ቀጥታ, በኦሮሚያ ክልል የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ታጣቂዎች ትናንት እሁድ ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተፈራ ደሴ መገደላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ። በወረዳው የምትገኘው አኖ ቀሬ ቀበሌ ሊቀ መንበር አስፋወሰን ኃይሌን ጨምሮ ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኦሮሚያ ክልል የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ

    የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ተፈራ ደሴ

    የፎቶው ባለመብት, Paartii Badhaadhinaa Damee Dagam

    በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ታጣቂዎች ትናንት እሁድ ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተፈራ ደሴ መገደላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

    በጥቃቱ በወረዳው የምትገኘው አኖ ቀሬ ቀበሌ ሊቀ መንበር አስፋወሰን ኃይሌን ጨምሮ ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።

    የዞኑ የፀጥታ መዋቅር ምንጮች ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ እንደተናገሩት፣ ዋና አስተዳዳሪው የተገደሉት እሁድ ከሰዓት በኋላ ሲሆን ጥቃት የተፈጸመው በደገም ወረዳ አኖ ቀሬ ቀበሌ ውስጥ ነው።

    በዕለቱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር ምንጮቹ አስረድተዋል። የቀበሌ ሊቀ መንበሩን ጨምሮ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናቱ ላይ ለተከፈተው ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) ታጣቂዎችን ነው። ታጣቂ ቡድኑ እስካሁን ስለ ጥቃቱ መረጃ ያለው ነገር የለም።

    የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የአቶ ተፈራን መገደል በተመለከተ ከክልሉ መንግሥትም ይሁን ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የተሰጠ አስተያየት የለም። ቢቢሲ ከዞኑ ዋና አስተዳደሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ባለልጣናትን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

    በየካቲት 2017 ዓ.ም. ሱሉልታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አበበ ወርቁ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።

    መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው እና 'ሸኔ' ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በወቅቱ በወጣው መግለጫው ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።

    በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ላይ ደግሞ የዞኑ የውሃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስዩም አበራ፣ የዞኑ አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን እጄታ እና የዞኑ የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ግዛው ተገድለዋል።

    ጥቅምት ላይ በተመሳሳይ የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ንጉሤ ኮሩን ጨምሮ ከ45 በላይ ሰዎች የሚሆኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረው ነበር።

  2. የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ ወደ ቴህራን ከማምራታቸው በፊት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ተነጋገሩ

    የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር

    የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር ሰኞ ዕለት ወደ ቴህራን ከማምራታቸው በፊት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር መነጋገራቸውን ሦስት የሮይተርስ ምንጮች ተናገሩ።

    የጦር አዛዡ ከትራምፕ ጋር የተነጋገሩት አሜሪካ ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ ቴህራን ላይ ለመጣል እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ነው።

    ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ተጠይቆ ወዲያውኑ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

    ሙኒር እና ትራምፕ በምን ጉዳዮች እንደተወያዩ ግልጽ አይደለም።

    ፓኪስታን እና ኳታር ቴህራን እና ዋሺንግተንን በማደራደር ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

    በተያያዘ ዜና የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ማክሰኞ ዕለት የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር ቡሳይዲ ወደ ቴህራን እንደሚመጡ ተናግረዋል።

    ባጋይ ጨምረውም ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ገልጸዋል።

    ቃል አቀባዩ የኦማኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት በሁለትዮች ጉዳይ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ከመናገር ውጪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    አክለውም ሁለቱ አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት የሚያደርጉት ውይይት “የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት ያጠናክራል” ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ የኦማኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ከፓኪስታኑ ጦር አዛዥ ጉብኝት ጋር ምንም የሚያይዛቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

  3. ማራዶና “በእግዜር እጅ” ግብ ያስቆጠረባት ኳስ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠች

    ኳሱ እአአ በ2022 በ2.37 ሚሊዮን ዶላር ተሸጦ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የምስሉ መግለጫ, ኳሱ እአአ በ2022 በ2.37 ሚሊዮን ዶላር ተሸጦ ነበር

