ቀጥታ, የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ 14 መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ተሾሙላቸው

ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ አዲስ አስተዳደራቸውን ያዋቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ ለ14 የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ሾሙ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ዘጠኝ ባለሥልጣናት ደግሞ ባሉበት ኃላፊነት ይቀጥላሉ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ከኢራን ጋር ስምምነት ማድረግ "የሚመርጡት ነገር አለመሆኑን" ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ድርድር "በጣም ጥሩ" እየሠሩ መሆኑን ገልጸው ስምምነት ግን የሚመርጡት ውጤት እንዳልሆነ ተናገሩ።

    "በኢራን ስምምነት ላይ በጣም ጥሩ እየሰራ ነው። ስምምነቱ እኔ ማድረግ የምፈልገው ነገር እንዳልሆነ አስባለሁ፤ ነገር ግን ጦርነቱን ለማቆም ማንኛውንም ነገር ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው" ሲሉ ትራምፕ በቴክሳስ ሳን አንቶኒዮ በተካሄደው የምርጫ ዘመቻ ላይ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

    “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በፍፁም አይኖራቸውም” ሲል አክለዋል።

    ትራምፕ በጋዛ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጥቀስ ዊትኮፍን “ታላቅ ተደራዳሪ” እና “አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችን ያደረገ” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር የተደረገው ጦርነት በቅርቡ እንደሚቆምም ተናግረዋል።

    “ጦርነቱ ያበቃል፤ ይህም በጣም በቅርቡ ይሆናል። በጣም በቅርቡ መሆን አለበት” ካሉ በኋላ ኢራንን “የወደቀች አገር” በማለት ገልጸዋታል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት መገናኛ ብዙኃን ዋይት ሐውስ ከኅዳሩ ምርጫ በፊት በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በሚመለከት ፔንታጎን አማራጮችን እንዲያዘጋጅ መጠየቁን ከዘገቡ በኋላ ነው።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ቴህራን በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ በሚሳኤልእና በድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም ምላሽ ሰጥታለች።

    በተጨማሪም የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ የባህርወሽመጥን ዘግታለች።

    አሜሪካ እና ኢራን በሰኔ ወር በአደረዳሪዎቻቸው በኩል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ሁለቱ አገራት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።

  2. በአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ የደረሰው ጉዳት ከተነገረው በላይ መሆኑን ኢራን አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ መከላከያ ኃይላቸው 81 የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ከጥቅም ውጭ አድርጓል የሚለውን ሪፖርት በመጠቀስ የደረሰው ጉዳት ከተነገረው በላይ ነው አሉ።

    አራጋቺ ሐሙስ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ለአሜሪካ ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት በኢራን ጦርነት ዘመቻ ወቅት 81 ጦር አውሮፕላኖች በጦርነቱ መጥፋታቸው ወይንም መውደማቸው ይገልጻል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች ያሉበትን ሁኔታ ለመፈተሽ ሴናተሮች ያቀረቡት ትኣቄ ተቀባይነት አላገኘም።

    “በግንቦት ወር የኮንግረስ የምርምር አገልግሎት የኢራን ጦር ኃይሎች 42 የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ማውደሙን ይፋ አድርጎ ነበር። አሁን 81 ደርሷል” ሲሉ ጽፈዋል።

    “ትክክለኛው የደረሰው ጉዳት ግን ከዚህም የባሰ ነው። ማስረጃ? አሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ደህንነታቸው የተጠበቀ ናቸው ያላቸውን ጦር ሠፈሮች ላይ ሴናተሮች ምልከታ እንዲያደርጉ አልፈቀደም” ሲሉ አጋራቺ አብራርተዋል።

    አራጋቺ በኤክስ ልጥፋቸው ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ ምርምር አገልግሎት ያወጣውን ሪፖርት ፎቶ አንስተው አጋርተዋል።

    ሪፖርቱ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 81 የጦር አውሮፕላኖች መጥፋታቸው ወይንም መውደማቸውን ዘርዝሯል።

    ሪፖርቱ የተዘጋጀው ከወጡ የዜና ዘገባዎች፣ የአሜሪካ መከላከያ እና ሴንቲኮም እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስቴር ቁጥጥር ቢሮ ያወጧቸው ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ እንደሆነ ተጠቅሷል።

    በሪፖርቱ ላይ የተቀመጠው ቁጥር ሊቀየር እንደሚችል ተገልጿል።

    ከየካቲትመጨረሻ 2026 ጀምሮ ኢራን በሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን እና ኦማን በሚገኙ ከ 20 በላይ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት እና የጦር ሰፈሮች ላይ በሚሳኤሎች እና ድሮኖች ጥቃት ሰንዝራለች።

  3. በአዲሱ ሹመት ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት ሚኒስትሮች እነማን ናቸው?

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ዕጩ የካቢኔ አባሎቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስሹመዋል።

    በዚህም በቀደመው ካቢኔያቸው የነበሩ ሚኒስትሮች ባሉበት የቀጠሉ እና ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት የተዘዋወሩ ሲኖሩ በርካታ አዳዲስ ሚኒስትሮችን አካተዋል።

    በቀደመው ካቢኔ ውስጥ ከነበሩት ሚኒስትሮች መካከል ከአስር የሚበልጡት ቦታቸውን ለአዲስ ተተኪዎች ለቅቀዋል። ከመካከላቸውም የተወሰኑት በሌላ ኃላፊነት የተሾሙ ሲሆን የበርካቶቹ መዳረሻ ግን እስካሁን አልታወቀም።

    በአዲሱ የሚኒስትሮች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት ባለሥልጣናት እነ ማን ናቸው?

