የፋኖ እንቅስቃሴ “በአማራ ክልል ብቻ የተወሰነ አይደለም” ያለው አፋብን በአበሽጌው ጥቃት ላይ ተሳትፎ እንደሌለው ገለፀ
በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ጥቃት የፈፀሙ ታጣቂዎች የአፋብን አባላት እንዳልሆኑ የድርጅቱ ቃል አቀባይ አስረስ ማረ ዳምጤ ለቢቢሲ ተናገሩ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ውስጥ ሰኞ መስከረም 4/2018 ዓ.ም. በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና መታገታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ካነጋገርናቸው መካከል አንዱ፣ 15 ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን እንዳረጋገጡም አስረድተዋል።
ከተገደሉት በተጨማሪ እስከ 20 የሚደርሱ ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸውንም የገለፁት ነዋሪዎቹ፣ ጥቃቱ የተፈፀመባት ዋልጋ ተብላ የምትጠራ አነስተኛ ከተማ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው መፈናቀላቸውንም አክለው ገልፀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፣ በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስፍራው መላኩን እና ሥራውን አጠናቆ ሪፖርት ገና አለማቅረቡን ገልፀዋል።
ጥቃት ፈፃሚዎቹ ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በበኩሉ በአበሽጌው ጥቃት ላይ ተሳትፎ የለኝም ብሏል።
የአፋብን ቃል አቀባይ አስረስ ማረ ዳምጤ፣ የድርጅቱ እንቅስቃሴ "በአማራ ክልል ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ" ገልፀው፣ "አበሽጌ ወረዳ በንፁሃን ላይ ተፈፀመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ግን እንደ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ኃላፊነት አንወስድም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአበሽጌም ይሁን በሌላ አካባቢ "ራሳቸውን ለመከላከል የሚደራጁ በፋኖነት ራሳቸውን የሚጠሩ ወጣቶች እንዳሉ እናምናለን" ሲሉም አክለዋል።
ለአብነትም “ወለጋ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው በድርጅታችን ‘ቼይን ኦፍ ኮማንድ’ [የዕዝ ሰንሰለት] ስር ያለ፣ ነገር ግን ንፁሃንን ለማጥቃት ሳይሆን ከመከላከያ ሠራዊቱ፣ ገዳ ኮማንዶ ከሚባለው ጨፍጫፊ ኃይል እና በተለያየ ስም እና መልክ ከተደራጀ የአገዛዙ ኃይል ጋር የሚታገል ንፁሃንን የሚጠብቅ የራሱ ‘ቼይን ኦፍ ኮማንድ’ እና አመራር ያለው ከድርጅታችንም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ነው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ፣ የአበሽጌውን "ጥቃት ፈፀሙት ተብሎ ክስ እየቀረበባቸው ያሉ ሰዎች በድርጅታችን 'ቼይን ኦፍ ኮማንድ' [የዕዝ ሰንሰለት] ስር የምናውቃቸው አይደሉም" በማለት አፋብን እውቅና የሰጠው ታጣቂ ቡድን በስፍራው አለመኖሩን አስረድተዋል።