ልጁን መግደል እንደሚፈልግ ለቻትጂፒቲ በመናገሩ የታሰረው አባት

የስልክ ስክሪን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ ራስን ማጥፋትን እና አካላዊ ጉዳትን የሚመለከት ይዘት አለው

"እኔን እና ልጄን ከገደለ 50 ሺህ እንደሰጠምው ነገርኩት። ነገር ግን ልጅ መግደል አልፈልግም አለ። ሰዎችን የመግደል ፍላጎት ከምን የመነጨ እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ። ሰዎች ሲሰቃዩ ማየት ያስደስተኛል።"

ይህ አንድ ብራዚላዊ አርሶ አደር ከቻትጂፒቲ ጋር ያደረገው የመልዕክት ልውውጥ ነው። ከሁለት ወራት በላይ ከቻትጂፒቲ ጋር አውርቷል።

ፖሊስ እንደሚለው አርሶ አደሩ የስምንት ዓመት ልጁን ለመግደል አስቦ ነበር። አባት ልጁን ገድሎ፣ ሌሎች ሰዎች ላይ ጥቃት አድርሶ ራሱን ለማጥፋት ማቀዱ ተገልጿል።

ቢቢሲ የተመለከታቸው እነዚህ የመልዕክት ልውውጦችን ተከትሎ ግለሰቡ ታስሯል።

ቻትጂፒቲን የፈጠረው ኦፕንኤአይ የመልዕክት ልውውጡን በተመለከተ ለአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ እና ለብራዚል ባለሥልጣናት መረጃ ከሰጠ በኋላ የ36 ዓመቱ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የግለሰቡ ጠበቃ እንደሚሉት ግን ከቻትጂፒቲ ጋር "ትርጉም የሌለው ነገር ያወራው" ደንበኛቸው ወንጀል አልፈጸመም።

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ለፖሊሶች፣ ፍርድ ቤቶች እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ፈታኝ ሆነዋል።

የኤአይ ቻትቦች ወንጀል ሳይፈጸም በፊት አደገኛ ነገር ቢያስተውል ምን ያድርግ? የሚለውን ላይም ጥያቄ አስነስቷል።

የልጁን ደኅንነት ለመጠበቅ ስንል ስሙን የማንጠቅሰው ብራዚላዊ አባት ሰኔ ላይ በሳዎ ጋብርዬል ዳ ፓልሀ ገጠራማ አካባቢ ታስሯል።

የብራዚል የፍትሕ ሚኒስቴር የበይነ መረብ ወንጀል ክፍል ጉዳዩን ለፖሊስ ካስታወቀ ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለው።

የኤስፒሪቶ ሳንቶስ የበይረ መረብ ወንጀል ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ብሬኖ አንድሬ "ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ የሰጠነው ከባድ ስለሆነ እና አባትየው ልጁን የሚገድልበትን ቀን ስላስቀመጠ ነው" ይላሉ።

ግለሰቡ ልጁን ለማሳደግ የሚውል ገንዘብ ለእናቱ ከመስጠት በዘለለ ግንኙነት እንደሌላቸው ኃላፊው ገልጸዋል።

አባት በዚህ ክፍያ ተበሳጭቶ ግድያውን እንዳሴረ መርማሪዎች ይገምታሉ።

ቤቱ ሲፈተሽ ምንነቱ ያልታወቀ ፈሳሽ የያዙ አራት ጠርሙሶች እና የተቋጠረ ገመድ ተገኝተዋል። ገመዱ ግለሰቡ ራሱን ለማጥፋት ማሰቡን እንደሚያሳይ መርማሪዎች ተናግረዋል።

ከቻትጂፒቲ ጋር የተደረገው የመልዕክት ልውውጥ

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግለሰቡ በትምህርት ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ፖሊሶች ላይ ጥቃት ስለማድረስ ቻትጂፒቲን መጠየቁ ተገልጿል።

ቢቢሲ የተመለከተው አንድ የጽሑፍ መልዕክት "አደንዛዥ ዕፅ መሸጫ ቦታ ሄጄ አራት ወንጀለኞችን ብገድል በከተማው ዝነኛ እሆናለሁ። ከዚያም አንድ ወይም ሁለት ፖሊሶች እገድል እና በሰላም እሞታለሁ" ይላል።