    1. አሕመድ ሽዴ የገንዘብ ሚኒስትሩ የነበሩ፣ አሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

    2. ሙፈሪያት ካሚል፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር የነበሩ፤ አሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

    3. አብርሃም በላይ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር የነበሩ፣ አሁን የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽነር

    4. ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ

    5. ጫልቱ ሳኒ፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር የነበሩ

    6. መላኩ አለበል፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩ

    7. ዓለሙ ስሜ፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር የነበሩ

    8. ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ

    9. በለጠ ሞላ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩ

    10. ሃብታሙ ተገኝ፣ የማዕድን ሚኒስትር የነበሩ

    11. ካሳሁን ጎፌ፣ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የነበሩ

    እነዚህ ሚኒስትሮች በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ባይካተቱም በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ በሚያደርጓቸው ሹመቶች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

  4. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ዘጠኝ ባለሥልጣናት ባሉበት ኃላፊነት ይቀጥላሉ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ መስከረም 28፣ 2019 ዓ. ም. በሰጡት ሹመት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ዘጠኝ ባለሥልጣናት ባሉበት ኃላፊነት ይቀጥላሉ።

    ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን፤ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ይቀጥላሉ።

    በተጨማሪም ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፣ አዲሱ አረጋ የግብርና ሚኒስትር፣ ሃና አርኣያሥላሴ የፍትሕ ሚኒስትር በመሆን በኃላፊነታቸው ይቀጥላሉ።

    ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጤና ሚኒስትር፣ ዐይንዓለም ንጉሤ የገቢዎች ሚኒስትር እና ሰላማዊት ካሳ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ይቀጥላሉ።

    ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አስተዳደራቸውን አዋቅረዋል።

  5. የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ 14 መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ተሾሙላቸው

    ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ አዲስ አስተዳደራቸውን ያዋቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ ለ14 የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ሾሙ።

    ዛሬ መስከረም 28/2019 ዓ.ም. አቶ ሙሳ አደም የሰላም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ ሱልጣን ወሌ (ዶ/ር) የመስኖ እና ቆላማ ሚኒስትር ሆነዋል።

    መሐመድ እድሪስ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የገንዘብ ሚኒስትር ሆነዋል።

    በተጨማሪም ያስሚን ወሀቢረቢ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር፣ ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል።

    አወሉ አብዲ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር፣ በረከት ፍሰሐጽዮን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ሆነዋል።

    ዓለምፀሐይ ጳውሎስ የማዕድን ሚኒስትር፣ ሳዳት ነሻ የሎጀስቲክስ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

    በተጨማሪም ሻዊት ሻንካ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ፍሬሕይወት ታምሩ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ መሐመድ አብዱራህማን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር እንዲሁም አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነዋል።

  6. ሁቲዎች በሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያዎች ባደረሱት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    ሁቲዎች ለሁለት ቀናት በሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎች ባደረሱት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    በየመን ተባብሶ የቀጠለው ውጊያው ሳዑዲ ላይ ጥቃት ወደማድረስ ተሻግሯል።

    የሳዑዲ አረቢያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንዳለው በአብሀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ፣ 28 ሰዎች ተጎድተዋል።

    በሪያድ በሚገኘው ንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፣ ስምንት ሰዎች ተጎድተዋል።

    የሁቲ አማጺያን ለጥቃቶቹ ኃላፊነቱን ወስደዋል። በሳዑዲ የሚደገፈው የየመን መንግሥት እና ሁቲዎች ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።

    በሁለቱ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥቃት የደረሰው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 6 እና 7 መሆኑ ተገልጿል።

    የተገደሉት ሁለት ሞሮኳዊ ሴቶች እና አንደ የአልጄርያ ዜጋ ናቸው።

    አብሀ አውሮፕላን ማረፊያ ከየመን ጋር ባለው ድንበር አቅራቢያ ይገኛል። በንጉሥ ኻሊድ አውሮፕላን ማረፊያ ሱዳናዊ መገደሉም ተገልጿል።

  7. አሜሪካ በቀጣይ ቀናት በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኑ ተዘገበ

    ፔንታጎን በቀጣይ ቀናት ውስጥ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ሁለት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    አክሲዮስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባለፉት ቀናት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ኢራን ላይ “ከፍተኛ ኦፕሬሽን” ለማከናወን እንዲዘጋጅ ከፔንታጎን ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

    አትላንቲክ መጽሔት ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ባወጣው ልዩ ዘገባ መሠረት፤ ከአሜሪካ የግማሽ ዘመን ምርጫ አስቀድሞ የኢራን ዒላማዎችን መምታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ፔንታጎን እንዲፈልግ ከዋይት ሀውስ ትዕዛዝ ተላልፏል።

    የፔንታጎን ትዕዛዝ ጥቃቱ የሚጀመርበትን ትክክለኛ ቀን እንዳላስቀመጠ እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱ የአክሲዮስ ዘገባ ያሳያል።