    ዲያጎ ማራዶና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1986ቱ የዓለም ዋንጫ በእጁ ግብ ያስቆጠረባት ኳስ በጨረታ 3.3 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠች።

    ከጨዋታው በኋላ ማራዶና ለጋዜጠኞች “በጥቂቱ በማራዶና ጭንቅላት እና በጥቂቱ በእግዜር እጅ” ግብ ማስቆጠሩን ተናግሮ ነበር።

    ማራዶና በዚያው የዓለም ዋንጫ ላይ ከበረኛው ውጪ አምስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አልፎ “የክፍለ ዘመኑ ግብ” የተባለለትን ጎል አስቆጥሯል።

    ቅዳሜ ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ለጨረታ የቀረበው ኳስ 10 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ተብሎ ቢጠበቅም በ3.3 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል።

    አጫራቹ ማይክ ፕሮቬንዛሌ ከጨረታው በፊት ለሮይተርስ የዜና ወኪል “ይህ ልዩ የሆነ ዕቃ ነው። እስካሁን ከተገኙት እጅግ አስፈላጊ የእግር ኳስ ዕቃዎች አንዱ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

    የ1986ቱን የዓለም ዋንጫ የዳኙት ቱኒዚያዊው አሊ ቢን ናስር ኳሱን ከጨዋታው በኋላ በመውሰድ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ጠብቀው አቆይተውታል።

    እአአ በ2023 በጨዋታው ላይ ጥቅም ላይ የዋለ ብቸኛው ኳስ መሆኑን በፊርማቸው ያረጋገጡ ሲሆን ገለልተኛ አጣሪዎችም እውነት መሆኑን መስክረዋል።

    ቢን ናስር እአአ በ2022 ኳሱን 2.37 ሚሊዮን ዶላር ሸጠውታል።

    እአአ በ2023 አዲሱ የኳሱ ባለቤት ለጨረታ ቢያቀርበውም የታሰበለትን ያህል ዋጋ ባለማውጣቱ ሳይሸጥ ቀርቷል።

    በዚሁ ጨዋታ ላይ ማራዶና የለበሰው ቲ ሸርት እአአ በ2022 በ7.1 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸጧል።

  4. በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ድሮን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ታግቶ የቆመ ነዳጅ ጫኝ መርከብን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መግደሉን የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ጥቃቱ የተፈጸመው በሶማሊያ ኑጋል ክልል፣ ጎዶብጂራን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት መርከቧ ኤምቪ ሉቱፍ (MV Lutuf) የምትባል ሲሆን ከቀናት በፊት በባሕር ላይ ወንበዴዎች ታግታ ወደ አካባቢው መምጣቷን ተናግረዋል።

    የካሜሮንን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልበው ይህች መርከብ መዳረሻዋ ቱርክ ነበር ተብሏል።

    ቢቢሲ የመርከቧን መዳረሻም ሆነ ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

    መርከቧ ከዚህ ቀደም ጋርማል የሚባል አካባቢ ቆማ የነበረ ሲሆን በአካባቢው በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አራት ሰዎች ሞተዋል።

    የድሮን ድብደባውን ማን እንደፈጸመው በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። የሶማሊያ መንግሥትም ጥቃቱን አላወገዘም።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘው የተገደሉት የባሕር ላይ ወንበዴዎች አይደሉም ብለው ነበር።

    የአካባቢው ባለሥልጣናት የድሮን ጥቃቱን የፈጸመችው ቱርክ ልትሆን ትችላለች ቢሉም የቱርክ ባለሥልጣናት ግን ለቢቢሲ ምንም መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    አብዲፋታህ ዩሱፍ የተባለ የዐይን እማኝ ማንነታቸው የማይለይ ስምንት በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን መመልከቱን ተናግሯል።

    “ስምንት በጥቃቱ የተቃጠሉ አስከሬኖች አይቻለሁ።” ብሏል።

    የጎዶብጂራን ከንቲባ የሆኑት ኬነን ኦማር ለመበስበስ የተቃረበ አስከሬን ቆይቶ በመገኘቱ የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ ደርሷል ብለዋል።

