በዩቲዩብ ላይ የጤና ምክሮችን የሚሰጡ በኤአይ የተፈበረኩ ዶክተሮች ለምን አረጋውያንን ዒላማ አደረጉ?

የፎቶው ባለመብት, @Dr.Rafael Costa/YouTube
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ለበርካቶች የመረጃ ምንጭ በሆኑበት ዓለም ከዜና እና ታሪኮች አንስቶ ጥንቃቄ እስከሚፈልጉት የጤና ይዘቶች ድረስ የተሳሳቱ መረጃዎች ይቀርባሉ።
የ82 ዓመቷ አዛውንት ሴሊ ፌሬራም ዩቲዩብ እየተመለከቱ ሳለ ነበር አንድ ዶክተር ቀርቦ ፍራፍሬዎችን በመመገብ የዓይን ብርሃንን መጠበቅ እንደሚቻል ሲናገር የሰሙት።
ፌሬራ ዶክተሩ የሰጠው ምክር አሳማኝ እንደሆነ አስበው በትኩረት ነበር ሲከታተሉት የነበረው። ሆኖም የዩቲዩብ ገጹ ትክክለኛ የጤና መረጃዎች የሚቀርቡበት አልነበረም።
ዶክተሩም ቢሆን በገሃዱ ዓለም ላይ ያለ አይደለም። ድምጹም ሆነ ገጹ በሰውሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተፈጠረ ነው።
ምንም እንኳን ዩቲዩብ ቪዲዮው በኤአይ የተፈጠረ እንደሆነ ቢገልጽም፤ ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ተመልካቾችን የሳበ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶችም ጎርፈውለታል።
በዚህም ምክንያት ፌሬራ ትክክለኛ ዶክተር እየሰሙ እንደሆነ ነበር ያመኑት።
በእርግጥ ይህ የእርሳቸው ችግር ብቻ አይደለም። አንድ ምርመራ በኤአይ የተፈበረኩ ዶክተሮችን የሚጠቀሙ በፖርቹጋል ቋንቋ የሚተላለፉ 29 ገጾችን ለይቷል። እነዚህ የዩቲዩብ ገጾች 70 ሚሊዮን ዕይታዎችን ማግኘት ችለዋል።
እነዚህ ይዘቶች ተደራሽነታቸው በዓለም ዙሪያ ነው። ቢቢሲ ኒውስ ብራዚል፣ ፖርቹጊዝ ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒንዲ፣ ስፓኒሽ፣ ጣሊያንኛ፣ ጀርመንኛ ፣ ፖሊሽ እና ተርኪሽን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች በኤአይ የተፈጠሩ ዶክተሮችን በመጠቀም እንዴት ቪዲዮ መሥራት እንደሚቻል የሚያስተምሩ 50 የዩቲዩብ ገጾችን መለየት ችለዋል።
ይዘት ፈጣሪዎቹ ዒላማ ያደረጉት ቪዲዮዎችን ለማየት ብዙ ትርፍ ጊዜ እንዳላቸው እና የሚባሉትን ነገር ለመግዛት ገቢ አላቸው ብለው ያሰቡትን በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ነው።
ዩቲዩብን የሚያስተዳድረው ጉግል የማኅራዊ ሚዲያ መድረኩ መመሪያዎች በኤአይ የሚፈጠሩ ይዘቶች ላይም ተፈጻሚ እንደሚሆኑ እና ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ከሕክምና ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደሚከለክሉ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Celi Ferreira
ኤአይ በመጠቀም እንደዚህ ዓይነት ቪዲዮዎችን ለመሥራት የሚያስፈልገው ቀላል ቀመር ነው።
የዶክተሮች መለያ የሆነውን ነጭ ገዋን ማልበስ እና በዕለት ተዕለት የምንጠቀማቸው ምግቦች፣ መድኃኒቶች ወይም አረጋውያንን ለአደጋ የሚያጋልጡ ልምዶችን በተመለከተ ለስለስ ባለ ድምጽ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ ማድረግ ነው።