    የአክሲዮስ የአሜሪካ እና እስራኤል ምንጮች እንዳሉት ከሆነ ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ እና ከእስራኤል ምርጫ አስቀድሞ ጥቃቱ ሊፈጸም ይችላል።

    የአሜሪካ ምርጫ ኅዳር መባቻ ላይ የሚከናወን ሲሆን ከዚህ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የእስራኤል ምርጫ ይካሄዳል።

    አክሲዮስ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በኢራን ላይ የሚፈጸሙ ኦፕሬሽኖች በአገሪቱ የኃይል አቅርቦት፣ መሠረተ ልማት እና የኒውክሌር ተቋማት ላይ የሚደርስ መጠነ ሰፊ ጥቃትን ያካትታሉ።

  8. በኬንያ በኢቦላ ከሞተው ግለሰብ ጋር ንክኪ የነበራቸው ከ50 በላይ ሰዎች እየተፈለጉ ነው

    በኬንያ በኢቦላ ከሞተው ግለሰብ ጋር ንክኪ የነበራቸው 10 ሰዎች ለይቶ ማቆያ ሲገቡ ሌሎች በርካታ ሰዎች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው።

    በተጨማሪም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ ኬንያ ከተጓዘው ግለሰብ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሌሎች 57 ሰዎች እየተፈለጉ ነው።

    ላለፉት ሰባት ዓመታት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይኖር የነበረው ኬንያዊ በአገሪቱ በኢቦላ የሞተ የመጀመሪያው ሰው ነው።

    የአፍሪካ በሽታ ቁጥጥር እና ክትትል ኃላፊ ጂን ኬስያ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ግለሰቡ የታመመው ከወር በፊት ሲሆን፤ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና ሲሰጠው ነበር።

    ሟቹ መጀመሪያ ላይ በመኪና ኡጋንዳ፣ ካምፓላ ገብቶ ወደ ናይሮቢ ደግሞ በአውሮፕላን ገብቷል። ያሳለፍነው ቅዳሜ በአውሮፕላን ማረፊያ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ነበር ሆስፒታል የገባው።

    በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተስፋፋው የኢቦላ ዓይነት ክትባት ያልተገኘለት ቡንዲቡግዮ ዝርያ ነው።

  9. በሩሲያ የወረርሽኝ ተመራማሪዋ መሞቷን ተከትሎ ትራምፕ ከፑቲን ጋር ሊነጋገሩ ነው

    በሳይቤሪያ በሚገኝ የወረርሽኝ ምርምር ማዕከል ውስጥ የቤተ ሙከራ ባለሙያ የሆነች ሩሲያዊት መሞቷን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ሊያነጋግሩ ነው።

    “እስካሁን ጥልቅ ንግግሮች ተደርገዋል” ያሉት ትራምፕ፤ ከፑቲን ጋር ስለሚኖራቸው ውይይት ነገ ሐሙስ መረጃ ሊሰጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው በዕቅድ የተያዘ የስልክ ጥሪ አለመኖሩን አስታውቀዋል።

    ሩሲያ በዓለም ጤና ድርጅት አሠራር መሠረት የባለሙያዋን መሞት እንዳስታወቀች ተናግረዋል። መገናኛ ብዙኃን እያወጡት ያለው ዘገባ “ሐሰተኛ” መሆኑንም ገልጸዋል።

    አሜሪካ ሩሲያ ተጨማሪ መረጃ እንድትሰጣት በይፋ ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ልካለች።

    ቃል አቀባዩ ግን ስለቀረበው ጥያቄ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

    የ28 ዓመቷን ተመራማሪ ሞት በተመለከተ ሩሲያ ምርመራ እንደከፈተች አስታውቃለች። ከባለሙያዋ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በበሽታ አለመያዛቸው ተረጋግጧል።

    የአሜሪካየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ክስተቱ የሳንባ ምች ወረርሽኝመስፋፋትን ሊያስከትልይችላል በሚል ስጋት ዋሽንግተን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች እንደምትገኝ ተናግረዋል። ሆኖም አሁን ላይ ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለአክለዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ሩሲያ መረጃ በግልጽ እንድታቀርብ ጠይቋል።

    ተመራማሪዋ የሞተችው "ምክንያቱ ባልታወቀ የሳንባ ምች" መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ ከሥራ ጋር የተያያዙ "ምንም ዓይነት ረቂቅ ሕዋሳት" በተወሰደው የሟቿ ናሙና ውስጥ እንዳልተገኙም ይፋ ተደርጓል።

    ለበሽታው የተጋለጠችው ለምርምር የተዘጋጀውን በበሽታው ውሕድ የተሞላ የቤተ ሙከራ ቱቦ ከሰበረች በኋላ አሊያም ወረርሽኙ በተፈጥሮ በዱር አይጦች መካከል የሚገኝበት አካባቢ ካደረገችው የመስክ ጉዞ በኋላ እንደሆነ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

  10. ሩቢዮ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ለመድረስ “በርካታ” ዕድሎች አምልጧታል አሉ

    የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ረቡዕ ዕለት ኢራን ከአሜሪካ ጋር በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ከስምምነት ለመድረስ “በርካታ” ዕድሎች እንዳመለጧት አስታወቁ።

