የኢራን ጦር በኩዌት በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
የኢራን ጦር ሠራዊት በኩዌት የሚገኙ የሳተላይት መገናኛ ሥርዓቶችን፣ የመሳሪያ ማከማቻ ቦታዎችን እና የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ማቆሚያ መጠለያዎችን ዒላማ አድርጎ መምታቱን አስታወቀ።
የኢራን ጦር ሐሙስ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፣ በኩዌት በሚገኘው አህመድ አል ጃበር የጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ ቁልፍ ወታደራዊ ዒላማዎችን በሚሳኤሎች እና ከፍተኛ የፍንዳታ አቅም ባላቸው ድሮኖች መምታቱን ገልጿል።
የኢራን ጦር በፈጸመው ጥቃት በጦር ሰፈሩ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት “በመገናኛ ሥርዓቶች እና በተዋጊ አውሮፕላኖች መጠለያ ላይ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።
በተመሳሳይ መግለጫው የኢራን ጦር፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሚገኘው አል ሚንሃድ የጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ “የአሜሪካ ጦር ኃይሎች መገኛ እና የራዳር ሥርዓቶችም” መምታቱን አስታውቋል።
የኢራን ሠራዊት መግለጫውን ከማውጣቱ ከአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የኩዌት ጦር ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ ከኢራን የተነሱ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን ለመከላከል የአየር መከላከያ ሥርዓቶቿን በተጠንቀቅ ማቆሙን አሳውቆ ነበር።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በኢራን ላይ መፈጸም የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በአጸፋው በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት እየፈጸመች መሆኗን አስታውቃለች።




















