የየመን ሁቲዎች ወደ ቀይ ባሕር የሚያስገባውን ባብ ኤል መንደብን ለመቆጣጠር መቃረባቸው ተዘገበ
የኢራን አጋር የሆኑት የየመን ሁቲ አማፂያን ወደ ቀይ ባሕር ለመግባት ወሳኝ በሆነው የባብ ኤል መንደብ መተላለፊያ ወሽመጥ ላይ ወሳኝ ተጽእኖ ለማሳረፍ እየተቃረቡ መሆናቸው ተዘገበ።
በዓለም ላይ ከሚገኙ እጅግ አስፈላጊ የንግድ መርከቦች መተላለፊያ መስመሮች መካከል አንዱ የሆነውን የባሕር ላይ መተላለፊያ ለመቆጣጠር መቃረባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል አራት የየመን መንግሥት ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሁቲዎች በየመን ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ ከሚመራው ጥምር ጦር እና ድጋፍ ከሚያገኙ ኃይሎች ጋር እያካሄዱ ያለው ውጊያም ወደ ሙሉ ጦርነት እንደገና የመመለስ አዝማሚያ እያሳየ ነው።
ምንጮቹ እንዳሉት፣ ሁቲዎች ከባብ ኤል መንዳብ ወሽመጥ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ የየመን የባሕር ዳርቻ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እየተቃረቡ ሲሆን፣ መላውን የየመን የቀይ ባሕር ዳርቻዎች ለመያዝ ወታደራዊ ግፊት እያደረጉ ነው።
ባለፉት ቀናት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የየመን መንግሥት ውስጥ ያሉ በሳዑዲ አጋሮች እና በሁቲዎቹ መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተባብሷል።
ይህም በኢራን ግጭት ውስጥ ሁለተኛ የጦርነት ግንባር ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ምንጮች አቅርቦት ላይ ስጋት እየፈጠረ ነው።
የባብ ኤል መንዳብ ወሽመጥ ሰርጥ በቀይ ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚገኝ ከሕንድ ውቅያኖስ ወደ ቀይ ባሕር መግቢያ እና መውጫ ነው። ይህ ቦታ በአረብ ባሕረ ገብ ምድር ላይ የምትገኘውን የመንን ከጅቡቲ እና ከኤርትራ ጋር የሚለይ ነው።
አሁን ወሽመጡን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ያሉት ሁቲዎች ሰሜናዊ የየመንን አብዛኛውን ክፍል እንዲሁም በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸውን የአገሪቱን ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎች ባብ ኤል መንደብን መያዝ ከቻሉ በቀታናው ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር ይችላሉ።
ወሽመጡ ከፍተኛ ነዳጅ እና ጋዝ ከሚመረትበት የባሕረ ሰላጤው አገራት የሚመጣ ድፍድፍ ነዳጅ ወደ ሱዌዝ ቦይ ለመድረስ ወደ ቀይ ባሕር የሚያስገባ በር ነው። እንዲሁም ወደ እስያ አገራት የሚያመሩ የተለያዩ ምርቶች እና ሸቀጦች የጫኑ ግዙፍ መርከቦችም ይተላለፉበታል።
የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ጥረታቸው ተሳክቶ ባብ ኤል መንደብን ለመቆጣጠር ወሳኝ የሆኑ ግዛቶችን መያዝ ከቻሉ የሚፈጥሩት ተጽእኖ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፈጠረችው ቀውስ ቀጥሎ ሌላ አሳሳቢ ሁኔታን ሊፈጥሩ ይችላሉ።