    ለሰባት ወር ከዘለቀው ጦርነት በኋላ በቴህራን እና በዋሺንግተን መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር ለውጥ ሳያመጣ ቆይቷል።

    ሩቢዮ ግሪክን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት “ኢራን ከእኛ ጋር በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ከስምምነት ለመድረስ የተገኙ በርካታ ዕድሎችን መጠቀም አልቻለችም” ብለዋል።

    በሁለቱ ወገኖች መካከል ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ በአደራዳሪዎች የሚደረጉ ጥረቶች ውጤት አላመጡም።

    ለድርድሩ መስተጓጎል አንዱ ምክንያት የአሜሪካ ወሳኝ ጥያቄ የሆነው የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ እንዳትችል ማድረግ የሚለው ነው።

    ሩቢዮ ይህንን ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ኢራን የምታበለጽገውን ዩራኒየም በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ መስማማት አለባት ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

    ቫንስ በወቅቱ ለሰባት ወራት የዘለቀውን ግጭት ለመፍታት የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት ኢራን የዩራኒየም ማበልጸግ ሥራዋን "ትርጉም ባለው ደረጃ” ለመቀነስ መስማማት አለባት ብለው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምነት ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ከተስማማች የማዕቀብ እፎይታ ጊዜ ለመስጠት ተስማምተዋል የሚለውን አስተባብለው ነበር።

  11. እስራኤላውያን በሐማስ የተፈጸመውን ጥቃት ሦስተኛ ዓመት እያሰቡ ነው

    ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት ጥቃት የፈጸመበት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ እስራኤል ውስጥ እየተካሄደ ነው።

    መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል በሐማስ በተፈጸመው ጥቃት በግምት 6,000 የሚሆኑ የቡድኑ ታጣቂዎች የጋዛን ድንበር አልፈው ወደ እስራኤል ከገቡ በኋላ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል፤ 251 ሰዎችን ደግሞ አግተው ወስደዋል።

    ይህንንም ተከትሎ በእስራኤል እና በሐማስ ላይ ጋዛ ውስጥ ባካሄደችው ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ ከ74 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ይገልጻል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም አኃዞቹ በአጠቃላይ ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምናል።

    በጋዛ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ከአንድ ዓመት በፊት የመጨረሻዎቹን የእስራኤል ታጋቾችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ ያስቻለው በአሜሪካ ሽምግልና የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም፣ በየቀኑ ለማለት በሚያስችል ደረጃ በጋዛ ላይ የሚፈጸሙት የእስራኤል ጥቃቶችን ቀጥለዋል።

    እስራኤል ባካሄደችው ዘመቻ ምክንያት ከጋዛ 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ አብዛኛው ተፈናቅሏል፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ የጋዛ ክፍልም በፍርስራሽ ተሸፍኗል።

    በእስራኤላውያን በኩል በሐማስ የተፈጸመውን ጥቃት ለመከላከል ባለመቻላቸው የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂነት ሊወስዱ ይገባል ወይስ አይገባም የሚል ጥያቄ አሁንም አልተመለሰም።

    በጦርነቱ አብዛኞቹ የሐማስ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ጋዛ ውስጥ እና በሌሎች አገራት ውስጥ በእስራኤል በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።

    በጋዛ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርን እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሁም የሐማስ መሪ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል ተከስሰዋል።

  12. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጦርነቱን ለማስቆም ኢራን የኒውክሌር ማብልጸግ አቅሟን መቀነስ አለባት አሉ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በኢራን ላለፉት ሰባት ወራት እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የኒውክሌር ማበልጸግ አቅሟ ላይ ጉልህ ቅነሳ ማድረግ አለባት ሲሉ ተናገሩ።

    ይህ የምክትል ፕሬዚዳንቱ አስተያየት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ለሚደረጉ ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የኒውክሌር ስምምነቶች ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ያሳየ ነው ተብሏል።

    ቫንስ ሰኞ ዕለት ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ አሜሪካ ስለ ወደፊቱ የቅነሳ እርምጃዎች ኢራን የምትሰጠውን ማረጋገጫ እንደማትቀበል ገልጸው፤ በምትኩ ቴህራን ዩራኒየም የማበልጸግ መርሃ ግብሯን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድትወስድ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

    "የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ካልፈለጋችሁ፣ ታዲያ ለምን እስከ 60 በመቶ የዳበረ ዩራኒየም ያስፈልጋችኋል?" ሲሉ ቫንስ ተናግረዋል። ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ አቅሟን በመቀነስ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ላለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየት እንደምትችልም በዚህ ወቅት አስረድተዋል።

    ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ኢራን እና አሜሪካ ጦርነቱን ያስቆማል፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ያስከፍታል ያሉትን ዕቅድ አቅርበዋል።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን ያቀረበችውን የሰላም ዕቅድ ውድቅ አድርገው በኅዳር ወር ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ ወታደራዊ እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል።

    ቫንስ ዋሺንግተን የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ክፍት መሆኗን ተናግረው ከቴህራን ወገን ተጨባጭ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።

    አክለውም ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ውይይቶች ቢደረጉም፣ በቴህራን የመጨረሻውን ውሳኔ የሚወስነው አካል ማን እንደሆነ ዋሽንግተን አሁንም እርግጠኛ አለመሆኗን ገልፀዋል።