    የሟቾቹ አስከሬን ሰኞ ይቀበራል ተብሎ ይጠበቃል።

    የፑንትላንድ የመረጃ ምክትል ሚኒስትር ቢሌ ቀቦውሳዴ ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች በመጣራት ላይ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል ከባሕር ላይ ዘረፋ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች እንደገና እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ የውጭ አካላት እየሞከሩ ሊሆን እንደሚችል የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ገልጸዋል።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት መርከቦቻቸው በባሕር ላይ ዘራፊዎች ሊያዙ ወይም ሊታገቱ የሚችሉ የመርከብ ባለቤቶች፣ ኦፕሬተሮች፣ የዋስትና ሰጪ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት ከዘራፊ ቡድኖች ጋር በቀጥታ ድርድር እንዳያደርጉ ወይም የማስለቀቂያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ አሳስበዋል። እንዲህ ዓይነት ክፍያዎች የወንጀል ቡድኖች ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ግብዓትና ማበረታቻ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

  5. ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኤም- 23 አማፂያን በሰላም ንግግር ማዕቀፎች ላይ ተስማሙ

    የኤም 23 አማፂያን በጎማ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኤም 23 አማፂያን በጎማ

    የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት እና በሩዋንዳ የሚደገፈው የኤም 23 አማፂ ቡድን የሰላም ድርድር ፍኖተ ካርታ ላይ ከስምምነት ደረሱ።

    በስዊትዘርላንድ ለአምስት ቀናት የተወያዩት ሁለቱ ወገኖች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት እና ግጭት ለመፍታት የሚያስችል ድርድር ለማድረግ” እንዲሁም የተኩስ አቁሙን ስምምነቱን አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችል አካል ለማቋቋም ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

    ፍኖተ ካርታው በ2025 በአሜሪካ አስተባባሪነት በተፈረመው የሰላም ማዕቀፍ ሥር ለሚደረጉ ውይይቶች የጊዜ ሰሌዳ ያስቀምጣል።

    ነገር ግን በኤም 23 ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች፣ የታሳሪዎች አለመፈታት እና የፖለቲካ ማሻሻያዎች የሚደረጉበትን ጊዜ ጨምሮ በርከት ያሉ ጉዳዮች አሁንም በቡድኖቹ መካከል ላለመግባባት ምክንያት ናቸው።

    በድርድሩ ላይ ኤም 23፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት፣ ኳታር፣ አሜሪካ፣ የቶጎ ሪፐብሊክ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና አስተናጋጇ ስዊትዘርላንድ ተሳትፈዋል።

    "ተፈላሚ ወገኖች የዶሃ ማዕቀፍ ስምምነትን ተከትሎ የተጣለባቸውን ግዴታዎችና ኃላፊነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል አካል ለማቋቋም ተስማምተዋል።" ሲል መግለጫው አክሏል።

    ግጭቱ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በአጎራባች ሩዋንዳ መካከል ካለው ውጥረት ጋር በቅርበት የተያያዘ ነው።

    ሩዋንዳ የፀጥታ ስጋት እንደሆነ የምትቆጥረውን ኤፍዲኤልአር የተባለውን ነፃ አውጪ ኃይል ዲሞክራቲክ ኮንጎ ማፍረስ እንዳልቻለች ገልጻለች።

    ዲሞክራቲክ ኮንጎ ታጣቂ ቡድኑን ኤፍዲኤልአርን እንደማትደግፍ አስተባብላ ሩዋንዳም ኤም-23ን በወታደሮችና በጦር መሳሪያዎች እንደምትደግፍ ትከሳለች።

    በጥር 2025 ኤም23 ጎማን እና ሁለት የአየር ማረፊያዎችን ጨምሮ ሲቆጣጠር ግጭቱ ተባብሶ ነበር።

    በአስርት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።

    ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ በሆኑ ኮልታን እና ሌሎች ማዕድኖች የበለፀገች ናት።