ሌላኛው መልዕክት "ሽጉጥ ገዝቼ ፖሊሶች ላይ ለመተኮስ እያሰብኩ ነው። ስተኩስባቸው ይገድሉኛል። ይህም ለእኔ መልካም እና ጥሩ ነው" ይላል።

ሪሲን የተባለውን መርዛማ ፈሳሽ ጨምሮ ሌሎችም መርዛማ ፈሳሾችን በተመለከተ ከቻትጂፒቲ መረጃ ሲጠይቅ እንደነበር መርማሪዎች ደርሰውበታል። ቻትጂፒቲ ደኅንነትን ለመጠበቅ የተዘረጋ አሠራር ቢኖረውም ይሄንን ጥሶ ለማለፍ ሞክሯል።

"ፖሊስ ቤቱ ሲደርስ ያገኘው በመተግበሪያው ላይ ካሉ እና ወደ እኛ ከመጡ ነገሮች ጋር የሚዛመዱ ናቸው" ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

ግለሰቡ ልጁ ላይ ጉዳት ለማድረስ እንደማይፈልግ በመግለጽ አስተባብሏል።

ለ54 ቀናት ከታሰረ በኋላ ምርመራው ስለተጓተተ ተለቅቋል። ፖሊስ ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን፤ እስካሁን ክስ አልተመሠረተም።

ግለሰቡ ላይ የተወሰዱ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች የግለሰቡ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ ክትትል ማድረግ እና ከልጁ እንዲሁም ከልጁ እናት ጋር እንዳይገናኝ ማገድን ይጨምራሉ።

መርማሪዎች እንደገለጹት የተጠርጣሪው ስልክ ላይ ፍተሻ እየተደረገ ይገኛል።

ዕቅዱን ለመፈጸም ተጨባጭ እርምጃ ወስዶ እንደሆነ ለማወቅም የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት እየተጠበቀ ነው።

ይህም ከቻትጂፒቲ ጋር በተነጋገረው መሠረት ቅጥረኛ ገዳይ ለማግኘት ሞክሮ እንደሆነ ማወቅን ያካትታል።

እነዚህ ማስረጃዎች ከተገኙ ግለሰቡ ጥቃቱን ከማቀድ ባለፈ ወደ ትግበራ ማምራቱን የሚያሳዩ እንደሆኑ መርማሪዎች ጠቁመዋል።

በብራዚል ሕግ ወንጀል ተፈጽሟል የሚባለው ድርጊቱ ሲከናወን ነው።

የግለሰቡ ጠበቃ ፔድሮ ፓውሎ ፔሲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ የወንጀል ድርጊት አልተፈጸመም።

"ከኤአይ ጋር ማውራት እና ትርጉም አልባ ነገር መናገር ወንጀል ከሆነ ሁሉም ሰው እስር ቤት ይገባል" ብለዋል።

ማስረጃ የማግኘት ፈተና

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ተጠቃሚዎችን ለፖሊስ ሪፖርት የሚያደርጉባቸው ሁኔታዎች ውስን ናቸው።

ነሐሴ ላይ ኦፕንኤአይ ፍሎሪዳ የሚኖር የ25 ዓመት ግለሰብን በተመለከተ ለኤፍቢአይ ሪፖርት አድርጓል። ግለሰቡ የቀድሞ ፍቅረኛውን ለመድፈር እና ለመግደል አቅዶ ለቻትጂፒቲ መንገሩን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የበይረ መረብ ወንጀል ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ብሬኖ እንደሚናገሩት፤ በአካባቢያቸው በኤአይ አማካኝነት ጥቆማ ሲሰጥ የአርሶ አደሩ ጉዳይ የመጀመሪያው ነው።

ከዚህ በፊት በመላው ብራዚል ሦስት መሰል ጥቆማዎች ተሰጥተዋል።

"ሰዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው ወንጀል ስለ መሥራት መረጃ አስሰው እንደሆነ ለማወቅ የሚደረገው ጥረት በፖሊስ ምርመራ አዲስ ዘርፍ ነው" ይላሉ ኃላፊው።

እንዲህ ያሉ ጥቆማዎች ከኤአይ ኩባንያዎች ሲሰጡ ከምርመራው ሒደት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