  13. በየመን የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት ወቅት ሁቲዎች የኤደን አውሮፕላን ማረፊያን አጠቁ

    በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲዎች በኤደን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በባሌስቲክ ሚሳዔል እና ፈንጂ በጫኑ ድሮኖች ጥቃት መፈጸማቸው ተሰማ።

    የየመን ትራንስፖርት ሚኒስቴር ስለጥቃቱ ባወጣው መግለጫ ከካይሮ የሚመጣ አውሮፕላን ለማረፍ ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውት እያለ አንድ ሚሳዔል አውሮፕላን መንደርደሪያው አቅራቢያ መውደቁን አስታውቋል።

    በየመን በተለያዩ ግንባሮች የሚካሄዱ ጦርነቶች ተባብሰው የቀጠሉ ሲሆን በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በሪያድ ሰሜናዊ ክፍል የተወነጨፈን ባሌስቲክ ሚሳዔል ማክሸፉን አስታውቋል።

    ከግብፅ ተነስቶ ወደ ኤደን አውሮፕላን ማረፊያ ተቃርቦ የነበረው አውሮፕላን መዳረሻውን ቀይሮ ጂዳ እንዲያርፍ መደረጉን ባለሥልጣናቱ ጨምረው አስታውቀዋል።

    በመንደርደሪያው ላይ የነበሩ ሁለት አውሮፕላኖች ተጨማሪ ጥቃቶች ሊኖር ይችላል በሚል ፍራቻ ከስፍራው እንዲነሱ መደረጉንም ገልፀዋል።

    ሁቲዎች ፈጸሙት ስለተባለው ጥቃት እስካሁን ድረስ የሰጡት አሰተያየት የለም።

    በየመን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን መንግሥት የሚደግፈው ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጥምረት ከሪያድ በስተሰሜን ሁቲዎች ያስወነጨፉትን ባላስቲክ ሚሳኤልን ማክሸፉን ተናግሯል።

    በሁቲ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሳናዓ ላይ ለማስወንጨፊያነት የሚያገለግል ስፍራን እየተከታተሉ መሆኑን እና እንደሚያወድሙት ያስታወቁት የሳዑዲ ባለሥልጣናት ነገር ግን ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

    የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ በሰጡት መግለጫ ቡድኑ በሪያድ የሚገኘውን የኪንግ ካሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በበርካታ ድሮኖች ማጥቃቱን ተናግረዋል። በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ስለተፈፀመ ጥቃት ከሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ አልተገኘም።

    ጥቃቶቹ የተከሰቱት በሳዑዲ የሚደገፉ የመንግሥት ኃይሎች በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የቀይ ባሕር ዳርቻን በተቆጣጠሩት ሁቲዎች ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከወሰዱ በኋላ በየመን በተለያዩ ግንባሮች ላይ ውጊያው እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ነው።

    ለየመን መንግሥት ኃይሎች፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት የአየር ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሲሆን በዚህ ሳምንት የቀይ ባሕር ዳርቻ ስትራቴጂካዊ አካል የሆነውን ባብ ኤል-ማንዳብ ወሽመጥ እና የሞቻ ከተማን መልሶ ለመያዝ ጥቃት ጀምረዋል። ይህም ሁቲዎችን ባለፈው ወር ከያዟቸው አካባቢዎች ለቅቀው እንዲወጡ አድርጓል።

  14. የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን ገለጹ

    የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳዓር ከኢትዮጵያው አቻቸው ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በስልክ መወያየታቸውን ገለጹ።

    “ከወዳጄ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተናል” በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰዓር ገልጸዋል።

    ነገር ግን ወቅታዊ ያሏቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ ሚኒስትሩ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም።

    አክለውም በውይይታቸው ስለኢትዮጵያ አንድነት እና መረጋጋት አስፈላጊነት እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋትን ለሁለቱ አገራት ስላለው የጋራ ጥቅም መነጋገራቸውን አመልክተዋል።

    ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ አገራት እና ተቋማት እንዳሳሰባቸው ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

    የእስራኤሉ ሚኒስትር አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ጥብቅ ወዳጅነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደምትመለከተው እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርም በትብብር እንደምትሠራ ገልጸዋል።

    የሁለቱን ሚኒስትሮች የስልክ ውይይት በተመለከተ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

    ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የአገራቱ ባለሥልጣናት በአገራቱ ውስጥ ጉብኝት አድርገዋል።

  15. ኢራን እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥራቸው ሥር መሆኑን በየፊናቸው እየተናሩ ነው

    ኢራን እና አሜሪካ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት የሚመረተው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና ጋዝ ይተላለፍበት የነበረው የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥራቸው ሥር መሆኑን እየገለጹ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የወሽመጡ መከፈት አጠያያቂ ሆኗል።

    ኻታም አል አንቢያ የሚባለው የኢራን የጦር ኃይሎች ማዘዣ ማዕከል ከፍተኛ አዛዦች መካከል አንዱ፣ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ በኢራን የጦር ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    በተመሳሳይም የአሜሪካ ጦር ኃይል ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) በበኩሉ በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው የባሕር እንቅስቃሴ ዕገዳ ተግባራዊ መሆኑን እንደቀጠለ ገልጾ፣ እስካሁን 130 የንግድ መርከቦች ላይ ክልከላ በመጣሉ ወደመጡበት መመለሳቸውን አስታውቋል።