  6. አሜሪካ በቴህራን ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ስትገልጽ፣ ኢራን በባሕረ ሰላጤው የሚካሄዱ የነዳጅ ግብይቶችን ለማቋረጥ ዛተች

    የኢራን ባንዲራ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    አሜሪካ፣ የኢራንን የንግድ አጋሮች ዒላማ ያደረጉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ሰኞ ዕለት ለመጣል ስትዘጋጅ፤ "እስካሁን ከተደረጉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛው የፋይናንስ ጥቃት" ብላ በጠራችው እርምጃ ኢራንን አስፈራራች።

    ኢራን በበኩሏ “የምጣኔ ሃብት ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ” በባሕረ ሰላጤው የሚካሄዱ የትኛውንም የነዳጅ ግብይቶች እንደምትዘጋ አስጠንቅቃለች።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ሰኞ ዕለት ረፋዱ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    አሜሪካ አሁን ለመጣል እየተዘጋጀች ያለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ እስላማዊ አብዮቱ እአአ በ1979 ከተመሰረተ ወዲህ አጋጥሞት የማያውቅ ነው ተብሏል።

    ቤሴንት በፋይናንሻል ታይምስ ላይ እሁድ ዕለት በታተመላቸው ጽሑፍ ላይ “[ሰኞ] ማለዳ አንድ ወሳኝ የኢኮኖሚ ጥቃት ይጀመራል፤ ይህም በአንድ ተቀናቃኝ ላይ እስካሁን ከተሰነዘሩት ሁሉ እጅግ የከፋው የፋይናንስ ጥቃት ነው።” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሳምንታት የተኩስ ልውውጥ ያላደረጉ ቢሆንም ለስድስት ወር የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም ተጨባጭ የሆነ ንግግር አላደረጉም።

    እሁድ ዕለት የኢራን የደኅንነት ኃላፊ አዲሱን የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚደግፉ አገራት በእስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን ላይ ”ጦርነት እንዳወጁ” እንቆጥረዋለን ሲሉ ዝተዋል።

    ሞህሰን ረዛኢ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ትራምፕ እርምጃ መውሰድ ከፈለጉ ተመጣጣኝ ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ ዝተዋል።

    ኢራን በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ዒላማ እንደምታደርግም ዝተዋል።

    ቤሰንት በፋይናንሻል ታይምስ ላይ በወጣው ጽሑፋቸው ላይ ዝርዝር እርምጃዎችን ሳይሰጡ የኢራን ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ላይ በመሳተፍ “የሚያባብሉ” ያሏቸውን “ፈሪ አገራትን” አሜሪካ ዒላማ እንደምታደርጋቸው አስታውቀዋል።

    “ይህን ማስቀጠል የሚያስከትለውን ውጤት ቢያጤኑት መልካም ይሆናል” ሲሉም በፋይናንሻል ታይምስ ላይ ጽፈዋል።

    ኢራን በበኩሏ ከአሜሪካ ሊሰነዘርባት ለሚችል የኢኮኖሚ ማዕቀብ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች።

    የኢራን ከፍተኛ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሞህሰን ረዛኢ፣ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “የኢኮኖሚ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ በሆርሙዝም ሆነ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ውስጥ ከየትኛውም ሥፍራ አንድም የነዳጅ ጠብታ ወደ ውጭ አይላክም” ብለዋል።

    “ኢራን፣ የትኛውም አገር በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው የኢኮኖሚ ጦርነት ውስጥ ቢሳተፍ ወይም ድጋፍ ቢሰጥ፣ ድርጊቱን እንደ ጦርነት ተግባር ትቆጥረዋለች” ሲሉም አክለዋል።

    ቤሰንት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የነዳጅ ምርት ከኢራን የምትገዛውን ቻይና ከአሜሪካ ጋር እንድትተባበር አሳስበው ነበር።

    በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እንድትከተል ጥሪ በማቅረብ "ማዕቀቦች እና ጫናዎች ችግሩን ለመፍታት አይረዱም።" ብለዋል።