ከዚያም መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ዶክተሮች ሙሉ በሙሉ በኤአይ የተፈጠሩ ሲሆኑ በገሃዱ ዓለም ላይ የሉም። በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ያለምንም ፈቃድ የትክክለኛ ዶክተሮችን ፊት፣ ድምጽ ወይም ማንነት በመውሰድ እንዲመሳሰሉ በማድረግ በኤአይ የተፈበረኩ ናቸው።
ሁለቱም መንገዶች በተመልካቾች ዘንድ ብቁ ባለሙያዎች ጠቃሚ የሆኑ የጤና መረጃዎችን እየሰጡ ነው የሚል ሃሳብን ይፈጥራሉ።
በኤአይ የተፈበረኩ ዶክተሮችን በመጠቀም በፖርቹጋል ቋንቋ መልዕክት የሚያስተላልፉት 29 የዩቲዩብ ገጾች የተጋለጡት ኮንትሮል + ዜድ (CTR +Z) በተሰኘ የብራዚል የሚዲያ ድርጅት ነው።
ቢቢሲ ኒውስ ብራዚልም ተመሳሳይ ርዕስ የተሰጣቸው ሌሎች ገጾች መኖራቸውን እና ድግግሞሹን ለማየት ቪዲዮዎቹን ተመልክቷቸዋል።
በዚህም ከዩቲዩብ ገጾቹ ላይ ከተሰጡ 27 ሺህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል ፌሬራን አግኝቷቸዋል።
አብዛኞቹ አስተያየቶች በኤአይ ዶክተሮች የተሰጡ ምክሮችን ተከትሎ የቤት ውስጥ ሕክምናን መጀመራቸውን ወይም የተሰጣቸውን መድኃኒት ማቋረጣቸውን የሚገልጹ ከአረጋውያን የተሰጡ ግብረ መልሶች ናቸው።
አንዳንዶቹ ምክሮቹን ተከትለው የወሰዷቸውን እርምጃዎችም አጋርተዋል።
ከአስተያየቶቹ መካከል የ85 ዓመት እንደሆኑ የተገለጹ ግለሰብ የጨጓራ አሲድ እንዲቀንስ የሚሰጥ መድኃኒትን በስኳር ድንች እንደተኩ ይገልጻሉ።
በሌላ አስተያየት ደግሞ አንድ የ77 ዓመት ሴት ለሦስት ዓመታት ሐኪም ቤት እንዳልሄዱ በመጥቀስ የመርሳት በሽታን በተመለከተ የኤአይ ሐኪሞች ለሰጧቸው ምክር አመስግነዋል።
ቢቢሲ ኒውስ ብራዚል ባገኛቸውና የኤአይ ዶክተሮችን በመጠቀም ቪዲዮዎችን እንዴት መሥራት እንደሚቻል በዩቲዩብ በተላለፉ ትምህርቶች (ቲቶሪያል) አስተማሪዎቹ፣ የሚያስደነግጡ አርዕስትን እና ተመልካቾች አስቸኳይ የጤና አደጋ እየገጠማቸው እንደሆነ የሚገልጽ ጽሑፍን መጠቀምን ይመክራሉ።
እነዚህ ይዘት ፈጣሪዎች ከዩቲዩብም ተመልካቾች እና የኤሌክትሮኒክ መጽሐፍት እና በገጻቸው የሚተዋወቁ ምርቶችን በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ።
በብራዚል ተቀማጭነቱን ያደረገ ጆፍ ኮይምብራ የተባለ ዩቲዩበር እንዳለው ይዘት ፈጣሪዎቹ በወር እስከ 5 ሺህ 816 ዶላር ገንዘብ ሊያገኙ ይችላሉ።
በሌላ ቪዲዮ ደግሞ በጣም አስደንጋጭ የድምጽ ቅላጼን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። ለዚህም 'ወደ አልጋ ከመሄዳችሁ በፊት' ፣ 'እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ!' ፣ 'በተኛችሁበት ላለመሞት ተጠንቀቁ' እና ሌሎች ተመሳሳይ ምሳሌዎች ቀርበዋል።
ቢቢሲ ብራዚል ዩቲዩበሩን ካነጋገረው በኋላ ከቪዲዮዎቹ አንደኛው ለሕዝብ እንዳይቀርብ ታግዷል።
ኮይምብራ በሰጠው መግለጫ የኤአይ ቪዲዮዎቹ የእርሱ ይዘቶች እንዳልሆኑ እና ከሌሎች የወሰዳቸው ምሳሌዎች መሆናቸውን ገልጿል።
ይዘቶቹ የጤና ባለሙያዎችን የሚተኩ ሳይሆኑ በኤአይ የሚሠሩ መረጃ የሚሰጡ ይዘቶችን በተመለከተ ትምህርት እንደሚሰጥ የገለጸው ኮይምብራ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩን ሕግ እና ሌሎች መመሪያዎችን የመጣስ ፍላጎት እንደሌለው አስረድቷል።