    ብርጋዲየር ጄነራል ሻምኻል ጃፋሪ ለኢራን ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ደግሞ “የጠላት መርከቦች እና የባሕር ላይ ወታደራዊ መሣሪያዎች ከኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ ጠረፎች በጣም ርቀው እንዲሰማሩ አስገድደናቸዋል” ብለዋል።

    እንዲሁም የኢራን ኃይሎች ከተቃራኒው ወገን መሣሪያዎችን “ማርከዋል” በማለት ገልጸዋል፤ ነገር ግን ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጡም።

    በሌላ በኩል፣ ሴንትኮም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፣ በኢራን ላይ የተጣለውን የባሕር ዕገዳ በማስፈጸም ሂደት 130ኛውን የንግድ መርከብ ወደ መጣበት እንዲመለስ መደረጉን አስታውቋል።

    እንደ የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ መረጃ፣ በኢራን ላይ የተጣለው ዕገዳ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ እንደገና የተጀመረ ሲሆን፣ ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት ወይም ከኢራን ወደቦች ለመውጣት የሚሞክሩ መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ የሚደያርግ ዕገዳ ነው።

    ዕዙ በተጨማሪ የአሜሪካ ኃይሎች ትዕዛዛቸውን ያልተከተሉ ሦስት መርከቦችን እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ እርምጃ እንደተወሰደባቸው እና ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ 13 የንግድ መርከቦችን ማውደማቸውን አስታውቋል።

    ሴንትኮም እነዚህ መርከቦች ዕገዳውን ጥሰዋል ወይም በኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃይሎች የሚመራ በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት ሀብት የሚያንቀሳቅስ የምሥጢራዊ እንቅስቃሴ አካል ነበሩ ብሏል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ብራድ ኩፐር የአሜሪካ ጦር ኃይል በዚህ ተልዕኮ ላይ አተኩሮ እንደሚቀጥል እና ዕገዳውን ለማለፍ በሚሞክሩ መርከቦች ላይ ፈጣን እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቀዋል።

    ሴንትኮም መርከበኞች በኦማን ባሕር እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲንቀሳቀሱ የባሕር ላይ መመሪያዎችን እንዲከተሉ እና በሬዲዮ ቻናል 16 በኩል ከአሜሪካ ባሕር ኃይሎች ጋር እንዲገናኙ አሳስቧል። ሆኖም የአሜሪካ መርከቦች የት እንደሚገኙ ወይም ከኢራን ድንበር ምን ያህል እንደራቁ አልገለጸም።

    የኢራን ወታደራዊ ባለሥልጣናት በቅርብ ቀናት ውስጥ የአሜሪካ መርከቦች ከአካባቢው እየራቁ እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ ቆይተዋል።

    የአብዮታዊው ዘብ ዋና አዛዥ አማካሪ ቦርድ ኃላፊ አድሚራል አሊ ፋዳቪ በቅርቡ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ፣ በሆርሙዝ ሰርጥ፣ በኦማን ባሕር እና በሰሜናዊ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ የአሜሪካ ወታደራዊ መርከብ እንደማይንቀሳቀስ እና የአሜሪካ ኃይሎች ከኢራን ድንበር ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

    የኢራን ጦር ኃይሎች ምክትል አስተባባሪ አድሚራል ሃቢቦላህ ሳያሪ ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ወደ ደቡባዊ ሕንድ ውቅያኖስ ማፈግፈጓን እና የባሕር ላይ ዕገዳውን ከኢራን የጦር መሣሪያዎች የርቀት ክልል ውጭ ሆና እያስፈጸመች መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ እንደምትቆጣጠር ማሳወቋን እንዲሁም ሴንትኮም የዘረዘራቸውን እርምጃዎች እና አሃዞች ከገለልተኛ ምንጮች እስካሁን አልተረጋገጡም። እንዲሁም በኢራን ወደቦች ላይ የቀጠለው የባሕር ላይ ዕገዳ ብቻውን የሆርሙዝ ወሽመጥን በሙሉ ቁጥጥሩ ሥር ማዋሉን አያረጋግጥም።

  16. በናይጄርያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ 32 ሰዎች ሞቱ

    በናይጄርያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ 32 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ የሦስት ቀን ብሔራዊ ሐዘን አወጁ።

    አውሮፕላኑ ከቤኒን ሲቲ ወደ ሌጎስ እየተጓዘ ሳለ ትናንት ጠዋት በደቡብ ናይጄርያ ኦንዶ ግዛት ተከስክሷል።

    ፕሬዝዳንት ቲኑቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አውሮፕላኑ በባሕር ኃይል የጦር ሰፈር አቅራቢያ በሚገኝ ረግረጋማ ቦታ ላይ የተከሰከሰ ሲሆን፣ የሰዎች ልብስ እና ጫማ ተገኝቷል።

