ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ወዴት እንደተወሰዱ እንደማያውቁ እና ለደኅንነታቸው እንደሰጉ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገለጹ
ከስምንት ቀናት በፊት በትግራይ ኃይሎች ከመኖሪያ ቤታቸው የተወሰዱት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ አሁን ላይ የት እንዳሉ እንማያውቁ የቢቢሲ ምንጮች አስታወቁ።
ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ቤተሰብ የሆኑት እኚህ ምንጭ እንደተናገሩት፤ ላለፉት ቀናት ኤችዜድ በሚባል ሆቴል ውስጥ "ተይዘው" ነበር።
ትናንት መስከረም 22፣ 2019 ዓ. ም. ከሰዓት 11 ሰዓት ገደማ ላይ የትግራይ የፀጥታ ኃይል አባላት ወደ ሆቴላቸው ሄደው "ልንወስዳችሁ ነው" እንዳሏቸው የቤተሰብ አባላቶቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"እነ ታደሰ ግን እኛ ከዚህ አንሄድም አሉ" ሲሉ የተናገሩት ቤተሰባቸው፤ የፀጥታ አካላቱ "መንግሥታችን ወዳዘጋጀላቸው እና ደኅንነታቸው ወደሚጠበቅበት ቦታ እንወስዳቸዋለን" የሚል ምላሽ እንደሰጡ ገልጸዋል።
20 የሚሆኑ የፀጥታ አባላት ወደ ሆቴሉ እንደሄዱም አክለዋል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ አሁን ላይ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አስረድተዋል።
ለሁለት ዓመት የቆየውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ከአቶ ጌታቸው ረዳ ተረክበው ለአንድ ዓመት ከመሩ በኋላ ሥልጣናቸው ለተጨማሪ ዓመት መራዘሙን ተከትሎ በህወሓት መሪዎች አስተዳደራቸው እንዲፈርስ መደረጉ ይታወሳል።
ላለፉት ወራት "በቁም እስር" ላይ እንደነበሩ የተገለጸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በትግራይ ኃይሎች ከመያዛቸው በፊት ጠባቂዎቻቸው "እንደተቀየሩ" እና ቤተሰባቸውም "ወደ ውጭ መውጣት" እንዳልቻለ ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
ትናንት ወደ ሆቴላቸው ላመሩት የፀጥታ ኃይሎች ከዚያ "እንደማይሄዱ" ቢገልጹም "ከሌሊቱ 5፡30 ተመልሰው ሄደው ከሆቴሉ አስወጥተው" እንደወሰዷቸው የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።
"የሆቴል መኝታ ክፍሎቻቸውን በር ሰብረው ነው ገብተው ያስወጡዋቸው" ብለዋል።
እስካሁን ወዴት እንደወሰዱዋቸው እንደማይታወቅ ጠቅሰውም "ቤተሰቡ በከፍተኛ ጭንቀትና ስጋት ውስጥ ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
ከሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር ተይዘው በሆቴል ውስጥ እንዲቆዩ ከተደረጉት መካከል የትግራይ ኃይሎች የመረጃና ደህንነት ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ እና የትግራይ ኃይሎች የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ኢሳያስ ታደሰ እንደሚገኙበት ምንጮቹ ጨምረው ገልፀዋል::
ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የተገለጸው፤ የህወሓት ኃይሎች መቀለን ለቅቀው መውጣታቸው በተዘገበበት ወቅት ነው።
የፈረንሳይ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) የክልሉን ጋዜጠኛ እና ነዋሪዎችን ጠቅሶ ይህንን የዘገበው የትግራይ ኃይሎች መቀለን ለቅቀው እየወጡ መሆኑ ከተሰማ እና የፌዴራል ኃይሎች ወደ ከተማዋ እየተቃረቡ መሆናቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር በመሆን ከትግራይ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ያለው 'የትግራይ የሰላም ኃይሎች' በበኩሉ፤ የክልሉን ዋነኛ አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠሩን መግለጹን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ቤተሰብ ባለፉት ቀናት "ጠዋት እና ማታ ምግብ ያደርሱላቸው እንደነበር" እና አሁን ላይ ያሉበት እንደማይታወቅ እንዲሁም ለደኅንነታቸው እንደሰጉ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሌተናንት ጄነራል ታደሰ ቤተሰብ "ለኤርትራ መንግሥት ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ የሚል ስጋት" እንዳላቸው ገልጸዋል።
አክለውም "በቂም በቀል ተነሳስተው ሊጎዱዋቸው ይችላሉ የሚል ስጋትም ገብቶናል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ኤርትራን እና ግብፅን መክሰሳቸው አይዘነጋም። ሁለቱም አገራት ክሱን አስተባብለዋል።
በሌላ በኩል የተራድኦ ድርጅት ሳተላይት ስልክ በመጠቀም ለቢቢሲ መረጃ የሰጡ ግለሰብ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ በፓሊስ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት እና በጦር ጉዳተኞች ሆስፒታል ዘረፋ ተፈጽሟል" ብለዋል።
ቢቢሲ ይሄንን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው አንድ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማዋ የፀጥታ ኃይሎች ባለመኖራቸው "የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረቶች ለዘረፋ ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ስጋት" እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሌላ ነዋሪም "በከተማዋ ሥርዓት አልበኝነት ሊስፋፋ እንደሚችል እና ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ" ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደምም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የረድዔት ድርጅት ምንጭም የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ሙሉ በሙሉ መውጣታቸውን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰብ "ሕዝቡ በየመንደሩ ተደራጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ ነው። የከተማው ወጣቶች ያለፍርሃት የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሰላም ኃይል ለመቀበል ወደ አደባባይና ወደ ጎዳናዎች እየወጡ ናቸው" ብለዋል።
የህወሓት አመራሮች "የሕሙማን ማመላለሻ አምቡላንሶች ሳይቀር ነው ይዘው የወጡት" ብለዋል።
ህወሓት ከስድስት ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመሆን "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመስረቱን ይፋ ካደረገ በኋላ በአፋር እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ጦርነት ተቀስቅሷል።
የጦርነቱ መቀስቀስን ተከትሎ በትግራይ ክልል የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
በትግራይ ክልል የተከፈቱ የባንክ አካውንቶችም በመዘጋታቸው ነዋሪዎች መቸገራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።