አሜሪካ በብሪታንያ ከሚገኘው የጦር ሠፈሯ ሁሉንም ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿን አወጣች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በፀረ-ሽብር ፖሊሶች ምርመራ እየተደረገበት ባለው የብሪታንያው 'ራፍ ፌይርፎርድ' የተባለ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ውስጥ የነበሩ ሁሉንም የቦምብ አውሮፕላኖቿን ከስፍራው ማንሳቷ ተገለፀ።
ከአንድ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን እሁድ ዕለት የተሰጠ መግለጫ፣ በጦር ሠፈሩ የነበሩት ሁሉም ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ወደ አሜሪካ መደበኛ ጣቢያዎቻቸው መመለሳቸውን አረጋግጧል።
አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በምን ምክንያት እንደሆነ አልገለፀችም። ሆኖም እርምጃው የተወሰደው መስከረም 17 ቀን በግሎስተርሻየር በሚገኘው ወታደራዊው አየር ማረፊያ አካባቢ ሦስት "አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች" ስለመታየታቸው መረጃ የደረሰው ፖሊስ ምርመራ ከጀመረ በኋላ ነው።
በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ወንዶች በአየር ማረፊያው አካባቢ ከተያዙ በኋላ በዋስትና ተለቅቀዋል። ቀጥሎም የዩኬ እና ኢራን ዜግነት ያለው ስድስተኛ ተጠርጣሪ ተይዞ እንደሌሎቹ በዋስ ተለቋል።
የለንደን ምንጮች ዋሽንግተን የወሰነችው እርምጃ ከራፍ ፌይር ፎርድ ክስተት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል መባሉን አልተቃወሙም።
ውሳኔው ፖለቲካዊ ሳይሆን የአሜሪካ ጦር ለብሪታንያ አቻው በማሳወቅ የወሰነው ወታደራዊ ውሳኔ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
ከክስተቱ ጥቂት ቀናት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም፣ በጦር ሰፈሩ በነበረው ሁኔታ ውስጥ የኢራን እጅ እንዳለበት "ጠንካራ ማሳያዎች" እንዳሉ ተናግረው የነበረ ሲሆን ዝርዝር ማብራሪያ ግን አልሰጡም። ቴህራን በበኩሏ በክስተቱ ውስጥ ምንም ሚና እንዳልነበራት አጥብቃ አስተባብላለች።
በወታደራዊው ጦር ሰፈር ከነበረው ሁኔታ ጋር በተገናኘ በመጀመሪያው ዕለት እድሜያቸው ከ23 እስከ 25 ዓመት የሆኑ አምስት ወንዶች ተይዘው ነበር። በአሜሪካ የአየር ኃይል ወደሚተዳደረው የጦር ሰፈር አቅጣጫ ሦስት ተሽከርካሪዎችን እያሽከረከሩ ሲጓዙ የነበሩት አምስቱ ግለሰቦች በለንደን የሚኖሩ የዩኬ ዜጎች ናቸው።
ግለሰቦቹ የፈንጅ ጥቃት እና የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በመዘጋጀት ተጠርጥረው የተያዙ ቢሆንም፣ ፖሊስ "በልምድና በስትራቴጂ ላይ የተመሠረተ የምርመራ ውሳኔ" ሲል በገለጸው ውሳኔ በዋስትና ተለቅቀዋል።
ስድስተኛው ተጠርጣሪ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ለሽብር ድርጊት በመዘጋጀት ተጠርጥሮ ሐሙስ ዕለት ለንደን ውስጥ ነበር የተያዘው። እሱም እንዲሁ ቅዳሜ ዕለት በዋስትና መለቀቁን የፀረ-ሽብር ፖሊስ አረጋግጧል።
ራፍ ፌይርፎርድ ለአስርት ዓመታት የአሜሪካ አየር ኃይል የኦፕሬሽን ጣቢያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
ባለፉት ወራት ውስጥ፣ በኢራን ላይ ለሚደረጉ ጥቃቶች የጦር ሰፈሩን ለመጠቀም አሜሪካ ያቀረበችው ጥያቄ በዩኬ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከዚህ ጣቢያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲነሱ ታይተዋል።
"በኢራን ግዛት ላይ ለሚፈፀም ጥቃት የሚያገለግል ማንኛውም የጦር ሰፈር የወታደራዊ ኃይሎቼ ሕጋዊ ዒላማ ይሆናል" ስትል ኢራን ሐምሌ ወር ላይ አስጠንቅቃ ነበር።
የራፍ ፌይርፎርዱን ክስተት ተከትሎ ስድስተኛው ተጠርጣሪ ከመታሰሩ በፊት፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ጉዳዩ በግልጽ የውጭ ተዋናይ እጅ እንዳለበት ያሳያል" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ አምስቱ ሰዎች በዋስትና መለቀቃቸው "አስገርሞኛል" ብለዋል።
"ስለ እነሱ ሁሉንም ነገር እናውቃለን፤ እኛ ብንሆን ኖሮ አንለቃቸውም ነበር" ያሉት ትራምፕ፣ ያም ሆኖ በዚህ ጉዳይ ላይ ዩኬ ከአሜሪካ ጋር በቅርበት ስትሰራ እንደነበር አክለው ገልፀዋል።




