    አደጋው የተከሰተበት ሥፍራ በጭስ ታፍኗል።

    ለሞቱት 25 ተሳፋሪዎች እና ሰባት የበረራ ሠራተኞች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ የተሟላ ምርመራ እንዲከፈት ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    “ለወታደሮቻችን እና ለመላው አገራችን አሳዛኝ ወቅት ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    የናይጄርያ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብም አዝዘዋል።

  17. በኬንያ የመጀመሪያው የኢቦላ ታማሚ ሕይወቱ አለፈ

    ላለፉት ሰባት ዓመታት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይኖር የነበረ ኬንያዊ በኢቦላ ተይዞ ሕይወቱ አለፈ።

    ግለሰቡ በአገሪቱ በኢቦላ የሞተ የመጀመሪያው ሰው ነው።

    የጤና ሚኒስትር አደን ዱአሌ እንዳሉት ግለሰቡ የታመመው ከወር በፊት ሲሆን፤ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና ሲሰጠው ነበር።

    ናይሮቢ ከደረሰ ከቀናት በኋላም ሕይወቱ አልፏል።

    ያሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 23 በአውሮፕላን ማረፊያ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ነበር ዘመዱ ወደ ሆስፒታል የወሰዱት። ሆኖም ትላንት ሰኞ መስከረም 25 ሕይወቱ ማለፉን የጤና ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2026 በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ4,000 በላይ ሰዎች በኢቦላ ሞተዋል።

    በኡጋንዳ ሁለት ሰዎች በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። ነሐሴ ላይ አገሪቱ ከበሽታው ነጻ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

    በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተስፋፋው የኢቦላ ዓይነት ክትባት ያልተገኘለት ቡንዲቡግዮ ዝርያ ነው።

    የኬንያ የጤና ሚኒስትር እንደተናገሩት፤ ሟቹ መጀመሪያ ላይ በመኪና ኡጋንዳ፣ ካምፓላ ገብቶ ወደ ናይሮቢ ደግሞ በአውሮፕላን ገብቷል።

    ሆስፒታል ከገባ በኋላ ለይቶ ማቆያ ክፍል ተወስዷል።

    ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው 28 ሰዎች ተለይተዋል። ይህም ቤተሰቦቹን እና የሕክምና ባለሙያዎችን ይጨምራል።

    ከግለሰቡ ጋር አውሮፕላን ውስጥ አብረው የተጓዙ 23 ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሠራተኞችን ለማግኘትም እየተሞከረ ይገኛል።

  18. ሳዑዲ በፌስቡክ ጽሑፍ ምክንያት ሞት የተፈረደበትን ሰው እንድትምር ጥሪ ቀረበ

    “ልጄ ለፈጸመው ስህተት እንድትምሩት እለምናለሁ። እባካችሁ ይቅር በሉትና መልሱልን” ሲሉ የሞት ፍርደኛው እናት ተማፀኑ።

    እናት ራሳማኒካም ዮጋላክሽሚ የበኩር ልጃቸውን ሕይወት ለማዳን የተማጸኑት በእምባ ታጅበው ነበር።

    የ24 ዓመቱ ስደተኛ ሠራተኛ አኖጃን ሲቫራሳ፣ በፌስቡክ ላይ ባሰፈረው አስተያየት እስልምናን እና ነቢዩ መሐመድን ተሳድቧል በሚል በሳዑዲ ይግባኝ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው ሞት የተፈረደበት።

    ጉዳዩ በመላው ስሪላንካ ድንጋጤ እና ጭንቀት የፈጠረ ሲሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች ፍርዱ እንዲቀለበስ የፊርማ ማሰባሰብ ተግባር አከናውነዋል።

    በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግሥት ተቋማትም ለግለሰቡ ምሕረት እንዲደረግለት በጋራ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እያካሄዱ ነው።

    ሆኖም ከመስከረም 18 ጀምሮ ስለ አኖጃን ሁኔታ ምንም አዲስ መረጃ እንዳላገኙ ቤተሰቦቹ ገልፀዋል። የስሪላንካ መንግሥት በበኩሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እተደረጉ ባሉበት ወቅት ቤተሰቡ ተጨማሪ መግለጫዎችን ከመስጠት እንዲቆጠቡ መመሪያ ሰጥቷል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት ቅጣቱ መቼ እንደሚፈጸም በይፋ ባለመግለፃቸው፣ ፍርዱ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን ግልጽ አይደለም።

    ሳዑዲ አረቢያ ሞት ስለተፈረደበት ሰው ለቤተሰቦች ወይም ለሚመለከተውን የውጭ አገር ኤምባሲ አስቀድማ ሳታሳውቅ ቅጣቱን በመፈፀም የምትታወቅ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ዘመዶች እንዲያውቁ የሚደረገው ቅጣቱ ከተፈጸመ በኋላ ነው።

    አኖጃን ለሞት ፍርዱ የዳረገው ክስ የተመሰረተበት፣ በስሪላንካ በተካሄደ የሂንዱዎች ሃይማኖታዊ ጉዞ ወቅት ከተከሰተ አንድ ክስተት በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ በተነሳ ክርክር ምክንያት ነው።

    ይሄውም በሰኔ መጨረሻ አካባቢ፣ አንድ ሙስሊም ወጣት ከሂንዱ አማኞች ጉዞ በኋላ አንድን ውሻ በእርግጫ ሲመታ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት መሰራጨቱ ነው። ይህም ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ክርክር አስነስቷል።

