ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቢቢሲ ማጣሪያ ያደረገባቸው የኤርትራ ወታደሮችን በትግራይ የሚያሳዩ ምሥሎች ምን ያመለክታሉ?
ረቡዕ ዕለት የኤርትራ ወታደሮች በአዲግራት ከተማ መታየታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን የተለያዩ ምሥሎችም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ በስፋት ተጋርተዋል።
ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከሆነ የኤርትራ ወታደሮች በአዲግራት ከተማ በኩል ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በጭነት ተሽከርካሪዎች እና በእግራቸው ሲያቋርጡ ታይተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የኤርትራ ወታደሮች ረቡዕ መስከረም 27/2019 ዓ.ም. ማለዳ ጀምሮ መታየታቸውን ይገልጻሉ።
የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ (ቢቢሲ ቬሪፋይ) በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ምሥሎች መካከል የተወሰኑት ምሥሎች ትክክለኛነታቸውን የቦታ እና የመልክዓ ምድር አመላካቾችን በመጠቀም ለማጣራት ሞክሯል።
ቢቢሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የኤርትራ ወታደሮች ናቸው በሚል የተሠራጩ ምሥሎችን ፈትሾ በጭነት መኪኖች እንዲሁም በእግራቸው ሲጓጓዙ የሚያሳዩት ምሥሎች በአዲግራት እና እዳጋ ሐሙስ አካባቢ መነሳታቸውን አረጋግጧል።
ቢቢሲ የተመለከታቸው ሦስት ምሥሎች ሲሆኑ በአንዱ ሁለት የኤርትራ ሠራዊትን የደንብ ልብስ በከፊል የለበሱ ሰዎች በዋና መንገድ ላይ አህዮች ሲነዱ ይታያል።
ቢቢሲ ረቡዕ ዕለት ያነጋገራቸው የአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች የኤርትራ ወታደሮች በከተማዋ አልፈው ወደ ደቡብ መቀለ መስመር ወዳለችው እዳጋ ሐሙስ ሲሄዱ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ሁለተኛው ምሥል የኤርትራ ሠሌዳ የለጠፈ ቢጫ ሲኖትራክ ላይ የተጫኑ ወታደሮች የሚታዩበት ሲሆን፣ ይህ ምሥል የተወሰደው በአዲግራት እና እዳጋ ሐሙስ መሆኑ ተረጋግጧል።
ሦስተኛው እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ሌላው ምሥል በቀይ የጭነት መኪና የተሳፈሩ ወታደሮች የሚታዩበት ነው።
ከእነዚህ ውጪ የ13 ሰከንድ ርዝመት ያለው ተንቀሳቃሽ ምሥል በድሮን የተመታ ነጭ የጭነት መኪናን ያሳያል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ የተመለከታቸው ፎቶዎቹ በአጠቃላይ የተነሱት ከመቀለ በሰሜናዊ አቅጣጫ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እዳጋ ሐሙስ ከተማ ላይ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
አህዮች እየነዱ በዋና መንገዱ ላይ የሚሄዱት እና ከፊል ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱት ሰዎች ደግሞ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚጓዙ ናቸው።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው አጭር ተንቀሳቃሽ ምሥል በአዲግራት ከተማ አቅራቢያ የተቀረጸ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
አንደኛው በድሮን ጥቃት የደረሰበት ጭነት መኪና ፊቱን ወደ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያዞረ በመሆኑ በተመታበት ወቅት ወደ መቀለ እየተጓዘ ነበር ለማለት ያስቸግራል።
ግጭትን የሚከታተለው አክሌድ ረቡዕ ምሽት ለሐሙስ አጥቢያ "የኤርትራ ወታደሮች እና የጦር መሣሪያዎቻቸው" በአዲግራት አካባቢ "በተደጋጋሚ የድሮን ድብደባ" እንደተፈጸመባቸው አስታውቋል።
"በርካታ የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል። አንዳንድ የኤርትራ የጭነት መኪኖችም ወድመዋል፤ አሁን በመንገድ ላይ አይታዩም" ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአዲግራት ነዋሪ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ተናግረዋል።
በአዲግራት የሚገኙ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው "ሌሊት ከፍተኛ ፍንዳታ" እንደሰሙ ገልጸዋል።
"በድሮን የተመቱ የኤርትራ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችንም አይቻለሁ" ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
ሦስተኛ የአዲግራት ነዋሪ ደግሞ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ሰሜን እያፈገፈጉ ያሉ ይመስል እንደነበርም ተናግረዋል።
የትጥቅ ግጭቶችን የሚሰንደው አክሌድ የኤርትራ ወታደሮች በዛላምበሳ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውን ጠቅሶ፣ በአዲግራት እና እዳጋ ሐሙስ መስመር እየተጓዙ ሳለ ጉአዳ በተባለ አካባቢ ከኢትዮጵያ መንግሥት የድሮን ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ገልጿል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑትን እናታለም መለሰ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ገልጸው የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቀው መውጣት አለባቸው ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በላይ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የኤርትራ ወታደሮች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ መሆናቸውን አሳውቀው ነበር።
ኤርትራ በበኩሏ ሠራዊቷ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቀው ገብተዋል የመባሉን ክሱ አስተባብላለች።
የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል የዓይን እማኞችን ምስክርነት "ኢትዮጵያ በጎረቤቷ ላይ ጦርነት ለመክፈት የምታደርገው ጥረት አካል ነው" ሲሉ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው መግባታቸው የተሰማው የትግራይ ክልልን ተቆጣጥረው የነበሩት እና በኤርትራ ይደገፋሉ የሚባሉት የህወሓት ኃይሎች ዋና ከተማዋን መቀለን ለቅቀው ከወጡ ከቀናት በኋላ ነው።
ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጋር የተሰለፉት "የትግራይ ሰላም ኃይሎች" አዛዥ ገብረእግዚአብሔር በየነ ለኤኤፍፒ የኤርትራ ጦር ከባድ መሣሪያዎችን ታጥቆ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን ተናግረዋል።
ከ1990-1992 ዓ.ም. በድንበር ይገባኛል ጦርነት የገጠሙት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ያላቸውን ዲፕሎማሲኣዊ ግንኙነት አቋርጠው ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸውን አድሰዋል።
የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የተዋጉ ሲሆን የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረምን ተከትሎ የአገራቱ ግንኙነት ሻክሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ሁለቱ አገራት ይፋ ወደ ወጣ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን የኤርትራ መንግሥት ህወሓትን እና ታጣቂ ኃይሎችን በመደገፍ የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ሲከስሱ ቢቆዩም ኤርትራ ግን ክሱን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አስር የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ከአዲስ አበባ ሲያባርር ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣለች።
ይህም ለ20 ዓመታት ተቋርጦ ከስምንት ዓመት በፊት መልሶ የተጀመረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንዲቋረጥ አድርጎታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ በተጨማሪ የግብፅ አንድ ዲፕሎማትንም ከግዛቱ ያባረረ ሲሆን፣ ካይሮም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደለች።