕሬሽኖች መጀመራቸውን ይፋ አድርጓል።

ሰንዓ ከ12 ዓመታት በፊት የእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር ውላለች።

በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት መንግሥትን ለሚደግፉ ኃይሎች "የማያቋርጥ" ድጋፍ እየሰጠ እንደሆነ ገልጿል።

324 "ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው" ዒላማዎችን ማውደሙንም አስታውቋል።

የሳዑዲ ደጋፊ የሆኑት ቱርክ እና ፓኪስታን ትናንት ሪያድ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄዱ ሲሆን፤ በመካ ወታደራዊ ስምምነት አማካኝነት በአፋጣኝ በሳዑዲ አረቢያ ወታደሮች ለማሰማራት ወስነዋል።

በሰንዓ በሚገኙት ሳንሀን እና ሳዋን አካባቢዎች ሳዑዲ ባደረሰችው የአየር ጥቃት አንድ ታዳጊ ተማሪ ሴት እና አንዲት አዋቂ ሴት መገደላቸውን ሁቲ የሚያስተዳድረው አል ማሲራህ ዘግቧል።

የሁቲ ቃል አቀባይ መሐመድ አብዱል ሳላም "ሳዑዲ በርካታ ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው፤ ተጠያቂ መሆን አለባት" ብለዋል።

ሁቲ የሚያስተዳድረው የሰብዓዊ ድርጊት አስተባባሪ እንዳለው ከቅዱሳኑ ከተሞች መካ እና መዲና ውጭ ያሉ ከተሞች የአየር ክልል ደኅንነቱ የተጠበቀ አለመሆኑን ለዜጎች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ "ሁቲዎች ድንበር ተሻግረው በሳዑዲ ላይ የሚያደርሱት ጥቃት በጣም አሳሳቢ እና የግጭቱን መባባስ የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የየመን ፕሬዝዳንታዊ አመራር ምክር ቤት እሑድ ባወጣው መግለጫ፤ በይፋ የማጥቃት ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።

'የመን ዳውን' የተባለው ኦፕሬሽን በሁቲዎች በተያዙ አካባቢዎች ላይ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ራሺድ አል-አሚኒ የሰላም አማራጮች ውጤታማ ስላልሆኑ ሁሉም ኃይሎች "አገሪቱ ከሁቲ አሸባሪዎች ነጻ እስከምትወጣ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ" ጠይቀዋል።

ሁቲዎች በደቡብ ምዕራብ ታይዝ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ተራራማ ሥፍራ ቆርጠው በማለፋቸው መንግሥት እና ነዋሪዎችን ከብበዋል።

ሁቲዎች ሳዑዲ ለፈጸመቻቸው ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት፣ በሳዑዲ አራምኮ ነዳጅ ፋብሪካ የባለስቲክ ሚሳዔል እና ድሮን ጥቃት መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ከሪያድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ አራምኮ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ሁቲዎች ገልጸዋል።

የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ 'ቢቢሲ ቬሪፋይ' በሳተላይት ምሥል አማካኝነት እሑድ ዕለት ከአራምኮ እና ከኩሪያስ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ጥቁር ጭስ መውጣቱን ተመልክቷል።