    በዚያ ክርክር ውስጥ አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ አንድን የሂንዱ አምላክ የሚያጣጥል እና የሚያዋርድ አስተያየት መጻፉን ተከትሎ አኖጃን በታሚል ቋንቋ በሰጠው ምላሽ ነቢዩ መሐመድን የሚዘልፍ ይዘት ያለው ጽሑፍ አስፍሯል።

    ምንም እንኳን አኖጃን አስተያየቱን ወዲያውኑ ሰርዞ ይቅርታ የሚጠይቅ ቪዲዮ ቢለቅም፣ የጽሑፉ ቅጂ ለቀጣሪው እና ለሳዑዲ ባለሥልጣናት ቀርቦ በሐምሌ ወር እንዲታሰር አድርጎታል።

    በሳዑዲ አረቢያ ፍርድ ቤቶች በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀሎች ወይም በግድያ ወንጀል ምክንያት ከሚፈረዱ የሞት ቅጣቶች ጋር ሲነጻጸር፣ በሃይማኖት ምክንያት የሚፈጸሙ የሞት ቅጣቶች በአንጻራዊነት እጅግ አነስተኛ ናቸው።

    ይሁን እንጂ አኖጃን ይቅርታ እንዲደረግለት ስለቀረቡት ጥያቄዎች ሳዑዲ በይፋ ያለችው ነገር የለም።

  19. ከኤርትራ ጋር ያለው ውጥረት መጨመሩ ቀጣናዊ ግጭት ሊያስከትል እንደሚችል የአውሮፓ ኅብረት አስጠነቀቀ

    የአውሮፓ ኅብረት፣ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት እየተባባሰ መቀጠሉ እንዲሁም በቀጣናው በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት መጨመሩ እንዳሳሰበው ገለፀ።

    ይህ ሁኔታ በመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከባድ መዘዝ ሊኖረው የሚችል “ሰፊ ቀጣናዊ ግጭትን ሊያስከትል ይችላል” ሲል ኅብረቱ አስጠንቅቋል።

    የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ትላንት ሰኞ መስከረም25/2019 ዓ.ም. በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ በሁሉም ግንባሮች በአስቸኳይ ውጥረቶች እንዲረግቡ ጠይቋል። ሁሉም አካላት ውጥረቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ እርምጃዎች እና ትርክቶች እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

    የፕሪቶሪያውን በዘላቂነት ግጭት የማቆም ስምምነት የፈረሙ አካላት በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን ዳግም ማረጋገጥ እንዳለባቸው ኅብረቱ ጨምሮ አሳስቧል።

    በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን በማክበር የሲቪል ዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለባቸው መግለጫው አስገንዝቧል።

    የሁሉም አገራት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሊከበር ይገባል የሚል ፅኑ አቋም እንዳለው በድጋሚ ያረጋገጠው ኅብረቱ፣ የውጭ አካላት “ጣልቃ ገብነትን ሊያስወግዱ ይገባል” ብሏል።

    እነዚሁ የውጭ ኃይሎች ሁኔታዎች በተጨማሪነት እንዳይባባሱ ለማድረግ ተጽዕኗቸውን እንዲጠቀሙ እና የፖለቲካ መፍትሄዎችን እና ዲፕሎማሲን እንዲያበረታቱም ኅብረቱ ጠይቋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ለሰላማዊ ጥረቶች ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነትም በመግለጫው ጠቅሷል።

  20. ትራምፕ የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከእንግሊዝ የወጡት ‘ስጋት’ ስላለ መሆኑን ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን እንግሊዝ ከሚገኘው የጦር ሰፈር ያስወጣችው በጦር ሰፈሩ ላይ የተጋረጠ “የተወሰነ ስጋት” ስላለ መሆኑን ተናገሩ።

    የጦር ሰፈሩ ውስጥ የሚገኙ ቦምብ ጣይ ቢ-1 አውሮፕላኖች ወደ አሜሪካ እንዲዘዋወሩ መደረጉን ፔንታገን አረጋግጧል።

    ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ አሜሪካ “ስጋት” መኖሩን በመረዳቷ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹ እንዲወጡ ወስናለች።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ በበኩላቸው ራፍ የጦር ሰፈር ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ብለዋል።

    ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የዩኬን “ፖሊስ፣ መከላከያ እና ደኅንነት ባልደረቦች” ሲያሞግሱ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

    በአውሮፓውያኑ መስከረም 27 በራፍ የጦር ሰፈር አቅራቢያ “አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች” እንደታዩ ለፖሊስ ጥቆማ ደርሷል።

    ከዚህ በኋላ በተከሰተ አዲስ ስጋት ምክንያት አሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿን እንዳስወጣች የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ትራምፕ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ስጋት” እንዳለ ገልጸዋል።

    “የተወሰኑ ስጋቶች አሉ። ጠላትን ከማማለል መያዝና ማሸነፍ ይሻላል። [ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹን] ለምን እዚያ እንተዋቸዋለን? ብዙም ሳይርቁ ወደ ሌላ ቦታ ተወስደዋል” ብለዋል።

    ስጋት የጋረጡትን አካላት ማንነት አሜሪካ እንደምታወቅ ቢጠቅሱም ማንነታቸውን ይፋ አላደረጉም።