"ርህራሔ የለም"
ቢቢሲ አሳሳቢ የሆኑ የጤና ጉዳዮችን እና መድኃኒቶችን ሊተኩ የሚችሉ ተፈጥሯዊ ሕክምናዎችን ለማስተዋወቅ በጣም ታዋቂ የሆነ ብራዚላዊ ሐኪም ገጽታን ያለ ፈቃዳቸው የተጠቀሙ ቢያንስ አምስት የዩቲዩብ ገጾችን አግኝቷል።
ዶ/ር ሄሊዮ ብራሲሲሌሮ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋ ሰብስክራይበሮች ያሉት እና ከተከፈተ ረዥም ጊዜ የሆነው ገጽ ለዩቲዩብ ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ለሳኦ ፖሎ ፖሊስም ክስ አቅርበዋል።
ገጹ ተወዳጅነታቸውን ያለአግባብ ከመጠቀሙ ባሻገር ስጋት የፈጠረባቸው አረጋውያን ተመልካቾች ምክሩን በመስማት መድኃኒቶቻቸውን መውሰድ ሊያቆሙ ይችላሉ በየሚለው ነው።
"ማንም ይፍጠረው ማን፣ ይህ ርህራሄ የሌለው ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስ ብራዚል ተናግረዋል። "በዚህ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት መሞከር በአረጋውያን ላይ የሞት አደጋ ሊያስከትል ይችላል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በሳኦ ፖሎ አልበርት ኢንስቲን ኢስራኤላት ሆስፒታል የጨጓራ እና የአንጀት ሐኪም የሆኑት ጄሚ ዛላድክ ጊል በበኩላቸው በእነዚህ ሐሰተኛ ምክሮች ምክንያት ህሙማን ውጤታማ ያልሆኑ መድኃኒቶችን በመውሰድ የጤና ችግራቸውን ሊያባብሱ ወይም የሚድኑበተን ጊዜ ሊያራዝሙ ይችላሉ ብለዋል።
"የሚያስፈልገው የሆነ ነገር ሁሉንም ችግራችሁን ይፈታል የሚሉ ቪዲዮች ሳይሆኑ፤ ትክክለኛ የሕክምና ምርመራ እና የተሻለ የህክምና ሥርዓት ነው" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, YouTube/Dr. Hélio – MedInformações
የብራዚል የሕግ ባለሙያዎችም ይዘት ፈጣሪዎች ዶክተሮችን ለወንጀል እንዲጋለጡ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ዩቲዩብን የሚያስተዳድረው ጉግል በበኩሉ ቪዲዮ የሚጋራበት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ ሁሉም ሕጎች በኤአይ በሚሠሩ ይዘቶችም ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ገልጿል።
ኩባንያው ጨምሮም መለያ ማድረጉ ተመልካቾች ይዘቱ መቼ እንደተለወጠ ወይም እንደተሠራ እንዲያውቁ ያደርጋል ብሏል።
ቢቢሲ ኒውስ ብራዚል 'ኮንትሮል+ዜድ' የተሰኘው የሚዲያ ተቋም የሰበሰባቸውን የዩቲዩብ ገጾች በተመለከተ ኩባንያውን ካነጋገረ በኋላ በአጠቃላይ 41 ሚሊዮን ዕይታ ያላቸውን የተወሰኑትን የዩቲዩብ ገጾች አስወግዷል።
ሴል ፌሬራ በኦንላይን የሚመለከቷቸው ይዘቶችን በመለየት ረገድ የተሻሉ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ።
"በእኔ ዕድሜ ኮምፒዩተር መጠቀም ላይ ጎበዝ እንደሆንኩ ነበር የማስበው፣ ሆኖም አሁንም ድረስ የትኛው እውነተኛ እና የትኛው ኤአይ እንደሆነ ማወቅ አልችልም" ብለዋል።




