አንደኛው ጥያቄ የመልዕክት ልውውጦች በፍርድ ቤት ማስረጃ ሆነው ይቀርባሉ? የሚለው ነው።

መርማሪዎች እንደሚሉት ኦፕንኤአይ የሰጠው መረጃ ግለሰቡ የላከውን መልዕክት እንጂ ቻትጂፒቲ የሰጠውን ምላሽ አያካትትም።

ጠበቃ ማሪያ ፈርናንዴዝ እንደሚሉት፤ ምላሹን አለማግኘት ማስረጃ በማቅረብ ሒደት ውስጥ ክፍተት ይፈጥራል። ምክንያቱም የመልዕክት ልውውጡ ዐውድ መታወቅ ይገባዋል።

"ቁንጽል ጽሑፍ መሆን የለበትም። አርትኦት ሊደረግበትም አይገባም። ሙሉው የመልዕክት ልውውጥ መቅረብ ይገባዋል" ይላሉ።

በግለሰቡ እና በቻትጂፒቲ መካከል የተደረገው ሙሉ የመልዕክት ልውውጥ፤ ቻትቦቱ ለተጠቃሚው ንግግር ምላሽ እየሰጠ ነው? ወይስ ውይይቱን እየመራ? የሚለውን ለመወሰን ይረዳል።

ኦፕንኤአይ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ የቻትጂፒቲ ምላሽ ለምን እንዳልተካተተ ከቢቢሲ ቢጠየቅም በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም።

ነገር ግን "ሌሎች ሰዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ታማኝ መረጃ" ሲገኝ ለሕግ አካል እንደሚሰጥ ገልጿል።

በመጋቢት 2026 በፍሎሪዳ በኦፕንኤአይ ላይ የወንጀል ምርመራ ተከፍቷል። ምርመራው በፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርስቲ ሁለት ሰዎች ላይ በተፈጸመው ግድያ ቻትጂፒቲ ያለውን ሚና ይመለከታል።

ኦፕንኤአይ ክሱን አስተባብሏል። የተሰጠው መረጃ ማንኛውም ሰው የሚያገኘው እንደሆነ እና ቻትቦቱ ሕገ ወጥ ድርጊትን እንዳላበረታታ ገልጿል።

ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ

ጠበቃዋ ማሪያ እንደሚሉት፤ ለጥቃት የተጋለጠው ልጅ መሆኑ ከኤአይ ኩባንያው ጥቆማ እንዲሰጥ ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን ክስን በኤአይ መረጃ ላይ ብቻ መመሥረት መለመድ የለበትም ይላሉ።

"ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሚረዳው መንገድ ከሄድን ሁሉም ሰው ላይ ምርመራ ሊደረግ ነው" ሲሉም ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያስረዳሉ።

እውነተኛ ስጋት እና ሰዎች ስሜታዊ ሆነው ወይም ምኞታቸውን ለመግለጽ የሚያደርጉትን ንግግር መለየት የሚቻልበት አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ጠበቃዋ ይመክራሉ።

የዲፒታል ሕግ ባለሙያዋ ፓትሪሽያ ፔክ እንደሚሉት፤ የብራዚሉ ክስተት ኤአይ "በተከታታይ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ተመርኩዞ አደገኛ ባህሪን መለየት የሚችል" አሠራር እንዳለው የሚያሳይ ነው።

ይህም የኤአይን አካሄድ መለወጡን ይጠቁማል።

"የሚደረገው ንግግር ከምናባዊ ዕሳቤ ወጥቶ አደጋ የሚያስከትል፣ የጥቃት ውጥን ያካተተ እና ሰለባ ያለው ሲሆን ከሥነ ምግባር እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ከሕግ አንጻር እምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ይላሉ።

ነገር ግን ከልክ ባለፈ ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት ያስጠነቅቃሉ።

"ለኤአይ ጥቅም ላይ የሚውል የሥነ ምግባር መርኅ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር የሚውል 'የሞራል መመሪያ' መሆን የለበትም። ጉዳት ሲኖር ብቻ ነው መተግበር የሚገባው" ይላሉ።

ስጋትን ችላ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ የሚጠቅሱት ባለሙያዋ ከመጠን ያለፈ ክትትል መደረግ እንደሌለበትም ያስጠነቅቃሉ።